አሜሪካ በአማራ እና በኦሮሚያ ያሉ ግጭቶች በፖለቲካዊ ንግግር እንዲፈቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጠየቀች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች ሰላማዊ እልባት እንዲበጅላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ጠየቀች።
በክልሎቹ ያለው ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነም ነው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን በስልክ ባነጋገሩበት ወቅት የገለጹት።
በሁለቱ ክልሎች ውስጥ በቀጠሉ ግጭቶች በርካታ ንጹሃን መገደላቸው እና መቁሰላቸው እየተነገረ ሲሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ እንዲደረግ መጠየቃቸውንም ቃለ አቀባያቸው ማት ሚለር ትናንት መስከረም 17/2016 ዓ.ም በወጣው መግለጫ ተናግረዋል።
የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ኃላፊው በክልሎቹ እየተከሰተ ያለው ግጭት በፖለቲካዊ ንግግር እንዲፈታ የጠየቁት በአማራ ክልል ረገብ ብሎ እንደነበር የተዘገበው ውጊያ ከሰሞኑ ማገርሸቱ እየተነገረ ባለበት ወቅት ነው።
በፋኖ ታጣቂዎች እና በመከላከያ ሰራዊት መካከል እየተካሄደ ያለው ግጭት እንደቀጠለ ቢቢሲ በክልሉ ከሚገኙ ነዋሪዎች ሰምቷል።
ከሰሞኑ ታሪካዊቷ የጎንደር ከተማ ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥን አስተናግዳለች።
የፋኖ ታጣቂዎች ሁለት እስር ቤቶች ላይ ጥቃት በመፈጸም እስረኞችን ማስለቀቁን ተከትሎም ግጭት መፈጠሩንም ነዋሪዎች ተናግረዋል። በከተማዋ በነበረውም ግጭት ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱ ተገልጿል። መከላከያ በበኩሉ በከተማ ሰርገው የገቡ የፋኖ ታጣቂዎች ጥቃት እንደከሸፈ እና ከ50 በላይ አባላቱንም እንደተገደሉ አስታውቋል።
ቢቢሲ ከሰሞኑ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንዳሉት በምዕራብ ጎጃም ዞን እንዲሁም በሰሜን ሸዋ አካባቢዎች ግጭቶች እየተካሄዱ ነው። በታሪካዊቷ ላሊበላ ከተማ አካባቢም በከባድ መሳሪያ የታገዙ ግጭቶች ስለመከሰታቸው ሪፖርት ተደርጓል።
በእነዚህ ከተሞች አንዳንድ የገጠር ቀበሌዎች በተኩስ ልውውጥ ወይም በከባድ መሳሪያ ተኩስ በርካታ ሰላማዊ ነዋሪዎች መሞታቸውን፣ ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውን እና ንብረት መውደሙንም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር ባለፈው ዓመት ማገባደጃ ላይ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር በተገናኙበት ወቅት በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች በድርድር እንዲፈቱ ይወያያሉ ተብሎ ነበር።
ልዩ መልዕክተኛው የሰላማዊ ዜጎች ደኅንነት ጥበቃ አስፈላጊነት ለኢትዮጵያ ባለስልጣናት ያነሱላቸዋልም ተብሏል።
ማይክ ሐመር ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ስላደረጉት ቆይታ የተባለ ነገር የለም።
አንቶኒ ብሊንከን በአፍሪካ ቀንድ ስላሉ የጸጥታ ችግሮች እንዲሁም ኢትዮጵያ አንድነቷ እና ሰላሟ ተጠብቆ የበለጸገች በምትሆንበት ጉዳይ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር መወያየታቸው ተገልጿል።
በኢትዮጵያ የምግብ እርዳታ መጠነ ሰፊ ዝርፊያ መፈጸሙን ተከትሎ የተቋረጠውን እርዳታ በተመለከተም እንደገና ማስጀመርን በተመለከተም ሁለቱ ባለስልጣናት ተወያይተዋል።
በረሃብ ለተጎዱ ሰዎች የተላከ እርዳታ በከፍተኛ ሁኔታ ዝርፊያ ተፈጽሞበታል፣ እንዲሁም ሽያጭ ላይ ውሏል በሚል የዓለም ምግብ ፕሮግራም እና የአሜሪካ መንግሥት የዓለም አቀፍ ልማት ተራድኦ ድርጅትም (ዩኤስኤአይዲ) ለኢትዮጵያ የሚያደርጉትን እርዳታ ማቋረጣቸው ይታወሳል።
የምግብ እርዳታውን እንደገና ለማስጀመርም የተሻሻለ ቁጥጥርንም በተመለከተ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ መክረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በዚህ የስልክ ቆይታ ያነሱት ሌላኛው ጉዳይ የሽግግር ፍትህ ሂደትን በተመለከተ ነው። አገሪቱ እውነተኛ፣ ተዓማኒ እና ሁሉን ያካተተ የፍትህ ሂደት ለመዘርጋት እየተከናወነ ያለውን ስራም በበጎ እንደሚያዩትም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መንገራቸውም ሰፍሯል።
ከሰሞኑ የተባበሩት መንግሥታት መርማሪ ኮሚሽን ኢትዮጵያ የሽግግር ፍትህ ሂደቱን ያቋቋመችው ዓለም አቀፍ ምርመራዎችን ለማምለጥ ነው ሲል ትችቱን አቅርቦ ነበር።
በኢትዮጵያ የርስ በርስ ጦርነት የተፈጸሙ ጥሰቶችን እንዲያጣራ በተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የተቋቋመው የሰብዓዊ መብቶች የባለሙያዎች ቡድን የፕሪቶሪያው ስምምነት የጦር ወንጀሎችን ማቆም ተስኖታል ብሏል።
የፕሪቶሪያው ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት ተከትሎም የጦር ወንጀሎች እና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች መቀጠላቸውን ኮሚሽኑ ከሰሞኑ ባወጣው ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል።
ኮሚሽኑ የኢትዮጵያ መንግሥት ጥሰቶችን በብቃት መከላከልም ሆነ ለመርመር እንደተሳነው እና በምትኩ አካታች እና ግልጽነት የሚጎድለውና ችግር ያለበትን የሽግግር ሂደት መጀመሩን ገልጿል።












