የኢትዮጵያ መንግሥት ሕዳሴ ግድብ በሱዳን 'ጎርፍ አስከትሏል' በሚል ግብፅ ያቀረበችውን ክስ ውድቅ አደረገ

ህዳሴ ግድብ

የፎቶው ባለመብት, Abiy Ahmed Ali

የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር፤ ግብፅ ሕዳሴ ግድብ "በአግባቡ ባለመተዳደሩ ምክንያት የተለቀቀ ውሃ በሱዳን ጎርፍ እንዳስከተለ" በመግለጽ ያወጣቸውን መግለጫ፤ "በሐሰት የተሞላ" እና "ተንኮል አዘል" በማለት ውድቅ አደረገ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ባይኖር ኖሮ ባለፉት ወራት በኢትዮጵያ ደጋማ ቦታዎች የታየው "ከፍተኛ ዝናብ"፤ "ሱዳን እና ግብፅ ውስጥ በሰው ሕይወት እና በመሠረተ ልማት ላይ ታሪካዊ ውድመት ሊያመጣ ይችል" እንደነበረም ገልጿል።

የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ዛሬ ቅዳሜ መስከረም 24/2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፤ ግብፅ "በሐሰት የተሞላ፣ ቅራኔ የሞላበት እና የተዛባ ረዥም መግለጫ" አውጥታለች ሲል ከስሷል።

የግብፅ የውሃ ሀብት እና መስኖ ሚኒስቴር ያወጣው መግለጫ "ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ለማሳሳት" እንዲሁም "ሐሰተኛ የተጎጂነት ትርክት ለመፍጠር ያለመ" እንደሆነ ገልጿል።

ግብፅ ትናንት አርብ መስከረም 23 ባወጣችው መግለጫ፤ የሕዳሴ ግድብን "ሕገ ወጥ" ስትል የጠራች ሲሆን፤ የግድቡ አስተዳደር በወሰደው "ግድየለሽ" እርምጃ የተነሳ "ኢንዱስትሪያል ጎርፍ" ተከስቷል በማለት ከስሳለች።

የግብፅ መግለጫ፤ ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ምረቃ ቀን ውሃ ሲፈስ ለማሳየት ስትል "ከሚጠበቀው በላይ መጠን ያለው ውሃ ይዛ ነበር" በማለት ይወነጅላል።

ምረቃው በተከናወነ ማግስት የግድቡ አስተዳዳሪዎች "በአንድ ቀን ውስጥ 485 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የደረሰ ከፍተኛ መጠን ያለው ውሃ ለመልቀቅ ወሰኑ" ብሏል።

ይህ እና በቀጣዮቹ ቀናትም የታየው የውሃ አለቃቀቅ የግድቡ አስተዳደር "ቁጥጥር የሌለበት እና የዘፈቀደ" መሆኑን እንደሚያረጋግጥ ጠቅሷል።

ይህ የኢትዮጵያ "ድንገተኛ" ውሃ አለቃቀቅ ከሌሎች ምክንያቶች ጋር ተዳምሮ በሱዳን "የእርሻ መሬቶች" እና "በርካታ መንደሮች" እንዲጥለቀለቁ ማድረጉን በመጥቀስ ከስሷል።

የኢትዮጵያ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ለዚህ ክስ ምላሽ በሰጠበት የዛሬ መግለጫው፤ የቀረቡትን ውንጀላዎች "ተንኮል ያዘሉ" እና "መሠረት የለሽ" በማለት ውድቅ አድርጓል።

"የግብፅ መንግሥት ተቋማት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና ዓባይ ወንዝን በተመለከተ በሚያወጡት መግለጫ ላይ ውሸት ዋና አካል ሆኗል" ብሏል።

ብሉ ናይል ከሕዳሴ ግድብ በፊት የነበረውን ታሪካዊ የፍሰት መረጃ "በቀላሉ ማነጻጸር" በቀላሉ "እውነታው የት እንደሚገኝ ያሳያል" ሲልም የቀረበውን ክስ አጣጥሏል።

የሕዳሴ ግድብ ከዚህ ቀደም የታችኛው ተፋሰስ አገራት ላይ ይደርስ የነበረውን ከፍተኛ የጎርፍ መጠን እንዲቀንስ ማድረጉን ለማስረዳትም በሱዳን የተመዘገበውን "የ93 ዓመታት" የውሃ ፍሰት መረጃ ጠቅሷል።

