የሱዳን ጦር ነዋሪዎችን እስከሞት ድረስ እያሰቃየ መሆኑን አንድ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድን አስታወቀ

'ዘ ኢመርጀንሲ ሎውየርስ' የተባለ ታዋቂ የሱዳን የሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድን፤ የሀገሪቱ ጦር እና የፀጥታ ኃይሎች ነዋሪዎችን እስከ ሞት ድረስ እያሰቃዩ እና "የግድያ ክፍሎችን" እያንቀሳቀሱ ነው ሲል ወነጀለ።

ተሟጋች ቡድኑ በዋና ከተማዋ ካርቱም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መታሰራቸውን ገልጿል። "ሁኔታው በጣም በከፋባቸው" አጋጣሚዎችም አንዳንድ ታሳሪዎች ስቅይት እንደተፈጸመባቸው በሚያስረዳ መልክ ሞተው እንደተገኙ አስታውቋል።

የሱዳን ጦር መጋቢት ላይ ከተማዋን ከፈጥኖ ደራሽ ኃይል እጅ በማውጣት መልሶ ይዟል። ሁለቱ ተዋጊዎች እያካሄዱት ባለው ሁለት ዓመት የደፈነ የእርስ በእስር ጦርነት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ተገድለዋል።

የሱዳን ጦር የቀረበበትን ውንጀላ በተመለከተ አስተያየት እንዲሰጥ ቢቢሲ ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።

ተሟጋቹ የጠበቆች ቡድን ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በሱዳን ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የተፈጸሙ አሰቃቂ ድርጊቶችን ሲሰንድ ቆይቷል።

'ዘ ኢመርሰንጂ ሎውየርስ' በኤክስ ገጹ ባወጣው መግለቻ የሚፈጸሙ "ጥሰቶች ላይ አደገኛ ጭማሪ" እንደተስተዋለ ገልጿል።

አንዳንድ እስረኞች በዘፈቀደ ተይዘው ወደ ትላልቅ ማቆያ ማዕከላት መወሰዳቸውንም ቡድኑ ተናግሯል።

"[የታሳሪዎቹ እጣ ፈንታ፤ ኢሰብአዊ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ መቆየት፣ በጣም መሰረታዊ የፍትህ መስፈርቶች በማያሟሉ እና በፀጥታ ኤጀንሲዎች በሚካሄዱ የፍርድ ሂደቶች ማለፍ ወይም በመጥፎ ጤና ሁኔታ ውስጥ መለቀቅ ነው" ሲል በመግለጫው አስፍሯል።

"በጣም በከፋ ሁኔታ፤ አንዳንዶች ከተገደሉ በኋላ ወይም በስቃይ ምክንያት ሞተዋል ከተባለ በኋላ ተገኝተዋል" ሲልም አክሏል።

በዜጎች ላይ ስቅይትን መፈጸም በቀድሞው የሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽር የጭቆና አገዛዝ ወቅትም የተለመደ ነበር።

የአሁኑ ጦርነት ከተጀመረ አንስቶም ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እስረኞች ላይ በደል ሲፈጽም እና ሲገድል ተስተውሏል።

የተባበሩት መንግስታት ለሱዳን ያቋቋመው ገለልተኛ ዓለም አቀፍ የእውነት ፍለጋ ተልዕኮ መጋቢት ላይ እንዳስታወቀው፤ ሁለቱም ወገኖች "የዘፈቀደ እስር እንዲሁም በታሳሪዎች ላይ ስቅይት እና በደል በስፋት እንደሚፈጽሙ" አስታውቆ ነበር።

ተልዕኮው፤ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እና የሀገሪቱ ጦር "መድፈር እና ሌሎች የወሲብ ጥቃቶችን፣ የዘፈቀደ እስር እና ማጎርን እንዲሁም ስቅይት እና እንግልትን" ተጠቅመዋል ሲልም ከስሷል።

በዓለም ላይ እጅግ የከፋውን የሰብአዊ ቀውስ ያስከተው የሱዳን የእስር በእስር ጦርነት፤ 12 ሚሊዮን ሰዎች ከቤታቸው እንዲፈናቀሉ እና በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች ርሃብ እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል።

ባለፈው ሳምንት ድንበር የለሽ የሀኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) የተባለው የህክምና በጎ አድራጎት ድርጅት፤ ጦርነቱ ሀገሪቱ ለዓመታት አይታው በማታውቀው መልኩ የከፋ የኮሌራ ወረርሽኝ እንዲከሰት ማድረጉን ገልጿል።

ባለፈው ዓመት ብቻ 100,000 ገደማ ሰዎች በበሽታው የተያዙ ሲሆን 2,470 ሰዎች ደግሞ ህይወታቸው አልፏል።