ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
'ልጆቻችን እየሞቱ ነው'- ረሃብ፣ በሽታ፣ ፍልሚያ እና ከበባ የፈተናቸው ሱዳናውያን
በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ተከበበችው የሱዳኗ አል ፋሸር ከተማ በጋራ ምግብ ማብሰያ ቤት የሚታዩት ሴቶች በተስፋ መቁረጥ ተቀምጠዋል።
"ዓይናችን እያየ ልጆቻችን እየሞቱ ነው" ስትል ከሴቶቹ አንዷ ለቢቢሲ ትናገራለች።
"ምን ማደረግ እንዳለብን አናውቅም። ንፁኃን ናቸው። ከጦሩ ጋርም ወይም [ከተቀናቃኙ] ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ጋር ምንም የሚያገናኛቸው ነገር የለም። ስቃያችን ከምታስቡት በላይ የከፋ ነው"።
በአል ፋሸር የምግብ እጥረት ያለ ሲሆን የምግብ ዋጋ በማሻቀብ የአንድ ሳምንት አስቤዛ ይሸፍን የነበረ ገንዘብ አሁን የአንድ ቀን ምግብን ብቻ ይሸምታል።
ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶች "የተሰላ ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ ደርጎ መጠቀምን" አውግዘውታል።
ቢቢሲ በከተማው ታጉረው የሚኖሩ ሰዎችን የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በአካባቢው ከሚገኝ የመብት ተሟጋች ቡድን ተልኮለታል።
የሱዳን የጦር አዛዦች በጋራ መፈንቅለ መንግሥት አድርገው ግንኙነታቸው ከሻከረ በኋላ የሱዳን ጦር ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ጋር ከሁለት ዓመት በላይ እየተዋጋ ይገኛል።
በምዕራብ ዳርፉር ክልል የምትገኘው ኤል ፋሸር በጦርነቱ ክፉኛ ከተጎዱ ከተሞች መካከል ናት።
የረሃቡ ቀውስ በግጭቱ የተፈናቀሉ ሰዎችን ባስጠለሉ ጣቢያዎች እየጨመረ ባለው የኮሌራ በሽታ ጭምር የታገዘ ሲሆን፤ ግጭቱ በዚህ ሳምንት ተፋፍሞ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እስካሁን ካደረጋቸው ከባድ የተባለውን ጥቃት በከተማዋ ላይ ፈፅሟል።
ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ዋና ከተማዋ ካርቱም ከእጁ መውጣቷን ተከትሎ ለ14 ወራት ከብቦ ወደያዛት አል ፋሸር ከተማ እየተጠጋ ሲሆን፤ የመጨረሻዋን የዳርፉር ቁልፍ ከተማ ለመያዝ እየተፋለመ ነው።
ጦሩ ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ግዛቶችን ለማስመለስ እየተፋለመ ባለበት በሰሜን እና ማዕከላዊ የአገሪቱ ክልሎች የምግብ እና የመድኃኒት እጥረት በንፁኃን ሰዎች ስቃይ ላይ ተጨማሪ ፈተና ደቅኗል።
ይሁን እንጂ ሁኔታው የጦርነት ቀጠና በሆኑት ምዕራብ እና ደቡባዊ ሱዳን ክፍሎች የባሰ ነው።
በአል ፋሸር በሚገኘው ማትባክ አል ካሂር የጋራ ምግብ ማብሰያ የለውዝ ፍሬ ዘይቱ ከወጣ በኋላ ለእንስሳት ከሚሰጠው ተረፈ ምርት ገንፎ እየሰሩ ነው።
በአካባቢው አልፎ አልፎ ማሽላ ማግኘት የሚቻል ቢሆንም፤ ቢቢሲ የደረሰው ተንቀሳቃሽ ምስል ሲቀረፅ የምግብ ማብሰያው ኃላፊ " ምንም ዱቄት ወይም ዳቦ የለም" ሲሉ ይደመጣሉ።
