ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ሥልጠና ካምፕ መገንባቱን የሮይተርስ የምርመራ ዘገባ አሳየ
የእርስ በስር ጦርነት ውስጥ ከምትገኘው ሱዳን ጋር በሚጎራበተው ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ የአማጺው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል የሥልጠና ካምፕ መገንባቱን ከምንጮች እና ከሳተላይት ምሥሎች ማረገጋጡን የዜና ወኪሉ ሮይተርስ አስታወቀ።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ሥልጠና ትሰጥበታለች በተባለው በዚህ ካምፕ ውስጥ የሚገኙት አብዛኞቹ ምልምሎች ኢትዮጵያዊ እንደሆኑ ምንጮች መናገራቸውንም የዜና ወኪሉ ዘግቧል።
ሮይተርስ ዛሬ ማክሰኞ የካቲት 3/2018 ዓ.ም. ያወጣውን የምርመራ ዘገባ ያጠናቀረው የኢትዮጵያ መንግሥት እና የዲፕሎማቲክ ምንጮችን በመጠቀም እንደሆነ ጠቅሷል። ከኢትዮጵያ የደኅንነት ተቋም እና ከዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ የተገኙ የመረጃ ልውውጦች እንዲሁም ካምፑን የሚያሳዩ የሳተላይት ምሥሎችም በዘገባው ውስጥ ተካትተዋል።
የሮይተርስ ዘገባ እንደሚያመለክተው ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ከሱዳን ጦር ጋር እየተዋጋ ያለው አማጺ ኃይል ሥልጠና ይሰጥበታል የተባለው ካምፕ የሚገኘው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል "መንጌ" በተባለ ስፍራ ላይ ነው።
ካምፑ የሚገኝበት ስፍራ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳንን የሚያዋስን እንደሆነ እንዲሁም ከድንበር ያለው ርቀት 32 ኪሎ ሜትር እንደሆነም ዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
የሮይተርስ ዘገባ፤ "አንድ ከፍተኛ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣንን ጨምሮ ስምንት ምንጮች፤ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የሰፈሩን ግንባታ በገንዘብ እንደደገፈች፣ እንዲሁም ለቦታው የወታደራዊ አሠልጣኞችን እና የሎጅስቲክስ ድጋፍ ማቅረቧን ገልጸዋል" ይላል።
ቢቢሲ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሕዝብ ግንኙነት ክፍል በጉዳዩ ላይ ምላሽ ለማግኘት ጥያቄ ቢያቀርብም አስካሁን ምላሽ አላገኘም።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መንግሥት የቀረበበትን ክስ በማስተባበል ለቢቢሲ ምላሽ የሰጠ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ግን አስካሁን ያለው ነገር የለም።
ካለፈው ዓመት ሚያዝያ አንስቶ የደን ምንጠራ እንዲሁም የብረት ጣሪያ ያላቸው ሕንጻዎች መገንባታቸውን እንደተረዳ ዘገባው አመልክቷል። ጥቅምት ላይ ደግሞ ካምፑ ውስጥ ድንኳኖች መተከላቸው ተጠቅሷል።
ኅዳር ላይ የተነሱ የሳተላይት ምሥሎች ላይ 640 ድንኳኖች መመልከቱን የጠቀሰው ሮይተርስ፤ ካምፑ በአጠቃላይ 10,000 ተዋጊዎችን የመያዝ አቅም እንዳለው የሚያሳይ የዲፕሎማቲክ መልዕክት ልውውጥ መመልከቱን ገልጿል።
