የአሜሪካው የመከላከያ ሚኒስትር ለባለቤታቸው እና ለወንድማቸው ምሥጢራዊ መረጃዎችን አጋርተዋል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካው የመከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት ባለፈው ወር በግል ስልካቸው በየመን ሁቲ አማፂያን ላይ የሚፈጸምን ጥቃት በሲግናል የመልዕክት መለዋወጫ በኩል ባለቤታቸው፣ የግል ጠበቃቸውን እና ወንድማቸውን አካትተው ማጋራታቸውን በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ዘገበ።
ሚኒስትሩ ምሥጢራዊ የሆኑ ወታደራዊ መረጃዎችን በሲግናል የመልዕክት መለዋወጫ በኩል እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር መጋቢት 15 በየመን የሁቲ አማፂያን ላይ የተፈጸመን ጥቃት ሲያጋሩ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው ተብሏል።
በዚህ መልዕክታቸው ላይ በሁቲ አማፂያን ላይ የሚፈጸም ጥቃትን በተመለከተ ሚሳዔል የታጠቀ ኤፍ/ኤ 18 ሆርኔት የተሰኘ የጦር አውሮፕላን በረራን የተመለከተ መረጃ አጋርተዋል።
ባለፈው ወር የ'ዘ አትላንቲክ' ከፍተኛ አዘጋጅ ጄፍሪ ጎልድረበርግ፣ በስህተት በሲግናል የመልዕክት መለዋወጫ ላይ ከትራምፕ ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር ተካትቶ በየመን ለመፈጸም ስለታሰበ የአየር ጥቃት ውይይት ሲደረግ መከታተሉ ተዘግቦ ነበር።
አሁን ይፋ የሆነው መረጃ እንደሚያሳየው የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር የሆኑት ፒት ሄግሴት፣ የቀድሞ የፎክስ ኒውስ ፕሮዲውሰር የሆነችውን ባለቤታቸውን እንዲሁም የመከላከያ ሚኒስቴር ባልደረባ የሆኑት ወንድማቸውን ፊል እንዲሁም የግል ጠበቃቸውን ቲም ፓርላቶርን አካትተዋል ተብሏል።
ዋይት ሐውስ ለኒውዮርክ ታይምስ በሰጠው ምላሽ ምንም ዓይነት ምሥጢራዊ መረጃ አልተጋራም ሲል አስተባብሏል።
በዚህኛው የመልዕክት መለዋወጫ ቡድን ውስጥ የተካተቱት 13 ሰዎች ሲሆኑ፣ ቡድኑ የተከፈተው በመከላከያ ሚኒስትሩ በራሳቸው ነው ተብሏል።
የመከላከያ ሚኒስትሩ ከዚህ በፊት ባለቤታቸውን ከውጭ አገራት መሪዎች ጋር በነበራቸው ስብሰባ ላይ ማካተታቸው ትችት አስከትሎባቸው ነበር።
ከዚህ ቀደም የተከፈተው የውይይት ቡድን በዶናልድ ትራምፕ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ማይክ ዋልዝ መሆኑ ተገልጾ ነበር።
የትራምፕ አስተዳደር መረጃውን ያጣጣለ ሲሆን፣ የፔንታጎን ቃል ቀባይ የሆኑት ሺን ፓርኔል "የቆየ እና ከሞተበት የተነሳ ዜና" ብለዋል።
"በምንም መልኩ ዜናውን ለመጻፍ ቢሞክሩ በሲግናል ቡድኑ ውስጥ ምንም ዓይነት ምሥጢራዊ መረጃ አልተካተተም" ሲሉ አስተባብለዋል።
"እውነት የሆነው ምንድን ነው፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ የትራምፕን አጀንዳ በማስፈጸም ረገድ ጠንካራ እና ውጤታማ ሆነው መቀጠላቸው ነው።"
የቀድሞ የፎክስ ኒውስ አቅራቢ የነበሩት ሄግሴት ለመከላከያ ሚኒስትርነት ሲመረጡ ወታደራዊ ልምድ ይጎድላቸዋል፣ የገንዘብ አስተዳደር ላይም እንከን አለባቸው፣ የመጠጥ ሱሰኛ እና ፆታዊ ጥቃት በመፈጸም ይታወቃሉ በሚል ተቃውሞ ቀርቦባቸው ነበር።
ዋሺንግተን በየመን የምትፈጽመው የአየር ጥቃት የሁቲ አማፂያን በንግድ መርከቦች ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት ለማስቆም ያለመ መሆኑን ትገልጻለች።
የሁቲ አማጺያን ከእስራኤል ጋር ግንኙነት አላቸው ያሏቸው መርከቦች ላይ በቀይ ባሕር እና በኤደን ባሕረ ሰላጤ ላይ ጥቃት እያደረሱ ቆይተዋል።
ይህንንም የሚያደርጉት ለፍልስጤም ያላቸውን ድጋፍ ለመግለጽ እንደሆነ ይጠቅሳሉ።
በምላሹ አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም የሁቲ ኃይሎችን ዒላማ በማድረግ የመን ውስጥ ተከታታይ ጥቃቶችን ፈጽመዋል።
በአጸፋው የሁቲ አማጽያን ከእነዚህ አገራት ጋር ግንኙነት ያላቸውን የሌሎች አገራት መርከቦችን ዒላማ እያደረጉ ይገኛሉ።
ይህ የአማጺያኑ ጥቃት በርካታ የመርከብ ድርጅቶች በዓለም የባሕር ንግድ ውስጥ 15 በመቶ ድርሻ ያለውን የቀይ ባሕር መስመርን እንዳይጠቀሙ እያስገደዳቸው ነው።
በቅርቡ አሜሪካ በየመን የነዳጅ ማከማቻ ላይ በፈጸመችው ጥቃት 74 ሰዎች ሲገደሉ 171 መቁሰላቸውን የሁቲ አማፂያን የጤና ሚኒስቴር ገልጿል።
በሁቲ የሚመራው መንግሥት አሜሪካ የምትፈጽመውን ጥቃት "የጦር ወንጀል" ሲል አውግዞታል።












