ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የጅምላ ግድያ እና ረሃብ የተንሰራፋባት የሱዳኗ ከተማ ኤል-ፋሸር
ከሱዳን ቁልፍ ከተሞች አንዷ የሆነችው ኤል-ፋሸር በፈጥኖ ደራሽ ኃይል ቁጥጥር ሥር መዋሏን ተከትሎ ነዋሪዎች ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ወድቀዋል።
በሱዳን ጦር ሥር የነበረችውን ከተማ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) ተቆጣጥሯል።
የተባበሩት መንግሥታት "የዘፈቀደ ግድያ" እየተፈጸመ መሆኑን ገልጿል። የዬል ዩኒቨርስቲ ሰብአዊ ጉዳዮች ጥናት ክፍል የሳተላይት ምሥል በመጠቀም ባደረገው ዳሰሳ "በዘፈቀደ የተገደሉ ሰዎች አስክሬን" መመልከቱን አስታውቋል።
ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ለ18 ወራት ኤል-ፋሸርን ከበባ ውስጥ መክተቱን ተከትሎ በከተማዋ ከዘፈቀደ ግድያ በተጨማሪ ረሃብም ተስፋፍቷል።
በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከከተማዋ መውጣት አልቻሉም።
አርኤስኤፍ ንጹኃንን መግደሉን እና አረብ ያልሆኑ ነዋሪዎችን ዒላማ ማድረጉን አስተባብሏል።
የመንግሥታቱ ድርጅት እና ሌሎችም የመብት ተሟጋቾች ማስረጃ በማቅረብ የጅምላ ግድያ ተፈጽሟል ብለዋል።
በዳርፉር ግዛት የምትገኘው ኤል-ፋሸር ከተማ በአርኤስኤፍ ሥር መውደቋ የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነትን አካሄድ ለውጧል።
በእርስ በርስ ጦርነቱ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ተገድለዋል። ወደ 12 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ተፈናቅለዋል።
በኤል-ፋሸር 130 ሺህ ሕጻናትን ጨምሮ 250 ሺህ ሰላማዊ ሰዎች ይኖራሉ። ከተማዋ ከበባ ውስጥ ከገባች ወዲህ ሰብአዊ እርዳታ እያገኙ አይደለም።
የሳተላይት ምሥሎት እንደሚያሳዩት በሆስፒታሎች ውስጥ የጅምላ ግድያ ተፈጽሟል። በከተማዋ ምሥራቃዊ ክፍል በኩል ለመውጣት ሲሞክሩ የነበሩ ነዋሪዎችም ተገድለዋል።
በከበባ ውስጥ ያለችው ከተማ
አርኤስኤፍ ኤል-ፋሸርን ሲቆጣጠር አንድ ነዋሪ "ምንም ምግብ የለንም፤ ወጥተን ምግብ መፈለግም አንችልም። አሁኑኑ እርዳታ ካልደረሰ የከተማው ሕዝብ አይተርፍም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ዩኒሴፍ እንዳለው ኤል-ፋሸር የሕጻናት ሰቆቃ፣ ሕመም፣ እንግልት እና ረሃብ ማዕከል ሆናለች። በየቀኑ ታዳጊዎች እንደሚሞቱም ገልጿል።
የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ካትሪን ረስል "አሰቃቂ ነገር እያየን ነው። የዩኒሴፍ ነፍስ አድን ምግብ ታግዶ የኤል-ፋሸር ሕጻናት እየተራቡ ነው" ብለዋል።
ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ አቢያንስ 600 ሺህ ሰዎች ከከተማዋ እና በአቅራቢያዋ ካሉ መጠለያዎች መፈናቀላቸውን ተቋሙ ገልጿል።
ከፍተኛ የምግብ እጥረት ከመከሰቱ ባሻገር የምግብ ዋጋ እጅጉን ንሯል።
ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅቶች "በታቀደበት ሁኔታ ረሃብ የጦር መሣሪያ" መደረጉን ኮንነዋል።
በቆሎ እና ማሽላ ዋጋቸው ከ300 ሺህ እስከ 350 ሺህ የሱዳን ፓውንድ ይገመታል። ሥጋ ማግኘትም "ቅንጦት" ሆኗል ሲሉ የሕክምና ባለሙያ ይናገራሉ።
"መድኃኒትም ማግኘት አንችልም። ቁስል መጠቅለያ ፋሻ ስለሌለ ትንኝ መከላከያ አጎበር እየተጠቀምን ነው" ሲሉም አክለዋል።
ሱዳን ከአውሮፓውያኑ 2024 ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ የኮሌራ ወረርሽኝ ገጥሟታል። ዩኒሴፍ እንዳለው ወደ 96 ሺህ ሰዎች በወረርሽኙ ሲያዙ 2,400 ሰዎች ሞተዋል።
ኤል-ፋሸርን ለመቆጣጠር የተደረገው ውጊያ
የእርስ በርስ ጦርነቱ ከሁለት ዓመት በፊት ከተቀሰቀሰ ወዲህ ሁለቱ ተገዳዳሪ ኃይሎች ከተማዋን ለመቆጣጠር ተዋግተዋል።
የሱዳን ጦር መሪ ጄነራል አብደል ፋታሕ አል-ቡርሐን አብዛኞውን ሰሜናዊ የሱዳን ክፍል ይቆጣጠራሉ።
