የኢራን የኒውክሌር ጣቢያዎችን ማጥቃት ምን ዓይነት አደጋዎች ሊያስከትል ይችላል?

እስራኤል በኢራን ላይ እየፈፀመችው ባለው ጥቃት የኒውክሌር መሠረተ ልማቷን ኢላማ አድርጋለች። በዋናነት ትኩረቷን ያደረገችው ደግሞ ከምድር በታች የሚገኙ የዩራኒየም ማበልጸጊያ ማዕከላቷ ላይ ነው።

እንደ ዓለም አቀፉ የአውቶሚክ ኢነርጅ ኤጀንሲ ከሆነ በአገሪቷ ማዕከላዊ ክፍል የሚገኘው ናታንዝ የኒውክሌር ጣቢያ የደረሰበትን ከባድ ጉዳት ተቋቁሟል።

ሌላኛው ፎርዶ የሚባለው ማዕከሏ ደግሞ በተራራ ሥር ከመሬት በታች በጥልቀት የተገነባ ነው። በመሆኑም ይህንን ከምድር በታች የሚገኝ ጣቢያ ለመምታት እጅግ ኃይለኛ የሆነ ቦምብ ያስፈልጋል።

ይህ ቦምብ ያላት ደግሞ አሜሪካ ብቻ ናት።

አሜሪካ ይህንን ብታደርግ እና በፎርዶ ላይ የቦምብ ጥቃት ቢፈፀም ምን ሊከሰት ይችላል?

ዓለም አቀፉ የአውቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ የኢራን የኒውክሌር ማዕከላት ላይ የተፈፀመውን ጥቃት "እጅግ አሳሳቢ" ሲል ገልጾታል።

የኤጄንሲው ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ግሮሲ ሰኞ ዕለት እንደተናገሩት "የወታደራዊ እርምጃዎች መባባስ በሰዎች እና በአካባቢ ላይ ከባድ ጉዳት የሚያስከትሉ ጨረሮች የመለቀቅ አደጋን ይጨምራል" ብለዋል።

የዩራኒየም ማበልጸጊያ ጣቢያዎች ወደተለያየ ቁስ አካል የመለወጥ ባህርይ ባላቸው አይሶቶፕስ ከተባሉ ኬሚካላዊ ንጥረ ነገሮች የሚሠሩ ቁሶችን ለማዘጋጀት ያገለግላሉ።

በሰሪይ ዩኒቨርሲቲ እና በዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ የፊዚክስ ቤተ ሙከራ ፕሮፌሰር የሆኑት ፓዲይ ሬጋን ዩራኒየምን ከመሬት ውስጥ ሲወጣ በሁለት መልክ እንደሚወጣ ያስረዳሉ።

"99.3 በመቶው ዩራኒየም-238 ሲሆን 0.7 በመቶው ደግሞ ዩራኒየም-235 ነው። የኒውክሌር የጦር መሣሪያ ለመሥራት የሚያስፈልገው ደግሞ ሁለተኛው ነው" ይላሉ።

የኃይል ፍንዳታ

ኒውክሌር የማበልጸግ ሒደት ማለት የዩራኒየም-235 መጠንን መጨመር ማለት ነው።

ይህ የሚሠራው ዩራኒየምን በጋዝ መልክ በመውሰድ እና ሴንትሪፊዩጋል በተባለ ማሽን በፍጥነት በማሽከርከር እንደሆነ ፕሮፌሰር ሬጋን ተናግረዋል።

ምክንያቱም ዩራኒየም-238 ከሚፈለገው ዩራኒየም-235 በበለጠ ከባድ ስለሆነ ሒደቱ ሁለቱን ለመለየት ያስችላል። በመሆኑም ዩራኒየሙ ይበልጥ እንዲበለጽግ ለማድረግ ይህንን በተደጋጋሚ ማድረግ ያስፈልጋል።

የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች፣ መቆጣጠር የሚቻል እና ኃይል የሚያወጣ የኒውክሌር ኃይል ለመፍጠር በዚህ መልኩ ከበለጸገው ዩራኒየም ከ3 እስከ 5 በመቶ የሚሆነው ብቻ ነው የሚያስፈልጋቸው።

ነገር ግን ዓላማው የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ለመሥራት ከሆነ የዩራኒየም-235 ከፍተኛ መጠን ማለትም እስከ 90 በመቶ ያህል ክምችት ያስፈልጋል።

ዩራኒየሙ በበለጸገ ቁጥርም ሁሉም አቶሞች ሲለያዩ የሚወጣው ኃይል ከፍተኛ ነው።

ዓለም አቀፉ የአውቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ እንደሚለው የኢራን ዩራኒየም 60 በመቶ በልጽጓል። በመሆኑም የኒውክሌር መሣሪያ ለመሥራት ጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል ማለት ነው።

