ደቡብ ኮሪያ፤ ኪም ጆንግ ኡንን "ታላቁ መሪያችን" እያለ የሚያንቆለጳጵሰው ሙዚቃ እንዲታገድ ወሰነች

ኪም ጆንግ ኡን፤ ባለቤታቸው [ግራ] እና ሴት ልጃቸው [መሐል]

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ኪም ጆንግ ኡን፤ ባለቤታቸው [ግራ] እና ሴት ልጃቸው [መሐል]

ደቡብ ኮሪያ የጎረቤቷ ሰሜን ኮሪያ መሪ የሆኑት ኪም ጆንግ ኡን "ቅን አባት" እና "ታላቅ መሪ" ናቸው እያለ የሚያንቆለጳጵሰው ታዋቂ ሙዚቃ እንዲታገድ አዘዘች።

የሴኡል የሚድያ ተቆጣጣሪዎች ይህ የሙዚቃ ቪድዮ የብሔራዊ ደኅንነት ሕጉን የሚጥስ ነው ብለዋል።

ባለፈው ሚያዚያ የተለቀቀው ሙዚቃ በተለይ በቲክቶክ ተጠቃሚዎች ዘንድ እጅግ ተወዳጅ እየሆነ መጥቷል።

"ሙዚቃው ኪም ጆን ኡንን ያንቆለጳጵሳል፤ ከሌሎች በላይ አድርጎ ይስላል" ይላል የደቡብ ኮሪያ ሚድያ ስታንዳርድ ኮሚሽን ሰኞ ያወጣው መግለጫ።

የደቡብ ኮሪያ የብሔራዊ ደኅንነት ሕግ የሰሜን ኮሪያ መንግሥት ድረ-ገፆችን የሚያግድ፣ መገናኛ ብዙኃን እንዳይሰራጩ የሚያደርግና ለኪም ጆንግ ኡን አገዛዝ የሚያደሉ ድርጊቶችን የሚቀጣ ነው።

'ፍሬንድሊ ፋዘር' የተሰኘው ሙዚቃ ሀያ ዘጠኝ ዓይነት ቪድዮ የተሠራለት ሲሆን ሁሉም እንደሚታገዱ የገለጠው ኮሚሽኑ እንዴት የሚለውን ግን ግልጥ አላደረገም።

ሙዚቃው በደቡብ ኮሪያ እንዲታገድ የሆነው ብሔራዊው የደኅንነት አገልግሎት ባቀረበው ጥሪ መሠረት መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጧል።

"ቪድዮው እንደተለመደው ከደቡብ ኮሪያ ጋር ያለውን ሳይኮሎጂካል ጦርነት የሚገልጥ ነው። የተለጠፈውም ቢሆን በውጭ ኃይል ነው። ዋና ዓላማው ደግሞ ኪምን ማንቆለጳጰስ ነው" ይላል ተቆጣጣሪው ድርጅት።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ነገር ግን በርካታ ደቡብ ኮሪያዊያን የሙዚቃ ቪድዮው በሀገራቸው መታገዱን ከሰሙ በኋላ ስለሙዚቃው ማወቃቸውን ማሕበራዊ ሚድያ ላይ በሚሰጡት አስተያየት ይፋ አድርገዋል።

አንዳንዶች ደግሞ የደቡብ ኮሪያ ባለሥልጣናት ቪድዮውን እንዳያግዱት ጠይቀው "ይህንን ቀልድ ሁላችንም ልናጣጥመው ይገባል" ይላሉ።

ላለፉት 50 የፒዮንግያን የፕሮፖጋንድ ማሽን ስለመሪዎቹ የተለያዩ ዓይነት ሙዚቃዎችን የሚለቅ የነበረ ሲሆን ይህ የፖፕ ሙዚቃ ዘውግ ቅርፅ ያለው ዘፈን ግን ተወዳጅ ሆኗል።

መካከለኛ ፍጥነት ያለውና ጥዑም ዜማ የተላበሰው ሙዚቃ ኪም ጆንግ ኡን "አባት" እና "ታላቅ" ሲል ይገልጣቸዋል። እኒህ ቃላት የሰሜን ኮሪያ የመጀመሪያው መሪ ለነበሩት የኡን አያት ኪም ኢል ሱንግን ለማንቆለጳጰስ ጥቅም ላይ ይውሉ ነበር።

"ኪም ጆንግ ኡን ታላቁ መሪ እያልን አንድ ላይ እንዘምር፤

ስለ ኪም ጆንግ ኡን ደረታችንን ነፍተን እንናገር፤

ቅኑ አባታችን፤"

አንዳንድ የቲክቶክ ተጠቃሚዎች ሙዚቃው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ አሊያም ቤት ውስጥ አንዳች ሥራ እየሠሩ የሚያደምጡት እንደሆነ ሲናገሩ ሌሎች ደግሞ ሙዚቃ የትዝታ አቅም ያለው እንደሆነ ገልጠው የቀድሞ የስፔን እና ፈረንሳይ ፖፕ ሙዚቃዎችን እንደሚያስታውሳቸው ይናገራሉ።

በአውሮፓውያኑ 1953 የኮሪያ ጦርነት ከተጠናቀቀ በኋላ ነው ሁለቱ ኮሪያዎች የየራሳቸውን ሀገር የመሠረቱት።

ምንም እንኳ ክላሽ ባይማዘዙም ደቡብ እና ሰሜን ኮሪያ እስከዛሬ የሰላም ስምምነት ስላለፈረሙ አሁንም ጦርነት ላይ ናቸው ብሎ መቁጠር ይቻላል።

የደቡብ ኮሪያን የብሔራዊ ደኅንነት ሕግ የጣሱ ሰዎች እስከ 7 ዓመት እሥር ሊጠብቃቸው ይችላል። ነገር ግን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ሕጉ ላላ ያለ ሲሆን የመናገር ነፃነት ስለሚጋፋ ሊታገድ ይገባል የሚሉ አስተያየቶችም መደመጥ ጀምረዋል።