ፈረንሳይ ከሩሲያ ጋር ጦርነት ሊጀመር ይቸላል በሚል ፍራቻ የብሔራዊ አገልግሎትን በድጋሚ ልትጀምር ነው

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን

የፎቶው ባለመብት, Shutterstock

ፈረንሳይ ከሩሲያ ጋር ግጭት ሊፈጠር ይችላል በሚል ፍርሃት ምክንያት የተወሰነ የወታደራዊ አገልግሎት ዓይነትን ዳግም ልትጀምር ነው።

የወታደራዊ አገልግሎት ምልመላ ከተቋረጠ ከ25 ዓመታት በላይ በኋላ በሚጀመረው አገልግሎት የሚሳተፉ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ለ10 ወራት እየተከፈላቸው በፈቃደኝነት ወታደራዊ ስልጠና እንዲያገኙ ያደርጋል።

"አደጋን ለማስወገድ ብቸኛው መንገድ መዘጋጀት ነው" ሲሉ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በደቡብ ምሥራቅ ፈረንሳይ ግሬኖብል አቅራቢያ በሚገኝ ጦር ሰፈር ዕቅዱን ሲያስታውቁ ተናግረዋል።

"አገሪቱን ለመከላከል፣ ዝግጁ ለመሆን እና ለመከበር መዘጋጀት አለብን" ብለዋል።

አዲሱ "ብሔራዊ አገልግሎት" ከወራት በኋላ መተግበር የሚጀመር ሲሆን ተሳታፊዎች በወር ቢያንስ 800 ዩሮ ይከፈላቸዋል።

"በዚህ እርግጠኛ መሆን በማይቻልበት ዓለም ውስጥ፣ ጦርነት እየተባባሰ ነው" ብለዋል ማክሮን። የጦር ኃይሉ ከሚቀላቀሉት ወጣቶች ተጠቃሚ ይሆናሉ ሲሉ አክለዋል። "ይህ በወጣቶቻችን ላይ የመተማመን ተግባር ነው።"

በሚቀጥለው ዓመት ቁጥሩ 3,000 ላይ ይገደባል ቢባልም፣ በ2035 ወደ 50 ሺህ እንዲጨምር ታቅዷል።

ፈረንሳይ በአሁኑ ጊዜ ወደ 200 ሺህ ጦር ሲኖራት እና ተጨማሪ 47 ሺህ የተጠባባቂ ወታደሮች አሏት። አዲሱ ዕቅድ ባለሙያዎችን፣ የተጠባባቂ ወታደሮችን እና በጎ ፈቃደኞችን ያቀፈ ይሆናል።

የሩሲያን ጥቃት በመፍራት በተለያየ ቁጥር የወታደራዊ አገልግሎት መርሃ ግብሮችን ከጀመሩ አገሮች ፈረንሳይን አንዷ ያደርጋታል።

ቤልጂየም እና ኔዘርላንድስ የበጎ ፈቃድ ወታደራዊ አገልግሎት አስተዋውቀዋል። ጀርመንም ተመሳሳይ ነገር እያቀደች ነው።

በዚህ ወር ብቻ የቤልጂየም የመከላከያ ሚኒስቴር 17 ዓመት ለሞላቸው ወጣቶች በወር ወደ 2,000 ዩሮ እንደሚከፍል ገልጾ በፈቃደኝነት እንዲሳተፉ የሚጋብዝ ደብዳቤ አውጥቷል።

ሊቱዌኒያ እና ላትቪያ ምልምሎች በዕጣ የሚመረጡበት የግዴታ መርሃ ግብሮች አሏቸው። በቅርቡ ኔቶን የተቀላቀለችው ስዊድን፣ በምርጫ ላይ የተመሠረተ ከዘጠኝ እስከ 15 ወራት የሚፈጅ ወታደራዊ አገልግሎት ጀምራለች።

እንደ ፊንላንድ እና ግሪክ ያሉ አንዳንድ የአውሮፓ አገሮች ወታደራዊ አገልግሎቱን አላቆሙም ነበር።

እን ደእንግሊዝ እና ስፔንን ያሉ አገሮች ግን አገልግሎቱን እንደገና ለማስተዋወቅ ምንም ዕቅድ የላቸውም።

ፈረንሳይ ወታደራዊ አገልግሎቶችን ያቋረጠችው እአአ በ1990ዎቹ ነበር

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የፈረንሳይ የጦር አዛዦች አዲሱን እርምጃ በስፋት ይደግፋሉ። ይህም ወታደሮችን ለመደገፍ እና ከጦር ሜዳ ውጭ ባሉ ተግባራት ሊተኳቸው የሚችሉ የሰለጠኑ ወታደሮችን እንደሚያስገኝ ተስፋ ያደርጋሉ።

