የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር "ግብፅ ውይይትን ገሸሽ አድርጋለች፤ ከቅኝ ግዛት ዕሳቤም አልወጣችም" ሲል ከሰሰ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ የግብፅ ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ ለውይይት የቀረበ ጥሪን "ውድቅ አድርገዋል" እንዲሁም "ቀጥተኛ በሆነም ባልሆነም መንገድ ዛቻ ማድረስ ቀጥለዋል" ስትል ኢትዮጵያ ከሰሰች።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት ኅዳር 24/2018 ዓ. ም. ከሰዓት ባወጣው መግለጫ፤ "የግብፅ መንግሥት ወደ 21ኛው ክፍለ ዘመን መሻገር አልቻለም" ሲል ወንጅሏል።
ይህ መግለጫ የወጣው የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብዲላቲ፤ ግድቡን በተመለከተ ከኢትዮጵያ ጋር "ተጨማሪ ውይይት" እንደማይደረግ ለቢቢሲ ከተናገሩ ከቀናት በኋላ ነው።
ከቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ ላለፉት 13 ዓመታት የተደረጉ ውይይቶች "አንዳችም መፍትሔ" አላመጡም ማለታቸው ይታወሳል።
የሕዳሴ ግድቡ ከተመረቀ በኋላ በኢትዮጵያ እና በግብፅ መካከል ያለው ግንኙነት "የበለጠ መሻከሩን" ጠቅሰው፤ በዚህ መካረር ምክንያት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ "ስጋት ሊሰማው" እንደሚገባም ተናግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት ባወጣው መግለጫ "በቅኝ ግዛት ዕሳቤ የተዋጡ አንዳንድ የግብፅ ባለሥልጣናት በዓባይ ውሃ ላይ ብቸኛ ተጠቃሚ የመሆን መብት ያላቸው ይመስላቸዋል" ብሏል።
"የቅኝ ግዛት ስምምነቶችን በማጣቀስ 'ታሪካዊ መብት' እንዳላቸው ይናገራሉ" ሲልም መግለጫው አክሏል።
የግብጽ ባለሥልጣናት "የካይሮን ፍላጎት ለማስፈጸም" ሲሉ በአፍሪካ ቀንድ ላይ "የሚዘወሩ፣ ደካማ እና የተከፋፈሉ ተላላኪ አገራት" እንዲኖሩ እየሠሩ መሆኑን በመጥቀስ ወንጅሏል።
የአገሪቱ ባለሥልጣናት ይህንን ፍላጎታቸውን ለማሳካት "በአፍሪካ ቀንድ፤ በተለይም በኢትዮጵያ ላይ ያተኮረ የማተራመስ ዘመቻ እያከናወኑ" መሆኑንም ገልጿል።
የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብዲላቲ፤ ከዚህ ቀደም ከኢትዮጵያ ጋር የተደረጉ ውይይቶች ምንም ውጤት ባለማስገኘታቸው "በቀጣይም ንግግር ማድረግ አስፈላጊ አይደለም" ብለዋል።
በኢትዮጵያ መንግሥት የተሰጠው ምላሽ ግን ውይይት እና ድርድርን ገሸሽ ያደረገችው ግብፅ መሆኗን ይገልጻል።
የግብፅ "የተንሻፈፈ አካሄድ እና ጥረት የአስተዳደሩን የከሸፈ ዕሳቤ ያሳያል" ሲልም ኮንኗል።
የግድቡ ጉዳይ "ከኢትዮጵያ ጋር ካለን የሁለትዮች ግንኙነት ጋር የሚያያዝ ነው" ያሉት የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው፤ ግድቡን "እንደተናጠል እርምጃ ነው የምንቆጥረው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል። አክለውም "ሕገ ወጥ ነው" ሲሉ የመንግሥታቸውን አቋም አንጸባርቀዋል።
ግድቡ "ከዓለም አቀፍ ሕግ ጋር የሚጣጣም አይደለም" የሚል አቋማቸውን የገለጹት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ "ዓለም አቀፍ ሕግ በግልጽ እንደሚለው ማንኛውም ድንበር ተሻጋሪ ወንዝ በዓለም አቀፍ ሕግ መርሆዎች መመራት አለበት። ይህም ማለት ማሳወቅን እና ጉዳት አለማስከተሉን ማረጋገጥ ያስፈልጋል" በማለት አብራርተዋል።
የትናንቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ "ኢትዮጵያ እንደ ሌሎች የተፋሰሱ አገራት የተፈጥሮ ኃብቱን የመጠቀም መብት አላት" ያለ ሲሆን፤ "ፍትሐዊ፣ ምክንያታዊ እና እኩል ተጠቃሚነት ዓለም አቀፍ ሕግ የተከተለ ነው" ሲልም አክሏል።
በተጨማሪም መግለጫው "ኢትዮጵያ በግዛቷ ሥር ያለውን የተፈጥሮ ኃብቷን ለመጠቀም የማንንም ፈቃድ አትጠይቅም" ብሏል።
በዓለማችን በርዝመቱ የሚታወቀው የዓባይ ወንዝ ከ85 በመቶ በላይ ውሃውን የሚያገኘው ከኢትዮጵያ ነው።
የወንዙን አብዛኛውን ውሃ የምትጠቀመው ግብፅ፤ በኢትዮጵያ ግድብ መገንባቱ የውሃ መጠን ይቀንስብኛል ስትል በተደጋጋሚ ከስሳለች። ኢትዮጵያ ይሄንን ውንጀላ በተደጋጋሚ ውድቅ አድርጋለች።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ". . .እስከዛሬ ኢትዮጵያን ያላሸነፈውን ያረጀ ያፈጀ አካሄድ መለወጥ ያሻል" ብሏል።
