የኢራኑን ጠቅላይ መሪ ለመግደል እስራኤል እና አሜሪካ ለወራት ያደረጉት ዕቅድ

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የኢራኑን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒን የመግደል እርምጃ ብዙዎች እንደሚጠብቁት ድንገት በእኩለ ለሊት የተፈጸመ አይደለም፤ ከዚያ ይልቅ ማለዳ የሆነ ነው።

ይህ የሆነበት ምክንያት አሜሪካ እና እስራኤል ከሰዓታት በፊት ቀደም ብሎ እጃቸው ላይ የገባን ወሳኝ የስለላ መረጃ ለመጠቀም መወሰናቸው ነው።

ለወራት ከፍተኛ የኢራን ባለሥልጣናት እስኪሰባሰቡ ድረስ እየጠበቁ የነበረ ሲሆን ቅዳሜ ማለዳ በማዕከላዊ ቴህራን በሚገኘው ቅጥር ግቢ ውስጥ ኻሜኒ እንደሚገኙ ተረዱ።

በተመሳሳይ ሰዓት ሌሎች ወታደራዊ እና የደኅንነት ባለሥልጣናት ስለሚሰባሰቡበት ስፍራ መረጃ ደርሷቸዋል።

ለወራት አሜሪካ እና እስራኤል የጠቅላይ መሪውን እንቅስቃሴ ሲከታተሉ ነበር። የተጠቀሙት ስልት ሚስጢራዊ ቢሆንም የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ያሰፈሩት መልዕክት ግን ፍንጭ ይሰጣል።

"[ኻሜኒ] ከደኅንነት ክትትላችን እና እጅግ ውስብሰብ ከሆነው የመከታተያ ስርዓታችን ሊያመልጥ አልቻለም" ነበር ያሉት።

ይህ ገለጻቸው መረጃ የሚያቀብልን ሰው ሊያመለክት ቢችልም ኢራናውያን ላይ ክትትል የሚያደርግ መሣሪያ የመሆን ዕድሉም ሰፊ ነው።

ባለፈው ዓመት ሰኔ ላይ በተካሄደው የ12 ቀናት ጦርነት ወቅት እስራኤል ከኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም ጋር የተያያዙ ሳይንቲስቶች እንዲሁም ባለሥልጣናት ላይ ዒላማ በማድረግ ጥቃት ሰንዝራለች።

በዚህ ወቅት የግለሰቦቹን እንቅስቃሴ ክትትል ለማድረግ የቴሌኮም እና የተንቀሳቃሽ ስልክ ስርዓቶችን መጠቀሟ ተገልጿል።

ይህ ከቁልፍ ባለሥልጣናት ጋር ግንኙነት ያላቸውን ጠባቂዎች እንቅስቃሴን ያካተተ ነው።

በረዥም ጊዜ ውስጥ "አዋዋላቸውን ለመረዳት" የሚጠቅም ሲሆን ከዚያ በተጨማሪ እንቅስቃሴዎቻቸውን እና ተጋላጭ የሚሆኑበትን ቅጽበት ለማግኘት ያግዛል።

ኢራን የበላይ መሪው በጠላቶቿ ዕይታ ውስጥ መሆናቸውን ትረዳለች። ስለዚህ በእነዚህ ወራቶች ውስጥ ተጋላጭነቶችን መለየት እና መፍትሄ መስጠት አለመቻሏ ለኢራን ደኅንነት እና ፀረ ስለላ ከፍተኛ ውድቀት ነው።

ወይንም ደግሞ እስራኤል እና አሜሪካ አዳዲስ የመከታተያ መንገዶችን ለማግኘት ዘዴዎቻቸውን በፍጥነት መቀያየር እንደሚችሉ ይጠቁማል።

አልያም ኢራናውያን በቀን ብርሃን የሚሰነዘር ጥቃት አነስተኛ መሆኑን አስልተውም ሊሆን ይችላል።

ኒውዮርክ ታይምስ እንደዘገበው አሊ ኻሜኒን ለመግደል በተወሰደው እርምጃ መረጃው የተገኘው ከሲአይኤ ቢሆንም፣ ጥቃቱን እስራኤል እንድትፈጽም ተላልፎ ተሰጥቷታል።