ብዙ በጎ ፈቃደኞችም ወደ ወታደራዊ ሙሉ ለሙሉ እንደሚገቡ ተስፋ ይደረጋል።

"አዲሱ ወታደራዊ አገልግሎት የጦር ኃይሎችን ወደ ውህደት አቅጣጫ ያንቀሳቅሰናል" ሲሉ የአገሪቱ ምክር ቤት የመከላከያ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ቶማስ ጋሲሉ ተናግረዋል።

ከሩሲያ ጋር ሊፈጠር የሚችል የግጭት ስጋት፣ የፈረንሳይ ብሔራዊ ውይይት አካል ሆኗል። መንግሥት በማኅበራዊ ሚዲያ በኩል አስተያየቶችን ለመመርዝ በሚደረጉ ሙከራዎች ወይም ከራዳር በታች በሚፈጠሩ ክስተቶች ላይ ማስጠንቀቂያውን ከፍ አድርጓል።

በቅርቡ አዲስ የተሾሙት የጦር አዛዡ ጄኔራል ፋቢየ ማንደ የፈረንሳይ ወታደራዊ ዕቅድ በሚቀጥሉት ሦስት ወይም አራት ዓመታት ውስጥ ከሩሲያ ጋር ግጭት እንደሚፈጠር በመገመት የተገነባ መሆኑን መናገራቸው የስጋት መጠኑን ከፍ አድርጎታል።

በቅርቡ አዲስ የተሾሙት የጦር አዛዡ ጄኔራል ፋቢየ ማንደ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ባለፈው ሳምንት ከከንቲባዎች ጋር በነበራቸው ቆይታ ፈረንሳይ የጎደላት የመስዋዕትነት መንፈስ መሆኑን በመግለጽ በጦርነት "ልጆችን የማጣት" ዕድል ሊኖር ስለመቻሉ እንዲያስቡ አሳስበዋል።

አስተያየቱ በርካታ ትችትን ከአየቅጣጫው ያስተናገደ ሲሆን ማክሮንም ወጣት ምልምሎችን ወደ ዩክሬን ለመላክ ምንም ዓይነት ዕቅድ እንደሌለ አረጋግጠዋል።

የሕዝብ አስተያየት እንደሚያሳየው አብዛኛው ዜጋ የፈቃደኝነት ወታደራዊ አገልግሎቱን ይደግፋል። በዚህ ሳምንት የተደረገ የኤላቤ ጥናት እንዳመለከተው 73 በመቶ የሚሆኑት የአገሪቱ ዜጎች እርምጃውን ደግፈዋል። ከ25-34 ዓመት እድሜ ያላቸው ወጣቶች ዝቅተኛውን ድጋፍ ቢሰጡም፤ በዚህ የዕድሜ ክልል ጭምር 60 መቶዎቹ ይደግፉታል።

ቢቢሲ ከፓሪስ ጎዳናዎች ላይ በሰበሰበው የሕዝብ አስተያየት ተመሳሳይ ውጤት ታይቷል።

"ጥሩ ነገር ነው" ሲል የ22 ዓመቱ ተማሪ ሉዊ ተናግሯል። "ሠራዊቱን የበለጠ ለማሳደግ ይረዳል፣ ነገር ግን አገርን የበለጠ መውደጃ መንገድ ነው።"

ሌላኛው ተማሪ ኢላን ደግሞ "በወታደራዊ አገልግሎት ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ ሰዎችን ታገኛለህ። አዲስ ዕይታ ይፈጥርልሃል... ከሌሎች ሰዎች ጋር መነጋገር፣ መተማመን እና አብሮ መኖርን ትማራለህ" ብሏል።

"በጋዜጦች ላይ ካነበብኩት አንጻር፣ ሠራዊታችን ያን ያህል ጠንካራ አይደለም። ለወደፊቱ መዘጋጀት ካለብን ጥሩ ሀሳብ ሊሆን ይችላል" ብላለች ዲዛይነር ብሪጊት።

የ21 ዓመቷ ላሊ በዚህ አልተስማማም። "ከዚህ የበለጠ አስፈላጊ ጉዳዮች አሉ ብዬ አስባለሁ።" ፕሬዝዳንቱ ለወጣቶች የአእምሮ ጤንነታቸው እና የፋይናንስ ሁኔታቸው ከማሰብ፤ ወታደራዊ አገልግሎት ላይ ትኩረት ማድረጋቸው ያሳዝናል" ብላለች።

ከሶቪየት ህብረት ውድቀት በኋላ ነበር በ1996 የወቅቱ ፕሬዝዳንት ዣክ ሺራክ የወታደራዊ አገልግሎትን ለማቆም ውሳኔ ያሳለፉት።

ወጣት ወንዶች የግዴታ ወታደራዊ ስልጠና መስጠት ከፈረንሳይ አብዮት ጀምሮ ተግባራዊ ነበር።