በርካታ ላንድ ክሩዘር እና ከባድ ተሽከርካሪዎች እንዲሁም የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል አሃዶች እንዲሁም የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አሠልጣኞች ጥር ላይ ወደ ካምፑ መግባታቸውንም ይህ ዲፕሎማሲያዊ መልዕክት ልውውጥ ጠቅሷል ተብሏል።
"ጥቅምት ላይ የኤምሬትሱ የሎጅስቲክስ ኩባንያ 'ጎሪካ ግሩፕ' አርማ ያለባቸው የጭነት መኪናዎች በአሶሳ ከተማ አድርገው ወደ ካምፑ ሲጓዙ መመልከታቸውን ሁለት ባለሥልጣናት ገልጸዋል" የሚለው ዘገባው ላይ ሰፍሯል።
ሮይተርስ "የተሽከርካሪዎቹ መጠን፣ ቅርጽ እና ዲዛይን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና አጋሮቹ ወታደሮችን ለማጓጓዝ ከሚጠቀሙባቸው ሞዴሎች ጋር ይመሳሰላሉ" ሲል ዘገባው ላይ ጽፏል። ይሁን እንጂ እነዚህ ተሽከርካሪዎች በአሶሳ በኩል ሲያልፉ የታዩት ስለመሆናቸው በገለልተኝነት አለማጣራቱን አስረድቷል።
"ከኢትዮጵያ የደኅንነት አገልግሎት" የውስጥ ማስታወሻ ተገኘ የተባለ መረጃ ደግሞ አስከ ጥር ወር መጀመሪያ ድረስ 4,300 የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ተዋጊዎች በስፍራው ወታደራዊ ሥልጠና እየወሰዱ እንደነበር አሳይቷል ተብሏል።
የተዋጊዎቹ "የሎጅስቲክስ እና የወታደራዊ አቅርቦት ትጥቅ የሚቀርበው በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ" እንደሆነ ከውስጥ ማስታወሻው መመልከቱን የዜና ወኪሉ አስታውቋል።
ሮይተርስ "[የሥልጠና] ካምፑን የማቋቋም ኃላፊነትን የወሰዱት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የመከላከያ ደኅንነት መምሪያ ዋና ኃላፊ የሆኑት ጄነራል ጌታቸው ጉዲና ናቸው" ሲል በዘገባው አስፍሯል።
አንድ የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን እንዲሁም አራት የዲፕሎማቲክ እና የደኅንነት ምንጮች ይህንኑ እንዳረጋገጡለትም የዜና ወኪሉ ገልጿል።
ሮይተርስ ከስድስት ባለሥልጣናት አገኘሁት ያለው መረጃ እንደሚያሳየው በካምፑ ውስጥ ከሚገኙት ምልምሎች ውስጥ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ናቸው። የደቡብ ሱዳን እና ሱዳን ዜጎችም ካምፑ ውስጥ ይገኛሉ ተብሏል።
ሱዳን ውስጥ የተወሰኑ ግዛቶችን የሚቆጣጠረው አማጺው 'SPLM-N' ተዋጊዎችም ካምፑ ውስጥ እንደሚገኙ ዘገባው ላይ ተጠቅሷል። ቡድኑ ግን ኃይሎቹ ኢትዮጵያ ውስጥ ይገኛሉ መባሉን አስተባብሏል።
እንደ ዜና ወኪሉ ዘገባ፤ ከካምፑ በ53 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው አሶሳ አየር ማረፊያም ካለፈው ነሐሴ ጀምሮ አዲስ ግንባታዎች እየተከወኑለት ነው።
በአየር ማረፊያው የሚደረገው ግንባታ ስፍራው የድሮን ማዘዣ ማዕከል እንዲኖረው የሚያደርግ መሆኑ ካደረገው የሳተላይም ምሥል ምርመራ እንዲሁም ከአንድ የመንግሥት ባለሥልጣን የተገኘ መረጃ መረዳቱን በዘገባው አካትቷል።
ሮይተርስ በምርመራው የደረሰባቸውን ግኝቶች በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንግሥት እና ከሱዳን ጦር ኃይሎች መረጃ ለማግኘት ያደረጋቸው ሙከራዎች እንዳልተሳኩ ገልጿል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ በሱዳን ጦርነት ውስጥ '"በማንኛውም መንገድ" ተሳትፎ እንደሌለው በመግለጽ ምላሽ እንደሰጠ ዘገባው ያመለክታል።
ቢቢሲ ይህንን ዘገባ በገለልተኛነት ለማረጋገጥ አልቻለም።