ሕንድ ከሩሲያ ነዳጅ ላለመግዛት፤ በምትኩም የተጣለባት የቅጣት ታሪፍ እንዲነሳ ከአሜሪካ ጋር ተስማማች

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ከሕንድ በሚገቡ ምርቶች ላይ ጥላ የነበረውን የ25 በመቶ ታሪፍ ወደ 18% ዝቅ እንድታደርግ የሚያስችል የንግድ ስምምነት ከሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ጋር መስማማታቸውን አስታወቁ።

ትራምፕ፤ ትሩዝ ሶሻል በተባለው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ሕንድ የንግድ መሰናክሎችን ወደ ዜሮ እንደምትቀንስ እና ከሩሲያ ነዳጅ መግዛት እንደምታቆም ገልጸዋል። ከዚህ ቀደም ሕንድ ከሩሲያ ነዳጅ መግዛቷ ለማቆም ባለመስማማቷ በቅጣትነት ተጥሎባት የነበረው ተጨማሪ የ25% ታሪፍም እንደሚነሳ አስታውቀዋል።

የሁለቱ አገራት ስምምነት ይፋ የሆነው፤ ሕንድ እና የአውሮፓ ኅብረት ለሁለት አስርት ዓመታት ያህል ንግግር ሲደረግበት የነበረውን ታሪካዊ የንግድ ስምምነት መፈጸማቸውን ይፋ ባደረጉ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነው።

የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ፤ ከአሜሪካ ጋር ስምምነት ላይ በመደረሱ "መደሰታቸውን" በኤክስ ገጻቸው ባጋሩት ልጥፍ ገልጸዋል።

ትራምፕ በማኅበራዊ ገጻቸው በለጠፉት ጽሑፍ፤ ከሞዲ ጋር ያደረጉት የስልክ ንግግር ንግድ እንዲሁም የሩሲያ-ዩክቴን ጦርነትን የተመለከተ እንደነበር ተናግረዋል።

"የሩሲያን ነዳጅ መግዛት ለማቆም እና ከአሜሪካ እንዲሁም ምናልባትም ከቬንዙዌላ ብዙ ነዳጅ ለመግዛት ተስማምተዋል" ሲሉ ትራምፕ ጽፈዋል።

ትራምፕ፤ በሞዲ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ በመስጠት ወዲያውኑ "ለንግድ ስምምነት መስማማታቸውን" ጠቅሰዋል። ስምምነቱ የተጣሉ ታሪፎች እንዲቀነሱ እንዲሁም የሕንድ ታሪፍ እና ታሪፍ ነክ ያልሆኑ የንግድ መሰናክሎች ወደ ዜሮ እንዲወርዱ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።

በተጨማሪም የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከ500 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጡ እንደ ኤነርጂ፣ ቴክኖሎጂ፣ የግብርና ውጤት እና ከሰል ያሉ ምርቶችን ከአሜሪካ ለመግዛት መስማማታቸውን አክለዋል።

አሜሪካ ከሕንድ የሚገቡ ምርቶች ላይ 50% ታሪፍ ከጣለች ወዲህ የዋሽንግተን እና የኒው ደልሂ ግንኙነት ሻክሮ ቆይቷል። ባለፈው ነሐሴ ላይ ደግሞ ሕንድ የሩሲያን ነዳጅ እየገዛች በመሆኑ ሌላ የ25% የቅጣት ታሪፍ ተጥሎባታል።

በአሁኑ ስምምነት መሠረት ከሩሲያ ነዳጅ ጋር የተያያዘው የቅጣት ታሪፍ ሙሉ በሙሉ እንደሚነሳ እንዲሁም ሌሎች ታሪፎች ወደ 18 በመቶ ዝቅ እንደሚደረጉ ዋይት ሐውስ ለቢቢሲ አረጋግጧል።

ሞዲ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ "ለዚህ ድንቅ ብስራት 1.4 በሆነው የሕንድ ሕዝብ ስም ፕሬዝዳንት ትራምፕን በጣም አመሰግናለሁ" ብለዋል።

"ሁለት ትልቅ ኢኮኖሚዎች እና ግዙፍ የዓለም ዴሞክራሲያዊ አገራት አንድ ላይ ሲሰሩ ሕዝባችንን ይጠቅማል፤ በሁለትዮሽ ጥቅም ላይ ለተመሰረተ ትብብርም ትልቅ ዕድል ይከፍታል" ሲሉ ጽፈዋል።

ትራምፕ የጣሉት ታሪፍ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ አንስቶ ሕንድ ወደ አሜሪካ የምትልከው ምርት ብዛት በከፍተኛ ደረጃ አሽቆልቁሏል።

የሕንድ ባለሥልጣናት፤ የትራምፕ ታሪፍ ችግር ውስጥ ከጣላቸው ሌሎች አገራት ጋር አጋርነት ለመፍጠር ሲጥሩ ቆይተዋል።

ባለፈው ሳምንት ሕንድ እና የአውሮፓ ኅብረት በሁሉም ዕቃዎች ላይ በሚባል ደረጃ የተጣለው ቀረጥ እንዲቀንስ የሚያደርግ የነፃ ንግድ ስምምነት መፈጸማቸውን አስታውቀዋል። ይህ ስምምነት ሕንድ እና የኅብረቱ አባል የሆኑት 27 አውሮፓውያን አገራት ከአሜሪካ ጋር የተፈጠረው ውጥረት እየተባባሰ በመሆኑ ግንኙነታቸውን ለማጥበቅ ማሰባቸውን የሚያሳይ ነው።