ሆኖም በእነዚህ በበለጸጉት የዩራኒየም ክምችቶች ላይ ሮኬት መተኮስ በጃፓን ፉኩሺማ ወይም በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ቸርኖቤል በኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ላይ ከተከሰቱ አደጋዎች ጋር ተመሳሳይ በሆነ መጠን "የኒውክሌር አደጋን" አያስከትልም።

"በከፍተኛ ሁኔታ የበለጸገ ዩራኒየም ካልበለጸገ ዩራኒየም በሦስት እጥፍ ራዲዮአክቲቭ ጨረሮች አሉት። ሆኖም በመጠናቸው ልክ ሁለቱም በራዲዮአክቲቭ ጨረሮች የተሞሉ አይደሉም። ስለሆነም የአካባቢ ብክለት ችግር አያስከትሉም" ብለዋል ከቸርኖቤል አደጋ በኋላ ያለው ክስተት ያጠኑትና በፖርትማውዝ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ጂም ስሚዝ።

"ሁላችንም በጣም የሰጋነው ፊውዥን ውጤቶች ላይ ነው።ይህም ዩራኒየሙ ከቦምብ ወይም ከሌላ ነገር ጋር በሚጋጭበት ጊዜ የሚፈጠሩ እንደ ራዲዮአክቲቭ ካሲየም፣ ራዲዮአክቲቭ ስትሮንቲየም፣ ራዲዮአክቲቭ አይዮዲን ያሉ ነገሮች ናቸው።እነዚህ አካባቢን የሚመርዙ ናቸው።"

ሆኖም በኒውክሌር ማበልጸጊያ ጣቢያዎች የኒውክሌር ሪአክሽን ካልተፈጠረ እና የቦምብ ፍንዳታው ካልነካው እነዚህ አደገኛ ራዲዮአክቲቭ -ፊውዥን ፕሮዳክቶች "አይኖሩም" ብለዋል።

በምትኩ በፍንዳታው ዩራኒየሙ እዚያው አካባቢ ሊበተን ይችላል።

በአካባቢው የሚኖር ስጋት

በናታንዝ ማዕከል ላይ ጥቃት ከተፈፀመ በኋላ ዓለም አቀፉ የአውቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ በአካባቢው የራዲዮአክቲቭ ብክለቶችን እንዳገኘ ገልጿል። ነገር ግን የራዲዮአክቲቩ [ጨረር] መጠን ያልተለወጠ እና መደበኛ መሆኑን አመልክቷል።

በብሪስቶል ዩኒቨርሲቲ የሚኒራል እና የራዲዮአክቲቭ ተረፈ ምርቶች አስተዳደር ኃላፊ የሆኑት ፕሮፌሰር ክሌር ኮርክሂል፣ "የዩራኒየም ጨረሩ ብዙም ሩቅ አይጓዝም" ብለዋል። ሆኖም ለማዕከላቱ ቅርብ የሆኑ ሰዎችን ጤና ለአደጋ ሊያጋልጥ እንደሚችል ተናግረዋል።

"በሰውነት ላይ የሚያስከትለውን መርዛማነት በተመለከተም፣ የዩራኒየም ቅንጣጢቶች በትንፋሽ እና በምግብ አማካኝነት ወደ ሳንባችን፣ ወደ ሆዳችን እንዲሁም በሴሎቻችን ውስጥ ይገባሉ። ቀስ በቀስም ጉዳት ያስከትላሉ" ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ለራዲዮአክቲቭ ኬሚካል መጋለጥ በአቅራቢያ ለሚኖር ሰው ጉዳት ሊያስከትል ይችላል።

በባንገር ዩኒቨርሲቲ የኒውክሌር ማቴሪያል ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ሳይመን ሚድልበርግም "አደጋ ቢከሰት እና ሴንትሪፉጅስ ሄክሳፍሎራይድ የተባለውን የዩራኒየም ጋዝ የሚለቀቅ ከሆነ ከባድ የኬሚካል አደጋ ያስከትላል" ብለዋል።

ፕሮፌሰር ሳይመን እንደሚሉት የዩራኒየሙ ሄክሳፍሎራይድ ከአየር እርጥበት ጋር ከተገናኘ እጅግ በጣም ጠንካራ የሆነ አሲድ ስለሚፈጥር በጣም መርዛማ እና የሚረብሽ ነው የሚሆነው።

"ሆኖም ግን በጣም ቅርብ ከሆነው አካባቢ በስተቀር በአካባቢው ላይ መጠነ ሰፊ የሆነ ተፅዕኖ አያስከትልም" ብለዋል።

ዓለም አቀፉ የአውቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ፣ የአደጋ እና ድንገተኛ አደጋ ማዕከሉ በአካባቢው ላይ እየሠራ ሲሆን፣ የኢራን ኒውክሌር ማዕከላት ያሉበትን ሁኔታ እና በሥፍራው ያለውን የጨረር መጠን መከታተሉን እንደሚቀጥል ገልጿል።