"አሁን ተረፈ ምርት መብላት ላይ ደርሰናል። ፈጣሪ ከዚህ ጥፋት ያውጣን። በገበያ ውስጥ የሚገዛ ምንም ነገር የለም" ብለዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት ወደ ከተማው እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች እንዲገቡ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ደጋግሞ ሲወተውት የቆየ ሲሆን፤ በዚህ ሳምንትም ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች በዓለም አቀፍ ሕግ ያለባቸውን ግዴታ እንዲያከብሩ ጠይቋል።
የሱዳን ጦር ተሽከርካሪዎቹ እንዲገቡ የፈቀደ ቢሆንም፤ የመንግሥታቱ ድርጅት ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ይፋዊ ፈቃድ እየጠበቀ ነው።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አማካሪዎች የተኩስ አቁም ስምምነቱ በአል ፋሸር ከተማ ውስጥ "ተከብቦ ለሚገኘው ጦሩ" ምግብ እና ተተኳሽ ለማቅረብ ጥቅም ላይ ይውላል የሚል ስጋት አንፀባርቀዋል።
አማካሪዎቹ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እና አጋሮቹ ንፁሃን ሰዎች ከተማዋን ለቅቀው እንዲወጡ "የደኅንነት መንገዶችን" እያመቻቹ መሆኑንም ተናግረዋል።
ምላሽ ሰጪ ባለሙያዎች የአደጋ ጊዜ ገንዘብ በዲጂታል የባንክ ስርዓት እየተላከላቸው ቢሆንም፤ ያን ያህል ጠብ የሚል አይደለም።
የኖርዌይ ስደተኞች ካውንስል የአድቮኬሲ ኃላፊ የሆኑት መቲልድ ቩ "በገበያዎች ዋጋው ሰማይ ነክቷል" ይላሉ።
"ዛሬ 5,000 ዶላር ለ1,500 ሰዎች የአንድ ቀን ምግብ ነው የሚሸፍነው። ከሦስት ወራት በፊት ገንዘቡ አንድ ሳምንት ሙሉ ይመግባቸው ነበር"።
ሐኪሞች ሰዎች በምግብ እጥረት እየሞቱ ነው ይላሉ። ምን ያህል ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል የሚለውን ማወቅ ከባድ ቢሆንም የክልል ጤና ባለሥልጣናትን ዋቢ ያደረገ አንድ ሪፖርት ባለፈው ሳምንት ከ60 በላይ ሰዎች ሞተዋል ብሏል።
ሆስፒታሎች ከአቅማቸው በላይ ሆኗል። ጥቂቶች እስካሁን አገልግሎት እየሰጡ ነው። በመሳሪያ ድብደባዎች የተጎዱ እና በገጠማቸው የሕክምና ግብዓት እጥረት በረሃብ የተጎዱትንም ሆነ በቀጠለው ድብደባ የሚቆስሉ ሰዎችን ለመርዳት ተቸግረዋል።
በአል ሳዑዲ ሆስፒታል የሕጻናት ሐኪም የሀኑት ዶ/ር ኢብራሂም አብደላህ ካተር "ሆስፒታል የገቡ በምግብ እጥረት የተጎዱ በጣም ብዙ ሕፃናት አሉ። ነገር ግን ምንም አጋዥ አልሚ ምግብ የለንም" ይላሉ።
በሆስፒታሉ በአሁኑ ሰዓት በሕክምና ላይ ያሉ በከፍተኛ የምግብ እጥረት የተጎዱ ሕፃናት ውስብስብ ሕመም ገጥሟቸዋል
"ሞታቸውን እየተጠባበቁ ነው" ይላሉ ዶ/ር ኢብራሂም።
የረሃብ ቀውስ ሲከሰት ተጋላጭ የሆኑ፣ ጤናማ ያልሆኑ እና የቆየ ሕመም ያለባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች መጀመሪያ ይሞታሉ።
"ሁኔታው አሳዛኝ ነው፤ በጣም አስከፊ ነው" ሲሉ ሐኪሙ በድምፅ መልዕክት ተናግረዋል።
"የአል ፋሸር ሕፃናት በምግብ እጥረት፤ በመድኃኒት እጥረት ምክንያት በየቀኑ እየሞቱ ነው። በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ቆሞ እያየ ነው"።