በሚኒስቴሩ መግለጫ መሠረት፤ ግድቡ ከመገንባቱ በፊት ከፍተኛው የጎርፍ መጥለቅለቅ በነሐሴ ወር በቀን ከ800 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር እንዲሁም በመስከረም ወር ከ750 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር በላይ ይደርስ ነበር።

በነሐሴ 2017 ዓ. ም. ግን ይህ ቁጥር በአማካይ ወደ 154.7 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ዝቅ ማለቱን፤ መስከረም ላይ ደግሞ 472 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ሆኖ መመዝገቡን አስረድቷል።

የህዳሴ ግድብ ውሃ ሲፈስስ

የፎቶው ባለመብት, Office of the Prime Minister-Ethiopia

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"ቁጥሮቹ ራሳቸው ይናገራሉ" ያለው የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር፤ ግድቡ የብሉ ናይል ውሃ ቁጥጥር በተደረገበት ሁኔታ እንዲፈስስ በማድረግ "በታችኛው ተፋሰስ አገራት የሚገኙ ማኅበረሰቦች ሕይወት እና ንብረቶች ከአስከፊ ጎርፍ" እንዲጠበቁ ማድረጉን ገልጿል።

"ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ባይኖር፤ ባለፉት ጥቂት ወራት በኢትዮጵያ ደጋማ አካባቢዎች የተከሰተው ከባድ ዝናብ በሱዳን እና በግብፅ በሰው ሕይወት እና በመሠረተ ልማት ላይ ታሪካዊ ጥፋት ሊያስከትል ይችል ነበር" በማለትም የግድቡን ጥቅም አንስቷል።

በተጨማሪም የግብፅ ክስ የሱዳን ባለሥልጣናት በአገሪቱ የተከሰተውን ጎርፍ በተመለከተ ከሰጡት ምክንያት ጋር "የሚቃረን" እንደሆነ በመግለጫው ሰፍሯል።

የሱዳን የግብርና እና መስኖ ሚኒስቴር የጎርፉ ዋነኛ ምክንያት "ከኢትዮጵያ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው የናይል ገባር ከሆነው ከነጭ ዓባይ የሚወጣው የውሃ ፍሰት መጨመር" እንደሆነ መግለጻቸውን ጠቅሷል።

በተጨማሪም የሱዳን ባለሥልጣናት የፍሰት መጨመሩ "ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተገናኘ የዝናብ መጠን መቀያየር የተከሰተ" ሊሆን እንደሚችል እንዲሁም በአገሪቱ እየተካሄደ ያለው ግጭት "መሠረተ ልማቶች ላይ ያደረሱት ጉዳት" ለሁኔታው መባባስ አስተዋጾ ማድረጉን እንደተናገሩ ዘርዝሯል።

የግብፅ መግለጫ "በጎረቤቶቿ ስም የመናገር መብት እንዳላት" አድርጎ ያቀረበ መሆኑን የጠቀሰው የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር፤ የአገሪቱ ባለሥልጣናት በሱዳን የተገለጸውን "እውነታ ችላ በማለት ጥፋቱን ወደ ኢትዮጵያ ለማዞር" እንደሞከሩ ገልጿል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፤ ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር የትብብር እና የመረጃ ልውውጥ ማዕቀፍ እንዳላት እንዲሁም ሕዳሴ ግድብ የጎርፍ አደጋን ለመቀነስ እንዲያስችል በቅርበት ከአገሪቱ ባለሥልጣናት እና ባለሙያዎች ጋር እንደሚሠራ አክሏል።

"ኢትዮጵያ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ግድቦችን በመገንባት እና በማስተዳደር ረገድ የረዥም ጊዜ ልምድ ያካበተች ሀገር ነች፤ ሕዳሴን ጨምሮ ግድቦቿን በማስተዳደር ረገድ ያላትን ከፍተኛ የሙያ ደረጃ እያስጠበቀች ትቀጥላለች" ብሏል።

የግብፅ ባለሥልጣናት በናይል ተፋሰስ ላይ የያዙትን "የውሃ የበላይነት ቅዠት" በመተው ከተፋሰሱ አገራት ጋር ለጋራ ትብብር እና ብልጽግና የመሥራትን "አዲስ እውነታ መቀበልን እንዲማሩ" አሳስቧል።