ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዩኬ የቻጎስ ደሴቶችን ለሞሪሺየስ ለመመለስ መወሰኗን ተቹ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ "ዲያጎ ጋርሲያን አትስጡ" ሲሉ ዩናይትድ ኪንግደም የቻጎስ ደሴቶችን ለሞሪሺየስ ለማስረከብ እና ወታደራዊ ሠፈርን ለመከራየት ማቀዷን ተቹ።
ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ በጻፉት ጽሑፍ "ይህ ደሴት ከዩኬ መወሰድ የለበትም" እና የምትሰጡ ከሆነ "በታላቋ አጋራችን ላይ ጉዳት ያስከትላል" ብለዋል።
ይህ የሆነው ዋሽንግተን ማክሰኞ ዕለት ዩናይትድ ኪንግደም ደሴቲቱን ለሞሪሺየስ ለማስረከብ ማቀዷን በይፋ እንደሚደግፍ ከገለፀ በኋላ ነው።
የዩኬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለትራምፕ በሰጠው ምላሽ የቻጎስ ደሴቶች ስምምነት "ለዩኬ እና ለቁልፍ አጋሮቻችን ደህንነት እና የብሪታኒያን ሕዝብ ደህንነት ለመጠበቅ ወሳኝ ነው" ብሏል።
"የደረስንበት ስምምነት የዚህን ወሳኝ ወታደራዊ ሠፈር የረጅም ጊዜ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ለማረጋገጥ ብቸኛው መንገድ ነው" ሲል መግለጫው አስታውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር ቀደም ሲል ስምምነቱ የጦር ሠፈሩን ቀጣይ አሠራር ለመጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረው ነበር።
ቀደም ሲል ሞሪሺየስ ብሪታንያ በደሴቶቹ ላይ ሉዓላዊነት መብት የላትም ስትል ትከራከር ነበር።
ዲያጎ ጋርሲያ በደሴቶቹ ውስጥ ትልቁ ክፍል ሲሆን የዩኬ እና የአሜሪካ ጦር ኃይሎች የጋራ ወታደራዊ ሠፈር በመሆን ያገለግላል።
ባለፈው ግንቦት ወር በተገለጸው ስምምነት መሠረት ዩኬ ዲያጎ ጋርሲያን ለ99 ዓመታት በሊዝ ትከራያለች።
የትራምፕ አስተያየት የመጣው በሚቀጥለው ሳምንት በአሜሪካ እና በሞሪሺየስ መካከል ከታቀደው ውይይት በፊት ነው።
ትራምፕ ከዚህ ቀደም ዩናይትድ ኪንግደም የቻጎስ ደሴቶችን ለሞሪሺየስ ለመመለስ መወሰኗን ደግፈው አስተያየት ሰጥተው ነበር።
ትራምፕ ረቡዕ ዕለት በትሩዝ ሶሸል የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ በጻፉት ጽሑፍ "የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመርን ለአገራት ሊዝ ምንም ጥቅም እንደሌለው እና የ100 ዓመት የሊዝ ስምምነት በመግባት ትልቅ ስህተት እየሰሩ እንደሆነ ነግሬያቸዋለሁ…" ብለዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዲያጎ ጋርሲያ "በሕንድ ውቅያኖስ ውስጥ ስትራቴጂካዊ በሆነ ቦታ ላይ ትገኛለች" ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል።
"ጠቅላይ ሚኒስትር ስታርመር ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በተከሰተ የይገባኛል ጥያቄ ምክንያት የዚህን አስፈላጊ ደሴት ቁጥጥር እያጡ ነው" ብለዋል።
"ሁልጊዜም ለዩኬ ለመታገል ዝግጁ፣ ፈቃደኛ ነን እንዲሁም አቅም አለን፣ ነገር ግን ዎኪዝም እና ሌሎች ችግሮች በፊታቸው ሲጋፈጡ ጠንካራ ሆነው መቆየት አለባቸው።"
ትራምፕ አገራቸው ከቴህራን ጋር ስለምታካሂደው የኒውክሌር ፕሮግራም ሲናገሩ "ኢራን ስምምነት ላለማድረግ ከወሰነች፣ ዩናይትድ ስቴትስ እጅግ በጣም ያልተረጋጋ እና አደገኛ በሆነ አገዛዝ ሊሰነዘር የሚችለውን ጥቃት ለማስወገድ ዲያጎ ጋርሲያን መጠቀም ሊያስፈልጋት ይችላል" ብለዋል።
የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር ኢራን ላይ ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ በተደጋጋሚ ሲያስፈራራ ቆይቷል።