ዩክሬን እስከ 100 ፈረንሣይ ሠራሽ ራፋሌ ተዋጊ ጄቶችን ልታገኝ ነው

ዜሌንስኪ እና ማክሮን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ዩክሬን እስከ 100 የሚደርሱ ፈረንሳይ ሠራሽ ራፋሌ ኤፍ 4 ተዋጊ አውሮፕላኖች እንዲሁም የተሻሻሉ የአየር መከላከያዎችን ልታገኝ ነው።

እነዚህ የጦር መሣሪያዎች ኪየቭ ራሷን ከሩሲያ ከባድ ጥቃቶች የመከላከል አቅሟን ለማሳደግ ያስችሏታል ተብለዋል።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ከፈረንሳዩ አቻቸው ኢማኑኤል ማክሮን ጋር በፓሪስ አቅራቢያ በሚገኝ የአየር ማረፊያ ስምምነቱን የያዘ ሰነድ ከተፈራረሙ በኋላ እርምጃውን "ታሪካዊ" ሲሉ አድንቀዋል።

የራፋሌ ኤፍ 4 ጄቶቹን እስከ እአአ 2035 ድረስ ሙሉ በሙሉ ለዩክሬን ለማስረከብ የታቀደ ሲሆን የጠላትን አውሮፕላኖች እንቅስቃሴ የሚጠልፉ ድሮኖችን በጋራ ማምረት በዚህ ዓመት ይጀምራል ተብሏል።

እስካሁን ድረስ የጦር መሣሪያዎችን ግዢ ወጪ ለመሸፈን የገንዘብ ምንጭ ከየት እንደሚገኝ ያልታወቀ ቢሆንም ነገር ግን ፈረንሣይ የአውሮፓ ኅብረት ድጋፍን ለማግኘት እና የታገዱ የሩሲያ ንብረቶችን ለመጠቀም አቅዳለች።

የሩሲያን እንዳይንቀሳቀሱ የታገዱ ንብረቶችን መጠቀም 27 አባላት ያሉትን የአውሮፓ ኅብረትን ለሁለት የከፈለ ውሳኔ ነው።

ዜሌንስኪ ሰኞ ዕለት ከማክሮን ጋር በጋራ በሰጡት መግለጫ "ይህ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ለ10 ዓመታት የሚቆይ ስትራቴጂያዊ ስምምነት ነው" ብለዋል።

በተጨማሪም ዩክሬን "በጣም ጠንካራ የፈረንሳይ ራዳሮች" ስምንት የአየር መከላከያ ስርዓቶች እና ሌሎች የተሻሻሉ የጦር መሣሪያዎችን ታገኛለች ብለዋል።

ዜሌንስኪ እንደዚህ ያሉ የተሻሻሉ ስርዓቶችን መጠቀም "የአንድን ሰው ሕይወት መጠበቅ ማለት ነው ... ይህ በጣም አስፈላጊ ነው" ሲል በመግለጫቸው ላይ አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።

የፈረንሳይ አየር ኃይል ንብረት የሆነው ራፋሌ ኤፍ 4 የኔቶ የጥበቃ ተልዕኮ አካል ሆኖ በባልቲክ ባህር ላይ ሲበርር

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የፈረንሳይ አየር ኃይል ንብረት የሆነው ራፋሌ ኤፍ 4 የኔቶ የጥበቃ ተልዕኮ አካል ሆኖ በባልቲክ ባህር ላይ ሲበርር
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሩሲያ ከቅርብ ወራት ወዲህ በዩክሬን ላይ በሰው አልባ አውሮፕላኖች እና በሚሳኤሎች የምትፈጽመውን ጥቃት በመጨመር በኤሌትሪክ ኃይል እና በባቡር መሠረተ ልማት ላይ ውድመትን አድርሳለች።

በዚሀም የተነሳ በመላ አገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የኤሌትሪክ ኃይል መቆራረጥ ደርሷል።

ኪየቭ እና ምዕራባውያን አጋሮቿ የጦር ወንጀል ሲሉ በገለጹት በዚህ ጥቃት በርካታ ሰላማዊ ዜጎች ተገድለዋል።

በሰሜን ምሥራቅ ዩክሬን በምትገኘው ባላክሊያ ከተማ ባለፈው ምሽት የሩስያ ሚሳኤል ጥቃት ሦስት ሰዎች ሲገደል 15 ደግሞ ቆስለዋል ሲሉ የአካባቢው ባለስልጣናት ተናግረዋል።

ከዜሌንስኪ ጋር በመሆን መግለጫ የሰጡት ማክሮን "100 ራፋኤል እያቀድን ነው፤ ያ በጣም ትልቅ ነው ። ለዩክሬን ጦር ኃይል እንደገና መወለድ የሚያስፈልገው ይህ ነው" ብለዋል።

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት አክለውም ዩክሬን ለሚመጣው ለማንኛውም ነገር እንድትዘጋጅ መርዳት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

እነዚህ ራፋኤል ተዋጊ ጄቶች የዩክሬንን ሰማይ ለመጠበቅ ወሳኝ ተደርገው ተቆጥረዋል። ምክንያቱም አገሪቱ በድንበር አካባቢዎች እና በከተሞቿ ላይ የሚፈጸሙ የረዥም ርቀት የአየር ጥቃትን ለመከላከል አቅም የላትም።

የዩክሬን የመከላከያ ተንታኝ ሰርሂይ ኩዝሃን "ሩሲያውያን በወር 6000 የሚወነጨፉ ቦምቦችን እየተጠቀሙ ነው። ለአየር ላይ ውጊያ የሚያገለግል 200 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚሸፍን የፈረንሳይ መሣሪያ ማግኘቷ አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም ሩሲያውያን 230 ኪ.ሜ ርቀት የሚሸፍን የራሳቸው ስሪት የሆነ አላቸው።"

የሮያል ዩናይትድ ሰርቪስ ኢንስቲትዩት ባልደረባው ጀስቲን ብሮንክ በበኩላቸው "ልዩነት የሚፈጥሩት በጊዜ ወሰን እና አብሯቸው በሚመጡት ሚሳኤሎች ላይ የተመሰረተ ነው" ብለዋል

ይህ ከተራ የግዢ ትዕዛዝ ይልቅ የረዥም ጊዜ የፖለቲካ ስምምነት ነው። ስለዚህ ጥቂቶች ይህ ስምምነት የሩሲያን ወረራ ይቀይረዋል ብለው እየጠበቁ ነው።

ምዕራባውያን የጦር መሣሪያ ድጋፍ ለማድረግ የሚገቡት ቃል በሥልጠና እና በመለዋወጫ ድጋፍ የታጀቡ ካልሆኑ ውጤታማነታቸው እምብዛም ነው።

ጀርመን ሠራሹ ሊዮፓርድ 2 ታንክም ሆነ አሜሪካ ሠራሹ ኤች 16 ተዋጊ አውሮፕላን ሁሉም ጠንከር ያለ ሥልጠና እና የመለዋወጫዎች አቅርቦትን እና የባለሙያዎች ድጋፍን ይጠይቃሉ።

ከራፋኤል ጋር የሚነሳው ሌላው ጥያቄ የግዢውን ወጪ ማን ይሸፍናል የሚለው ነው።

ፈረንሳይ ለኪየቭ የምታደርገው ድጋፍ ውስጥ ታካትተዋለች ወይም የአውሮፓ ኅብረት ስምምነቱን ለማስፈጸም ብድር ያቀርባል የሚለው በሂደት የሚታይ ይሆናል።