በሱዳን የሚገኙ ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በዚህ ሳምንት ባወጡት አስቸኳይ መግለጫ "የቀጠሉ ጥቃቶች፣ እርዳትን ማስተጓጎል እና ቁልፍ መሠረተ ልማቶች ላይ ማነጣጠር ንፁኃን ሕዝብን ረሃብ፣ ፍርሃት እና መሰላቸት እንዲሰማው ለማድረግ ሆን ተብሎ የሚፈፀም ስልትን ያሳያል" ብለዋል።
ድርጅቶቹ አክለውም ለወታደራዊ ኃይሎች ጥቅም ለማዋል ምግብ ማከማቸት የሕዝቡን ስቃይ ማራዘሚያ ነው ብለዋል።
"ከከተማዋ የሚያስወጣ ደኅንነት ያለው መንገድ የለም። መንገዶች ተዘግተዋል፤ ለቅቀው ለመውጣት የሚሞክሩ ሰዎች ጥቃት፣ የኬላ ክፍያ፣ ማኅበረሰባዊ አድልዎ እና ሞት ይገጥማቸዋል" ሲሉም ድርጅቶቹ አስታውቀዋል።
ባለፉት ወራት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በሚያዚያ ወር በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከተያዘው በአል ፋሸር አቅራቢያ ከሚገኘው የዛምዛም የተፈናቃዮች ጣቢያ ለቀው ወጥተዋል።
ተፈናቃዮቹ በመንገዳቸው በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አጋር ቡድኖች ጥቃት እና ዝርፊያ ከተፈፀመባቸው በኋላ ከአል ፋሸር በ60 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ታዊላ ከተማ የደረሱት ተዳክመው እና በውሃ ጥም ተሰቃይተው ነበር።
ሕይወት በሰዎች በተጨናነቁ መጠለያ ጣቢያዎች የተሻለ ደኅንነት አላት። ነገር ግን በአብዛኛው እንደ ኮሌራ ያሉ ገዳይ በሽታዎች አላስኖር ብሏቸዋል።
በሽታው በተበከለ ውሃ የሚከሰት ሲሆን በውሃ ማጣሪያ መሰረተ ልማቶች ውድመት እና በምግብ እና መድኃኒት እጥረት፤ በዝናባማ ወራት ደግሞ በጎርፍ ምክንያት በሱዳን በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሕልፈት ምክንያት ሆኗል።
ከአል ፋሸር በተለየ በታዊላ የረድኤት ድርጅቶች አሉ። ነገር ግን የግብዓት እጥረት አለባቸው ይላሉ ጆን ጆሴፍ የተባሉ የአንድ የጣቢያ አስተባባሪ።
የድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን ሠራተኛ የሆኑት ስልቪያን ፔንቹያድ በመጠለያ ጣቢያዎች ለአንድ ሰው በቀን ሦስት ሊትር የሚጠጋ ውሃ ብቻ እንዳለ ገልፀው፤ ይህም "ከሚያስፈልገው መሠረታዊ ፍላጎት በጣም ያነሰ ነው፤ ሰዎች ከተበከሉ ስፍራዎች ውሃ እንዲጠቀሙ ያስገድዳል" ብለዋል።
ዙቤይዳ ኢስማኤል በድንኳን በተሰራው ክሊኒክ ተኝታለች። የሰባት ወር ነፍሰ ጡር ናት፤ በድካም እያቃሰተች ነው። ታሪኳ በብዙዎች የሚነገረው የሰቆቃ ታሪክ ነው።
አል ሻፈርን ሸሽታ ከመውጣቷ በፊት በነበራት ትንሽ ገንዘብ ትነግድ እንደነበር ትናገራለች።
ባለቤቷ ወደ ታዊላ ከተማ በሚወስደው መንገድ በታጣቂዎች ተይዟል። ሴት ልጇ ጭንቅላቷ ላይ ተጎድታለች።
ዙቤይዳ እና እናቷ መጠለያ ጣቢያው በደረሱ በአጭር ጊዜ ውስጥ በኮሌራ ተይዘዋል።
"ውሃ ሳናፈላ ጠጣን። ውሃ የሚሰጠን ማንም የለም። እዚህ ከመጣሁ በኋላ ምንም የቀረኝ ነገር የለም" ትላለች።
በአል ፋሸር በጋራ ማብሰያ ክፍሉ የተከማቹ ሴቶች እርዳታ እንዲደረግላቸው ይማፀናሉ።
"በጣም ደክሞናል። ከበባው እንዲከፈትልን እንፈልጋለን" ትላለች ፋይዛ አብካር ሞሐመድ።
"ከአየር ምግብ ቢወረውሩልን እንኳ ሙሉ ለሙሉ ተዳክመናል።"