ከካርቱም ወጥተው ፖርት ሱዳንን እንደ ዋና መቀመጫ እየተጠቀሙ ይገኛሉ። መንግሥታቸውንም የተበባሩት መንግሥታት ዕውቅና ይሰጠዋል።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪ ጄነራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ (ሔሜቲ) አብዛኛውን የዳርፉር ግዛት እና ኮርዶፋን ከተማን ጨምሮ ምዕራቡን የሱዳን ክፍል ይቆጣጠራሉ።
ሱዳናዊው የፖለቲካ ተንታኝ ዳሊላ አብደልሞኒም እንደሚሉት፤ ኤል-ፋሸር በሱዳን ጦር ሥር የነበረች የመጨረሻዋ የዳርፉር ከተማ ነበረች።
"ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ (አርኤስኤፍ) ለመገንጠል ወይም ነጻ ግዛት ለማድረግ ሊሞክር ይችላል" ይላሉ።
የጎሳ ግጭቶች
ለዓመታት በኤል-ፋሸር የጎሳ ግጭቶች ተነስተዋል።
በዳርፉር ግዛት ፉር፣ ዛግዋ እና ማሳሊትን ጨምሮ ሌሎችም ጎሳዎች ይኖራሉ። አረብ ያልሆኑ ዜጎችን ያገላል የሚሉትን የሱዳን መንግሥት ፖሊሲ ይቃወማሉ።
በአውሮፓውያን 2003 በነበረው የጎሳ ውጥረት ምክንያት መንግሥት አፍሪካውያን የአካባቢው ነዋሪዎችን ዒላማ ያደረገ ጥቃት ሰንዝሯል።
የሱዳን መሪዎች እና በሱዳን መንግሥት የሚደገፈው ጃንጃዊድ የአረብ ታጣቂ ቡድን የዘር ማጽዳት፣ ስቅይት እና የጦር ወንጀሎች መፈጸሙን ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት በይኗል።
በአስር ዓመት በፊት ደግሞ ጃንጃዊድ ሚሊሻ ራሱን ለውጦ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ሆኗል። አሁን ዳርፉርን ለመቆጣጠር እየተንቀሳቀሰ ነው።
የፖለቲካ ተንታኙ "አብዛኞቹ የኤል-ፋሸር ነዋሪዎች አፍሪካውያን ናቸው። የአርኤስኤፍ ኃይሎች በአብዛኛው አረቦች ናቸው። የከፋ ጥቃት ሊፈጽሙ ይችላሉ። ታሪክ የሚያሳየንም ጥቃት ለማድረስ እንደማይፈሩ ነው" ይላሉ።
ሁለቱም ተገዳዳሪ ኃይሎች የሰብአዊ መብት ጥሰት በመፈጸም ተከሰዋል።
ከቻድ ጋር ባለው ድንበር አቅራቢያ የሚገኝ የሱዳን ተፈናቃዮች መጠለያን በ2025 የጎበኙት የቀድሞው የዩናይትድ ኪንግደም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚይ "በሕይወቴ ከሰማኋቸው እና ካየኋቸው አሰቃቂ ነገሮች የከፋውን አይቻለሁ" ብለዋል።
"ሴቶች እና ሕጻናት ሕይወታቸውን ለማትረፍ ይሸሻሉ። ለግድያ፣ ለምግብ እጥረት እና ለወሲባዊ ጥቃት ተጋልጠዋል። የተስፋፋውን ረሃብ መመልከትም ያስከፋል" በማለትም ተናግረዋል።
ወርቅ እና ጦርነት
ተንታኞች እንደሚሉት ዋነኛው የግጭቱ ገፊ ምክንያት የሱዳን የወርቅ ሀብት ነው።
ኤል-ፋሸን ለመያዝ የሚደረገው ውጊያም ማዕድናትን ከመቆጣጠር ጋር ይገናኛል።
የቢቢሲ ጋዜጠኛ ሞሐናድ ሐሺም "በዳርፉር ከፍተኛ የማዕድን ክምችት አለ። ነዳጅ፣ ዩራኒየም እና የከርሰ ምድር ውሃ ቢኖርም ዋነኛው የግጭቱ ዘዋሪ ግን ወርቅ ነው" ይላል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የባለሙያዎች ቡድን ባወጣው ሪፖርት "ለውጊያው ገንዘብ የሚገኘው በዋነኛነት ከወርቅ ነው" ብሏል።
በሰሜናዊ ዳርፉር በኩል ወደ ሊቢያ እና ቻድ መሻገር ይቻላል። ወርቅ ለመሸጥም ይሄ መንገድ ሁነኛ አማራጭ ነው። መሣሪያ በማስገባት ውጊያውን ለመቀጠልም ይውላል።
የአሜሪካ የግምጃ ቤት መረጃ እንደሚያሳየው፤ ሔሜቲ ካለፈው ጥር አንስቶ የዳርፉርን የወርቅ ንግድ ይቆጣጠራሉ።
ሔሜቲ የዘር ጭፍጨፋ ፈጽመዋል በሚል የከሰሰው የአሜሪካ መንግሥት ዕግድ ጥሎባቸዋል።
የሱዳን ጦር ያለፈው መጋቢት ላይ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስን "በምዕራብ ዳርፉር የዘር ጭፍጨፋ እንዲፈጸም ለአርኤስኤፍ የገንዘብ እና ወታደራዊ ድጋፍ በመስጠት" በዓለም አቀፉ የፍትሕ ፍርድ ቤት ከሷል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ "ትኩረት ለማግኘት የተሰነዘረ ነው" በማለት የሱዳንን ክስ አስተባብላለች። በዓለም አቀፉ የፍትሕ ፍርድ ቤት የቀረበው ክስ ውድቅ እንደሚደረግም አገሪቱ አስታውቃለች።
ሱዳን ላይ የተጣለውን የጦር መሣሪያ ማዕቀብ የሚከታተለው የመንግሥታቱ ድርጅት የባለሙያዎች ቡድን እንደሚለው፤ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ለፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በቻድ በኩል የጦር መሣሪያ እያስገባች ነው የሚለው ክስ ተዓማኒ ነው።