አያቶላህ አሊ ኻሜኒ እንዴት ለ37 ዓመታት በሥልጣን ቆዩ?

የንባብ ጊዜ: 6 ደቂቃ

የ86 ዓመቱ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ለረዥም ጊዜ በሥልጣን ከቆዩ መሪዎች አንዱ ነበሩ። ለአራት አሥርት ዓመታት ኢራን በአምባገነን አስተዳደራቸው ሥር ዘልቃለች።

በአሜሪካ እና እስራኤል ጥምር ጥቃት የተገደሉት ጠቅላይ መሪው ከአውሮፓውያኑ 1989 ወዲህ ኢራንን አስተዳድረዋል። የ1979ኙን የኢራን አብዮት ተከትሎ ሁለተኛው የኢራን መሪ ናቸው።

የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ እንዲሁም የኢራን ጠቅላይ መሪ መገደላቸውን ተከትሎ ብሔራዊ ሐዘን ታውጇል።

ሃይማኖታዊ አስተዳደግ

የተወለዱት በአውሮፓውያኑ 1939 ማሻሀድ ከተማ ውስጥ ነው። አባታቸው የሺአ ሃይማኖታዊ መሪ ነበሩ።

አያቶላህ አሊ ኻሜኒ በድህነት እንዳደጉ ይናገራሉ። ሃይማኖተኛ ቤተሰብ እንደማደጋቸው እሳቸውም ጥብቅ ሃይማኖተኛ ነበሩ።

"ከዳቦ እና ዘቢብ" ውጪ የሚመገቡት እንደልነበረ ይናገሩ ነበር። በማሻሀድ ከተማ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ ጀምረው ወደ ናጃ እና ኢራቅ ተሻግረዋል።

በሃይማኖታዊቷ የኢራን ከተማ ቆውም ውስጥም ተምረዋል። ኋላ ላይ እስላማዊ ዘብን የመሠረቱ መሪዎችን ጨምሮ በርካታ የሃይማኖት መምህራን አስተምረዋቸዋል።

የኢራኑን ንጉሣዊ አስተዳደር አጥብቀው ያወግዙ ነበር። የሻህ አስተዳደር በ1979 አብዮት ከሥልጣን ተወግዷል።

ለዓመታት ከዕይታ ተሰውረው ለመኖር ተገድደዋል። የሻህ ምሥጢራዊ ፖሊስ ስድስት ጊዜ አስሮ አሰቃይቷቸዋል።

በአብዮቱ ወቅት በጉልህ በአደባባይ የሚታዩ ሰው ባይሆኑም በአጭር ጊዜ ውስጥ ዋነኛ ከሆኑ መሪዎች አንዱ ለመሆን በቅተዋል።

የሻህ መንግሥት ሲገረሰስ ሥልጣን የተረከበውን አብዮታዊ ካውንስልን ተቀላቅለዋል። የሽግግር መንግሥት የተመሠረተው በዚህ ካውንሰል ነበር።

የመጀመሪያ ሥልጣናቸው የመከላከያ ምክትል ሚኒስትርነት ነበር። የቴህራን የአርብ ፀሎት መሪ ሆነውም አገልግለዋል።

ፖለቲካዊ ስብከታቸው በመላው ኢራን ይሰራጭ ነበር።

የግድያ ሙከራ

በአውሮፓውያኑ ሰኔ 1981 የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸዋል። ትምህርት እየሰጡ ሳለ ነበር ቦምብ የፈነዳው።

ከአብዮት በኋላ የአብዮት ዘቡ ሥልጣን አደላድሎ እንዲቆጣጠር በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።

የፓርቲው ዋና መቀመጫ ላይ ቦምብ ሲጣል እሳቸው ከሆስፒታል አልወጡም ነበር። የግድያ ሙከራ ሲደረግባቸው ሳምባቸው ተጎድቷል። ለማገገም ረዥም ጊዜ ወስዶባቸውም ነበር።

በወቅቱ የኢራን እጩ ፕሬዝዳንት ነበሩ።

በምርጫው ድምጽ የሚያገኙ መሪዎችን የሚወስነውን ካውንስል በዋናነት ይቆጣጠሩ ነበር። 97 በመቶ ድምጽም አግኝተዋል።

"ሊበራሊዝም እና ግራ ዘመም የአሜሪካ ዕሳቤን" ለማስወገድ ቃል በመግባት ነው ወደ መሪነት የመጡት።

የኢራን-ኢራቅ ጦርነት

ምርጫው ከመካሄዱ ከወራት አስቀድሞ ኢራቅ ኢራንን ወረረች።

የኢራቅ ፕሬዝዳንት ሳዳም ሑሴን የኢራን አብዮት ሥልጣናቸውን እንዳይገዳደር በመስጋት ጥቃት ፈጽመዋል።

ስምንት ወራት በወሰደው ግጭት በሁለቱም አገራት በኩል በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል።