እስካሁን እየሆኑ ያሉት ነገሮች እንደሚያሳዩት በእስራኤል እና በአሜሪካ መካከል ግልጽ የሆነ የሥራ ክፍፍል መኖሩን ነው።

እስራኤል የኢራን ባለሥልጣናት ላይ ጥቃት ስትፈጽም አሜሪካ ደግሞ ወታደራዊ ዒላማዎች ላይ ታተኩራለች።

በዚህም የተነሳ የእስራኤል የስለላ ተቋም የከፍተኛ መሪውን እና የሌሎች ባለሥልጣናትን እንቅስቃሴ በተመለከተ አስቀድሞ መረጃ በመቀበል የረዥም ርቀት ሚሳዔሎችን የሚተኩሱ ጄቶችን በመጠቀም ጥቃት ለማካሄድ ዕቅድ ማውጣት ችሏል።

ስለዚህም አንድ ጥቃት ብቻ ፈጽሞ ባለሥልጣናቱን ከማስወገድ ይልቅ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ ለማካሄድ የተፈጠረውን ዕድል ለመጠቀም ሁለቱም አገራት በጥምረት ተንቀሳቅሰዋል።

የእስራኤል የጦር አውሮፕላኖች ቴህራን ለመድረስ ሁለት ሰዓት ያህል ሊፈጅባቸው ይችላል፤ ነገር ግን ከምን ያህል ርቀት ላይ ሚሳዔሎቻቸውን እንደተኮሱ ግልጽ አይደለም።

ውሳኔው ሲወሰድ የእስራኤል ጄቶች በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር 9፡40 አካባቢ 30 ቦምቦችን ተጠቅመው ጥቃት መፈጸማቸው ተዘግቧል።

ይህም ምናልባት የበላይ ኃላፊው በቅጥር ግቢው ውስጥ በሚገኝ፣ ከምድር በታች የተቆፈረ ዋሻ ውስጥ ተደብቀው ሊሆን ስለሚችል ነው።

በርካታ ሚሳዔሎችን በመተኮስ ስፍራውን መደብደብ ያስፈለገው ጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ የተደበቀን ዒላማ ለማግኘት እንደሆነ ይታመናል።

በኢራን ዋና ከተማ ላይ ጥቃት ከተፈጸመባቸው ሌሎች ስፍራዎች መካከል አንዱ የፕሬዚዳንቱ ማስዑድ ፔዜሽኪያን ቢሮ ሲሆን በኋላ ላይ መግለጫ በማውጣት ደህና መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኢራን የመከላከያ ምክር ቤት ጸሐፊ አሊ ሻምካኒ፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ ብርጋዴር ጄኔራል አዚዝ ናስርዛዴህ እና የኢራን ሪጂክ አዛዥ ጄኔራል መሐመድ ፓኩርን ጨምሮ ሦስት ከፍተኛ የኢራን የመከላከያ ባለሥልጣናት መገደላቸውን የኢራን መንግሥት አረጋግጧል።

የጦር ጄቶቹ ጥቃት በፈጸሙበት ወቅት፣ ፕሬዚዳንት ትራምፕ እና ከፍተኛ ባለሥልጣኖቻቸው በተሰባሰቡበት በፍሎሪዳ ማር አ ላጎ እኩለ ሌሊት ነበር።

የኢራን የበላይ መሪ መገደላቸውን ለማረጋገጥ ሰዓታት ይፈጅ ነበር።

ኢራን ይህ ሊሆን እንደሚችል በማወቅ ተዘጋጅታለች። ለኻሜኒ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናትም ጭምር ተተኪዎችን ለማዘጋጀት ዕቅድ መኖሩን የሚወጡ ዘገባዎች ያሳያሉ።

በዚህም የተነሳ የበላይ መሪው ግድያው ለዚህ ግጭት ምን ማለት እንደሆነ እስካሁን ግልጽ አይደለም።