አያይዞም "ኢትዮጵያ በፓን-አፍሪካኒዝም እና በመላው አህጉሪቱ በሚደረግ የፀረ ቅኝ ግዛት ንቅናቄ የረዥም ጊዜ ታሪክ" እንዳላት በመጥቀስ "በአፍሪካውያን ትብብር የምታምን" አገር መሆኗን አስረግጧል።
"ኢትዮጵያ፤ ካይሮ ልትተወው ያልፈለገችውን የቅኝ ግዛት ትርክት የምታስተናግድበት ቦታ የላትም" ሲልም የኢትዮጵያን መንግሥት አቋም አሳውቋል።
ከአንድ ወር በፊት ግብፅ ብሔራዊ ጥቅሟን እና የውሃ ደኅንነቷን ለማስጠበቅ "አስፈላጊ የሆኑ ሁሉንም እርምጃዎች እንደምትወስድ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል-ሲሲ መናገራቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያ በሰጠችው ምላሽ፤ ግብፅ "ሕገ ወጥነት እና የበላይነት በተሞላው መንገድ" የዓባይ ወንዝን ለመቆጣጠር መሞከሯን ቀጥላለች ብላለች።

የፎቶው ባለመብት, Abiy Ahmed Ali
ባለፈው መስከረም ወር ማገባደጃ ላይ የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ሲካሄድ የግብፁ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ ኢትዮጵያ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ምክንያት "በታችኛው ተፋሰስ የሚኖሩ የሚሊዮኖችን ሕይወት አደጋ ላይ ጥላለች" ብለው በመክሰስ አገራቸው ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፉ የፍትሕ ፍርድ ቤት እንደምትወስድ ተናግረው ነበር።
በዚያው ጉባዔ ላይ የተገኙት በተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ምክትል ቋሚ ተወካይ ዮሴፍ ካሳዬ ለግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በሰጡት ምላሽ፤ "ግብፅ ስለ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ያደረገችው ንግግር መሠረት አልባ እና አሳሳች ነው" ሲሉ አጣጥለዋል።
በትናንቱ መግለጫ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር "ግብፅ ንግግር እና ድርድር እንደማትፈልግ አሁን ግልጽ ሆኗል። ከዚህ ቀደም ድርድር እያደረገች እንደሆነ ስታስመስል ነበር። ሆኖም ግን የብቸኛ ተጠቃሚነትን በማቀንቀን የድርድር እና መፍትሔ የማግኘት ሒደትን ስታደናቅፍ ነበር" ብሏል።
ግብፅ "ለመደራደር ዝግጁ እንደሆነች ብታስመስልም ትርጉም ባለው ውይይት ላይ ለመሳተፍ አልፈቀደችም። ይህም ይፋ እና የበለጠ ቀጥተኛ ሆኗል" ሲልም አክሏል።
መግለጫው አክሎም "ድርድርን ገሸሽ በማድረግ ነገሮችን ለማባባስ በነውጠኛ ትርክት ቀጥላለች" ሲል ግብፅን ወንጅሏል።
የሕዳሴ ግድቡ ከተመረቀ በኋላ ግድቡ "በአግባቡ ባለመተዳደሩ ምክንያት የተለቀቀው ውሃ በሱዳን ጎርፍ አስከትሏል" በሚል ግብፅ ክስ አቅርባ ነበር።
ኢትዮጵያ ክሱን አስተባብላ፤ የግብፅ ክስ "ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ለማሳሳት" እንዲሁም "ሐሰተኛ የተጎጂነት ትርክት ለመፍጠር ያለመ" እንደሆነ ገልጻለች።
ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን በታላቁ ሕዳሴ ግድብ አስተዳደር እና የውሃ ሙሌት ላይ ለዓመታት ድርድር አድርገዋል። ሆኖም ሁሉንም የሚያስማማ መቋጫ ላይ ሳይደርሱ የግድቡ ግንባታ ተጠናቅቆ ሥራ ጀምሯል።
ግብፅ በአፍሪካ ግዙፉ የሆነውን ግድብ ጉዳይ ባለፉት ዓመታት ለተባበሩት መንግሥታት፣ ለአፍሪካ ኅብረት እና ለአረብ ሊግ በማቅረብ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ሞክራለች።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫም "የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ይሄንን ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ማውገዝ አለባቸው" ብሏል።
አይይዞም "እንደ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ፕሮጀክቶች አፍሪካውያን ራሳቸውን የሚችሉበት እና የለውጥ መንገድ ማሳያ ከሆኑ" ተምሳሌቶች አንዱ መሆኑን ጠቅሷል።
"ግብፅ የሚበጃት ከኢትዮጵያ ዕድገት ጋር ተቻችሎ መኖር እና በቀናነት ለትብብር መዘጋጀት ነው። ዓለምም፣ አፍሪካም የምትፈልገው ትብብር እንጂ ውጥረትና ግጭት አይደለም" ብሏል።















