ግብፅ 'የውሃ ደኅንነቴን ለማስጠበቅ እርምጃዎችን እወስዳለሁ' ማለቷን ኢትዮጵያ አጣጣለች

ግብፅ 'የውሃ ደኅንነቴን ለማስጠበቅ አስፈላጊ እርምጃዎችን እወስዳለሁ' ማለቷን ኢትዮጵያ አጣጣለች።
የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ዛሬ ጥቅምት 3/2018 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ፤ "ግብፅ ከዓባይ ወንዝ እና ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ላይ የከፈተችውን ዘመቻ አጠናክራ ቀጥላለች" ሲል ወንጅሏል።
ግብፅ ብሔራዊ ጥቅሟን እና የውሃ ደኅንነቷን ለማስጠበቅ "አስፈላጊ የሆኑ ሁሉንም እርምጃዎች እንደምትወስድ ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ አል-ሲሲ መናገራቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያ በሰጠችው ምላሽ፤ ግብፅ "ሕገ ወጥነት እና የበላይነት በተሞላው መንገድ" የዓባይ ወንዝን ለመቆጣጠር መሞከሯን ቀጥላለች ብላለች።
አል-ሲሲ በካይሮ በተካሄደው 8ኛው የውሃ ሳምንት ላይ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ግብፅ በዲፕሎማሲ እና እንደ መንግሥታቱ ድርጅት ባሉት ዓለም አቀፍ ተቋማት ላይ መተማመኗ እንደ ድክመት መቆጠር የለበትም ብለዋል።
ፕሬዚዳንቱ፤ ኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብን በማስተዳደር ረገድ እየተከተለች ያለውን "ኃላፊነት የጎደለው" አካሄድ አገራቸው "እጇን አጣጥፋ አትመለከትም" ብለዋል።
የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ "ኢትዮጵያ በዓባይ የመጠቀም መብቷን አሳልፋ እንደማትሰጥ" አስረግጧል።
"ከኢትዮጵያ ጠላቶች በኩል በእጅ አዙር ጫና ቢበረታም" የኢትዮጵያ ዕድገት "አይቀለበስም" ሲልም አክሏል።
ከቀናት በፊት የሕዳሴ ግድቡ በሱዳን 'ጎርፍ አስከትሏል' በሚል ግብፅ መክሰሷ ይታወሳል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሰጠው ምላሽ የግብፅን መግለጫ "በሐሰት የተሞላ" እና "ተንኮል አዘል" በማለት ውድቅ አድርጓል።
የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ በተካሄደበት ወቅት ደግሞ፤ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደላቲ፤ ኢትዮጵያን ወደ ዓለም አቀፉ የፍትሕ ፍርድ ቤት እንደሚወስዱ መናገራቸው አይዘነጋም።
በተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ምክትል ቋሚ ተወካይ ዮሴፍ ካሳዬ ለግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በሰጡት ምላሽ፤ "ግብፅ ስለ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ያደረገችው ንግግር መሠረት አልባ እና አሳሳች ነው" ሲሉ አጣጥለዋል።
አል-ሲሲ በካይሮ በተካሄደው 8ኛው የውሃ ሳምንት ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ድርቅ እና የውሃ መጥለቅለቅ በሚኖርበት ወቅት የውሃ አለቃቅን ለመቆጣጣር የሚያስችል እና ሁለቱን የታችኛው ተፋሰስ አገራት ያካተተ አሳሪ ስምምነት እንዲኖር ጠይቀዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ "ግብፅ በጎርፍ ከመጥለቅለቅ እስከ ረሃብ ድረስ ጽንድ ለጽንፍ ያሉ ሐሰተኛ ክሶችን ማቅረቧን" በመጥቀስ ይህም "በጋራ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ መፍትሔ ለማበጀት ፍላጎት እንደሌላት ያሳያል" ብሏል።