ኢራቅ ከኢራን ጋር በሚያዋስኗት መንደሮች ኬሚካል የጦር መሣሪያ ተጠቅማለች። እንደ ቴህራን ያሉ ከተማዎችን በሚሳዔል ደብድባለች።

አሜሪካ በወቅቱ ለኢራቅ ድጋፍ ሰጥታለች። በጦርነቱ ምክንያት ኻሜኒ አሜሪካን የበለጠ መጠራጠራቸውን ቀጥለዋል።

ጠቅላይ መሪው ኻሜኒ

በ1989 አያቶላህ ካሆሜኒ ሲሞቱ አያቶላህ ኻሜኒ ተተክተዋል። ጠንካራ የሃይማኖት መሠረት የላቸውም ተብለው ተተችተው ነበር።

"ብዙ ድክመት ያለብኝ ሰው ነኝ" ሲሉ ነበር የመጀመሪያ ንግግራቸውን ያደረጉት።

"ሆኖም ግን የፈጣሪ እርዳታ ተጨምሮበት የተጣለብኝን ከባድ ኃላፊነት በሙሉ አቅሜ እወጣለሁ" ብለውም ቃል ገብተዋል።

የአያቶላህ ካሆሜኒ የቅርብ ሰዎች ኻሜኒን እምብዛም ስላላመኗቸው በጥንቃቄ ይጓዙ ነበር።

ቆየት ብለው በፍትሕ ሥርዓቱ፣ በፀጥታ ኃይሉ፣ በምክር ቤቱ እና በመገናኛ ብዙኃን ታማኝ ወዳጆችን ማፍራት ቻሉ።

በዋሽንግተን በሚገኘው ካንኒጌ ኢንዶውመንት ፎር ኢንተርናሽናል ፒስ ውስጥ የሚሠሩት ካሪም ሳድጃፑር እንደሚናገሩት የኻሜኒ ሥልጣን በአብዮት ዘቡ እና በሃይማኖት መሪዎች ጥበቃ ለዓመታት ቆይቷል።

የኢራን መገናኛ ብዙኃን ጠቅላይ መሪው ከባለቤታቸው፣ ከልጆቻቸው እና የልጅ ልጆቻቸው ጋር በመተሳሰብ እንደሚኖሩ የሚያሳዩ ዘገባዎች ሲያወጣ ቆይቷል።

የተቃውሞ መበርታት

ጠቅላይ መሪው ተቃውሞዎችን በማፈን ሥልጣናቸውን አስቀጥለዋል።

በአውሮፓውያኑ 1999 የኢራን ተማሪዎች ተቃውሞ ቢነሳም ብዙ ርቀት አልተጓዘም። ከአሥር ዓመት በኋላ የምርጫ መጭበርበርን በመቃወም የተነሳ ተቃውሞም ታፍኗል።

ተቃዋሚዎች አስለቃሽ ጭስ ተተኩሶባቸዋል፤ ተደብድበዋል፤ በጥይትም ተመትተዋል።

በ2019 የነዳጅ ዋጋ መናርን ተከትሎ ሌላ ተቃውሞ ሲነሳ ኢንተርኔት ተዘጋ። ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች አምነስቲ እንዳለው ፖሊስ ተቃዋሚዎችን ገድሏል።

ሒጃብ መልበስን የሚያስገድደውን ሕግ የተቃወሙ ሴቶች ስቅይት እንደተፈጸመባቸው እና ለየብቻቸው እንደታሰሩም ተገልጿል።

አንድ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ሴት 148 ጊዜ ተገርፋ የ38 ዓመት እስራት ተፈርዶባታል።

በ2022፤ የ22 ዓመቷ ማህሳ አሚኒ በኢራን ፖሊሶች ይዞታ ሥር ሳለች መሞቷን ተከትሎ ከፍተኛ ተቃውሞ ተነስቷል። ማህሳ አስገዳጁን የሒጃብ ሕግ ከተቃወሙ አንዷ ነበረች።

አሜሪካ የሚገኘው የኢራን የሰብአዊ መብት ተሟጋች እንዳለው በተቃውሞው የተገደሉ 400 ሰዎችን ስም መዝግቧል።

በቅርቡ የተነሳው ተቃውሞ መነሻው የምጣኔ ሃብት አለመረጋጋት ቢሆንም የመንግሥት ለውጥ ያስፈልጋል ወደሚለው ተሻግሯል።

ኻሜኒ ከተቃውሞው ጋር በተያያዘ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን አምነዋል።

"ከእስራኤል እና አሜሪካ ጋር ግንኙነት ያላቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ነውጥ ሲቀሰቅሱ እና ወንጀል ሲፈጽሙ ተገድለዋል" ብለዋል።

የኢራን የሰብአዊ መብት ተሟጋች ግን መንግሥት ያልተመጣጠነ የኃይል እርምጃ በመውሰዱ ከ7,000 በላይ ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል።

የኮቪድ ክትባት ክልከላ

በአውሮፓውያኑ 2022 ቢቢሲ ፐርዢያ ባደረገው ምርመራ፤ በኮሮናቫይረስ ወረርሽን ምክንያት በኢራን 300,000 ሰዎች መሞታቸው ተረጋግጧል። ቁጥሩ መንግሥት ይፋ ካደረገው በእጥፍ ይበልጣል።

አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ማስረጃ ባያቀርቡም "የኢራናውያንን ዘረ መል በመጠቀም አንደኛው የቫይረሱ ዓይነት ኢራን ላይ ያነጣጠረ ነው" ብለዋል።

የአሜሪካ እና አውሮፓ መድኃኒት አምራች ተቋማት ክትባት ማከፋፈል ሲጀምሩ ኻሜኒ ክልከላ ጥለዋል።

ጠቅላይ መሪው በኢራን ከተሠሩ ክትባቶች አንዱን መውሰዳቸው ተዘግቧል።

አሜሪካን መቃወም

ከአብዮቱ በኋላ በ1989 የአያቶላህ ካሆሜኒ ታማኝ ወዳጅ የሆኑ ተማሪዎች የአሜሪካን ኤምባሲ ተቆጣጥረው ነበር።

አሜሪካ ለሻህ ቤተሰቦች ጥገኝነት በመስጠቷ አሜሪካውያን ዲፕሎማቶችን አግተው ነበር።

ታጋቾቹ ለ444 ቀናት ተይዘው ቆይተዋል። በአገር ደረጃ ፀረ አሜሪካ እና ምዕራባውያን ፖሊሲ የተጠናከረበት ወቅት ነበር።

አያቶላህ ካሆሜኒን የተኩት አያቶላህ አሊ ኻሜኒ፤ ፀረ አሜሪካ አቋምን አስቀጥለዋል።

ከ9/11 ጥቃት በኋላ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ ኢራንን "የእኩይ ጥምረት መሪ" ብለዋል።

በሊባኖስ የሚገኘውን ሔዝቦላህ እንዲሁም ሌሎች የእስራኤል እና አሜሪካ ጠላቶችን ኢራን ትደግፋለች።

የኒውክሌር መርሃ ግብር

ኻሜኒ የኒውክሌር የጦር መሣሪያ ግንባት "እስላማዊ አይደለም" ብለው በአውሮፓውያኑ 2003 ፈትዋ ሰጥተዋል። በዚህም መሠረት አገሪቱ የኒውክሌር የጦር መሣሪያ እንደማትገነባ ተገልጿል።

ሆኖም ግን አሜሪካ እና እስራኤል ይሄንን አያምኑም። መሐሙድ አሕማዲንጂድ ፕሬዝዳንት ሳሉ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እና ሚሳዔል መገንባት መጀመሯን ይገልጻሉ።

በዚህ ምክንያት ኢራን ላይ በርካታ ማዕቀቦች ተጥለዋል።

በአውሮፓውያኑ 2015፤ ኢራን፣ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ፣ ቻይና፣ ሩሲያ እና ጀርመን የደረሱበት ስምምነት ኢራን የምታበለጽገውን የዩራንየም መጠን ይገድባል።

"ገዳይ መንግሥት ሰላማዊ የኒውክሌር መርሃ ግብር ሊኖረው አይችልም" ያሉት ትራምፕ አሜሪካን ከስምምነቱ አስወጥተዋል። የተቀሩት የስምምነቱ ፈራሚ አገራት የትራምፕን ውሳኔ ተቃውመዋል።

ኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብሯ ሰላማዊ እንደሆነ በተደጋጋሚ ገልጻለች። ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ተቋም ይሄንን አረጋግጧል።

ትራምፕ አሜሪካን ከስምምነቱ ሲያስወጡ የቀድሞው የኢራን አብዮታዊ ዘብ ኃላፊ ቃሲም ሱሌይማኒ የበቀል እርምጃ እንደሚወስዱ ዝተው ነበር።

ከሩሲያ እና ከቻይና ጋር ይቀራረቡ የነበሩት ሱሌይማኒ በአሜሪካ ተገድለዋል።

አምና እስራኤል በወሰደችው እርምጃ የኢራን የኒውክሌር ተቋማት እና ከፍተኛ አመራሮች ዒላማ ተደርገዋል። ኢራንም ወደ እስራኤል ሚሳዒል በመተኮስ የአጸፋ ጥቃት ፈጽማለች።

ኢራን የኒውክሌር የጦር መሣሪያ እንድትገነባ "በፍጹም አልፈቅድም" ያሉት ትራምፕ ከእስራኤል ጋር በመቀናጀት ኢራን ላይ ጥቃት አድርሰዋል። ኢራንም የአጸፋ እርምጃ መውሰዷን ቀጥላለች።

አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ራሳቸውን ከኢራን ፖለቲካ በላይ አድርገው ያስቀምጡ ነበር። በአምባገነንነት ኢራንን መርተዋል።

በለውጥ ፈላጊዎች እና በወግ አጥባቂዎች መካከል ላለው ፍጥጫ ብዙም ትኩረት ሳይሰጡ ቆይተዋል።

አያቶላህ አሊ ኻሜኒን ማን ይተካቸዋል? የሚለው ሲታወቅ የኢራን ቀጣይ እጣ ፈንታ ግልጽ ይሆናል።