ኔታንያሁ በጋዛ ጦርነት ምክንያት በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ጥያቄ መቅረቡን አጥብቀው ተቃወሙ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እሳቸውን ጨምሮ የሐማስ መሪዎች በጋዛ ግጭት ፈጽመዋል በተባለው ወንጀል ምክንያት የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) የእስር ትዕዛዝ እንዲወጣባቸው መጠየቁን በቁጣ አውግዘዋል።
ኔታንያሁ “ዲሞክራሲያዊት እስራኤል” “ከጅምላ ገዳዮች” ካሏቸው ጋር እኩል መፈረጇን በመጸየፍ እንደማይቀበሉትም ገልጸዋል።
የኔታንያሁን አስተያየት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተጋብተውታል። በእስራኤል እና በሃማስ መካከል ምንም ዓይነት ተመሳሳይነት የለም ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ኔታንያሁ እና የመከላከያ ሚኒስትሩ ዮአቭ ጋላንት በጋዛ ለተፈጸሙ የጦር እና በሰው ልጆች ላይ ለተፈጸሙ ወንጀሎች ተጠያቂ ናቸው ብሎ ለማመን የሚበቁ ምክንያቶች አሉ ሲሉ የአይሲሲ ዋና ዓቃቤ ህግ ካሪም ኻን ገልጸዋል።
በጋዛ የሚገኘውን ሐማስን የሚመሩት ያህያ ሲንዋር ላይም ተቋሙ በጦር ወንጀለኞች ምክንያት የእስር ማዘዣ እንዲወጣባቸው ጠይቋል።
እስራኤል እና ዋነኛ አጋሯ ዩናይትድ ስቴትስ እአአ በ2002 የተቋቋመው የአይሲሲ አባል አገራት አይደሉም።

የፎቶው ባለመብት, EPA-EFE/REX/Shutterstock
በእስራኤል እና በሐማስ መሪዎች ላይ የተሰነዘረው ውንጀላ መስከረም 26 የሐማስ ታጣቂዎች በእስራኤል ላይ ጥቃት ሰንዝረው ወደ አንድ ሺህ 200 የሚጠጉ ሰዎችን ገድለው 252 ሰዎችን አግተው ወደ ጋዛ ከወሰዱበት ክስተት ጋር የተያያዘ ነው።
ጥቃቱን ተከትሎ እስራኤል በወሰደችው የአጸፋ ምላሽ በጋዛ ቢያንስ 35 ሺህ 500 ፍልስጤማውያን መሞታቸውን በሐማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ባይደን ሰኞ ዕለት “በእስራኤል እና በሐማስ መካከል አንዳች እኩልነት የለም፤ ምንም” ብለዋል።
ባይደን “እስራኤል ሲቪሎችን ለመታደግ የምትችለውን ሁሉ ማድረግ እንደምትፈልግ ግልጽ ነው” ሲሉ አክለዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከንም የፕሬዚዳንቱን ውግዘት “ዋሽንግተን እርምጃውን በመሠረታዊነት አትቀበልም” ሲሉ አስተጋብተዋል። "አሳፋሪ ነው። [አይሲሲ] በዚህ ጉዳይ ላይ ስልጣን የለውም" ብለዋል።
የእስር ማዘዣ ጥያቄው የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ እየተደረገ ያለውን ጥረት አደጋ ላይ ይጥላል ሲሉም ብሊንከን ጠቁመዋል።
ጋላንት እና የሐማስ የፖለቲካ መሪ ኢስማኤል ሃኒያህ ከቡድኑ ወታደራዊ ኃላፊ መሐመድ ዲፍ ጋር የእስር ማዘዣ እንዲወጣባቸው ኻን ጠይቀዋል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የመከላከያ ሚኒስትር በጦርነት፣ በግድያ፣ በሲቪል ህዝብ ላይ ሆን ተብሎ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በመምራት እና በመግደል እና በሲቪሎች ላይ በሚደርስ ርሃብ በተፈጸሙ ወንጀሎች ተጠርጥረዋል ብለዋል።