"ሱዳንንም ወደዚህ ሐሰተኛ ክስ ጎትታ አስገብታለች። ሆኖም ግን ኢትዮጵያ እና ሱዳን በሕዳሴ ግድቡ ላይ ለሕዝቦቻቸው ዕድገት በስኬታማ መንገድ ተባብረው እየሠሩ ነው" ሲልም አክሏል።
የግብፅ አመራሮች፤ ከፀሐይ የሚመጭ ኃይልን በመጠቀም፣ የከርሰ ምድር ውሃን በማቆር እንዲሁም የዝናብ ውሃን ለእርሻ በዋማል ረገድ "በተለይም በዓባይ ተፋሰስ አገራት ያሉ ወንድሞቻቸውን እንደሚደግፉ" ጠቁመዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ይህንን ንግግር በማጣቀስ "የግብፅ የተንሸዋረረ አፍሪካዊ ትብብር ማሳያ ነው" ሲል ተችቷል።
የዓባይ ተፋሰስ አገራትን "የግብፅ እርዳታ ተቀባይ" አድርጎ የሳለ ንግግር ነው በማለትም አጣጥሏል።
"ይህ ያረጀ ያፈጀ የትብብር ትርክት ነባራዊውን እውነታ እንዲሁም የአፍሪካን ፍላጎት አያንፀባርቅም" ሲልም አክሏል።
ግብፅ በአውሮፓውያኑ 1959 የተፈረመው እና አብዛኛውን የውሃውን ድርሻ የሚሰጣትን የቅኝ ግዛት ስምምነት በመጥቀስ የወንዙን ውሃ ሙሉ በሙሉ በበላይነት ለብቻዋ የመጠቀም ፍላጎት እንዳላት ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ከሳለች።
በዛሬው መግለጫም፤ የግብፅ ቅኝ ግዛትን ማዕከል ያደረገ ዕሳቤ "በኢትዮጵያ ላይ የከሸፈና የተንሻፈፈ ፖሊሲ" እንድትከተል አድርጓል ስትል ወንጅላለች።
ለዓመታት ኢትዮጵያን ጨምሮ የዓባይ ተፋሰስ አገራት ከግብፅ ጋር ለመነጋገር ቢሞክሩም ስኬታማ አለመሆናቸውም ተጠቅሷል።
በሦስትዮሽ ድርድር ወቅትም ይሁን የመጀመሪያው ዙር የሕዳሴ ግድቡ ሙሌት ሲከናወን ዓለም አቀፍ ሕግን በማክበር የውይይት ሙከራዎች ቢደረጉም ግብፅ በቀናነት አለመሳተፏን ኢትዮጵያ ገልጻለች።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር "እውነተኛ መተባበር የሁሉንም አገራት የመበልጸግ መብት ከግምት ያስገባ መሆን አለበት። ይህም የተፋሰሱ አገራት በዓባይ እኩልና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እንዳላቸው ዕውቅና ከመስጠት ይጀምራል" ብሏል።
ግብፅ የተፋሰሱን አገራት ፍላጎት እና መብት ችላ በማለት 'ታሪካዊ መብት' አለኝ በሚል የቅኝ ግዛት ትርክትን ታራምዳለች ሲልም ከሷል።
አያይዞም "የዓባይ ጉዳይ፤ ግብፅ አሸማጋይም፣ ጠብ አጫሪም፣ ወንጀለነኛም ሆና እንደምትቀርብባቸው ቀጣናዊ ጉዳዮች አይደለም። መፍትሔ የሚገኘው የተፋሰሱን አገራት በማሳተፍ ነው" ብሏል።
የግብፅ እጣ ፈንታ ከተፋሰሱ አገራት ጋር የተቆራኘ ስለሆነ ጉዳዩን "በእኩልነትና በቀናነት እንዲሁም ያለ ዛቻና ማስፈራሪያ" እንድትይዘውም አሳስቧል።
"ኢትዮጵያ አሁንም የዲፕሎማሲ እና ወዳጅነትን የተመረኮዘ መንገድን በመምረጥ ትቀጥላለች" በማለትም የኢትዮጵያን አቋም አንፀባርቋል።
ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን በታላቁ ሕዳሴ ግድብ አስተዳደር እና የውሃ ሙሌት ላይ ለዓመታት ድርድር አድርገዋል። ሆኖም ሁሉንም የሚያስማማ መቋጫ ላይ ሳይደርሱ የግድቡ ግንባታ ተጠናቅቆ ሥራ ጀምሯል።
ግብፅ በአፍሪካ ግዙፉ የሆነውን ግድብ ጉዳይ ባለፉት ዓመታት ለተባበሩት መንግሥታት፣ ለአፍሪካ ኅብረት እና ለአረብ ሊግ በማቅረብ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ሞክራለች።
በዓለማችን በርዝመቱ የሚታወቀው የዓባይ ወንዝ ከ85 በመቶ በላይ ውሃውን የሚያገኘው ከኢትዮጵያ ነው።
የወንዙን አብዛኛውን ውሃ የምትጠቀመው ግብፅ፤ በኢትዮጵያ ግድብ መገንባቱ የውሃ መጠን ይቀንስብኛል ስትል በተደጋጋሚ ከሳለች።















