ሮናልዶ የትናንቱ ግጥሚያ ሳያልቅ ስታዲየሙን ለቆ ሄደ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የማንችስተር ዩናይትድ የፊት መስመር ተጫዋች ክርስቲያኖ ሮናልዶ ቡድኑ ትናንት ምሽት የነበረው ጨዋታ ሳይጠናቀቅ ስታዲየሙን ለቆ መሄዱ ተገለጸ።
በተቀያሪ ወንበር ላይ የነበረው ፖርቹጋላዊ ቡድኑ ማንችስተር ዩናይትድ ቶተነሃምን 2-0 እየመራ 89ኛው ደቂቃ ላይ ከተቀያሪ ወንበር ተነስቶ ሲወጣ ታይቷል።
ሮናልዶ ከተቀያሪ ወንበር ተነስቶ በቀጥታ ወደ ልብስ መቀየሪያ ከሄደ በኋላ ከስታዲየሙ መውጣቱ ተገልጿል።
ከጫወታው በኋላ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የተጠየቁት አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ፤ የሮናልዶን ጉዳይ ዛሬ እንደሚመለከቱት ተናግረዋል።
“አይቼዋለሁ (ከተቀያሪ ወንበር ተነስቶ ሲሄድ)፤ ግን አላነጋገርኩትም” ብለዋል ኤሪክ ቴን ሃግ።
ሮናልዶ ስታዲየም ለቆ የወጣው አሰልጣኙ አጥቂውን አንቶኒ ኤላንጋን እና አማካዩን ክርስቲያን ኤሪክሰንን ቀይረው ካስገቡ በኋላ ነው።
ሮናልዶ ከዚህ ቀደም በነበረ ጨዋታ ተቀይሮ ሲወጣ ደስተኛ እንዳልነበረ በግልጽ አሳይቷል። ማንችስተር ዩናይትድ በሜዳው ኒውካስትል ዩናይትንድ አስተናግዶ ያለ ምንም ግብ በተለያየበት ጨዋታ፤ ሮናልዶ በራሽፎርድ ተቀይሮ ሲወጣ በውሳኔው ደስተኛ አለመሆኑን በተደጋጋሚ ጭንቅላቱን በመወዝወዝ አሳይቷል።
ከኒውካስትል ጨዋታ በኋላ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ ከሮናልዶ ጋር “ምንም አይነት ችግር የለኝም” ያሉ ሲሆን፤ የሜዳ ላይ ጨዋታውን ለማረጋገጥ ግን በብቃቱ ሊያሳምነኝ ይገባል ብለዋል።
ክርስቲያኖ ሮናልዶ ትናንት ምሽት ጨዋታው ሳይንጠናቀቅ ሜዳ ጥሎ መውጣቱ ብዙ ትችቶችን እያስከተለበት ነው።
የቀድሞ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አጥቂ ጌሪ ሊኒከር የፖርቹጋላዊው ባህሪ ቡድኑ በቶተነሃም ላይ ያስመዘገበውን አስደናቂ ድል ያደበዘዘ ሆኗል ብሏል።
“ይህ ተቀባይነት የሌለው ነው- እጅግ የወረደ ነው” ሲል በቢቢሲ ማቻ ኦፍ ዘ ደይ ፕሮግራም ላይ ተናግሯል።
የዌልስ ብሔራዊ ቡድን አምበል የነበረው አሽሊ ዊሊያምስ ደግሞ፤ “ምሽቱ ለማንችስተር ዩናይትድ ድንቅ ነበር ግን ይሄው አሁንም ሜዳ ገብቶ ስላልተጫወተው ክርስቲያኖ ሮናልዶ እያወራን ነው” ብሏል።