አቃቤ ሕጉ እንዳሉት የተጠረጠሩባቸው ወንጀሎች የተጀመሩት ለሐማስ መሪዎች እስራኤል ላይ ጥቃት ከተፈጸመበት “ቢያንስ ከመስከረም 26 ጀምሮ” ሲሆን ለእስራኤል መሪዎች ደግሞ “ቢያንስ ከመስከረም 27 ጀምሮ” ነው።
“ከፍተኛ ጥረት ቢደረግም” ስለወንጀሎቹም ሆነ በምርመራ ላይ ያሉ ግለሰቦችን ጉዳይ ለማየት በአገር ውስጥ [በእስራኤል] የተወሰደ እውነተኛ እርምጃ ስለመኖሩ ምንም አይነት መረጃ አላገኘም ሲል አይሲሲ ሰኞ ዕለት ውሳኔውን ተከላክሏል።
የአይሲሲ ዳኞች የእስር ትዕዛዙን በማውጣት ላይ ውሳኔ ይሰጡበታል። ትዕዛዙ ከወጣ የአይሲሲ አባል አገራት ሰዎቹን የማግኘት ዕድል ካላቸው በቁጥጥር ስር ያውሏቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ለረዥም ጊዜ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን በማገልገል ላይ የሚገኙት ኔታንያሁ የእስር ትዕዛዝ እንዲወጣባቸው መጠየቁን “የማይረባ እና የውሸት ትዕዛዝ” ሲሉ አውግዘውታል።
በዕብራይስጥ ቋንቋ በተላለፈ መግለጫቸው ፍርድ ቤቱ ሐማስን እና እስራኤልን “በምን ድፍረት ለማወዳደር ቻለ” ሲሉ ጠይቀዋል።
ንጽጽሩ “እውነታን ማዛባት” ነበር ሲሉ ኔታንያሁ አክለዋል።
"በአለም ላይ እየተቀጣጠለ ባለው ጸረ-ሴማዊነት እሳት ላይ ቤንዚን ማርከፍከፍ" ሲሉ ዓቃቤ ህጉንም ከሰዋል።
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እስራኤል ካትስ በበኩላቸው ኻን የወሰዱትን እርምጃ በመስከረም 26 ሰለባዎችን “ማጥቃት” እና “ለዘላለም የሚታወስ ታሪካዊ ውርደት” ሲሉ ጠርተውታል።
አንዳንድ የእስራኤል አጋሮች ባወጡት በመግለጫ አይሲሲን በቀጥታ ከመተቸት ተቆጥበዋል።
የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ ፍርድ ቤቱን እና “በሁሉም ሁኔታዎች ውስጥ ያለቅጣትን መከላከል” ሲል የጠራውን ውሳኔ እንደሚደግፍ ተናግሯል።
የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም የአይሲሲን ነፃነት እና አሠራር እንደሚያከብር ተናግሯል።
በእስራኤል እና በሐማስ መሪዎች ላይ የተሰነዘሩ ክሶች በአንድ ጊዜ መውጣታቸው እርምጃ "ትክክለኛ ያልሆነ የተመሳሳይነት ስሜት ፈጥሯል" በማለት አስታውቋል።
“በፍልስጤም ተቃውሞ መሪዎች ላይ የወጡት የእስር ማዘዣዎች በሙሉ እንዲሰረዙ” ሐማስ የራሱን ጥያቄ አቅርቧል።
"የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አቃቤ ህግ ተጎጂውን ከገዳዩ ጋር ለማመሳሰል ያደረገውን ሙከራ ሐማስ አጥብቆ ያወግዛል" ሲል ቡድኑ አስታውቋል።
በኔታንያሁ እና ጋላንት ላይ እስር ትዕዛዝ እንዲወጣ የቀረበው ጥያቄ “ሰባት ወር” ዘግይቶ በመቅረቡ ቅሬታው አቅርቧል። ሌሎች የእስራኤል የፖለቲካ እና ወታደራዊ መሪዎችም አብረው ሊካተቱ ይገባ ነበር ሲል አክሏል።
የሐማስ መሪዎችን ማጥፋት፣ ግድያ፣ ማገት፣ አስገድዶ መድፈር እና ወሲባዊ ጥቃት እና ማሰቃየትን ጨምሮ ሌሎች ወንጀሎችን ፈጽመዋል ሲሉ ኻን ከሰዋል።












