አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ላይ የከፈቱት ጦርነት ምን ያህል ሊቆይ ይችላል?

የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

የኢራኑ የበላይ መሪ አያቶላጅ አሊ ኻሜኒ ቅዳሜ ዕለት አሜሪካ እና እስራኤል በጋራ በፈጸሙት ጥቃት መገደላቸውን ተከትሎ በመካከለኛው ምሥራቅ ግጭት እየተስፋፋ ነው።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ኢራናውያንን መንግሥታቸውን ከመንበሩ ለማውረድ ጊዜው አሁን መሆኑን በመግለጽ አበረታተዋል።

ኢራን በበኩሏ በቀጣናው ወደሚገኙ አገራት ሚሳዔሎችን እና ድሮኖችን ተጠቅማ ጥቃት መፈጸም ጀምራለች።

በኢራን ጥቃት ዒላማ ከተደረጉት አገራት መካከል እስራኤል፣ ባህሬን፣ ኳታር፣ ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ፣ ዮርዳኖስ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ቆጵሮስ እና በሆርሙዝ ሰርጥ የሚያልፉ መርከቦች ናቸው።

በኢራን መንግሥት የሚደገፈው የሊባኖሱ ታጣቂ ሄዝቦላህ ጦርነቱን ወደ እስራኤል ሮኬቶችን በማስወንጨፍ ተቀላቅሏል።

በኢራን እየሆነ የነበረው ምንድን ነው?

አሜሪካ እና እስራኤል በጋራ በመሆን ጥቃት መክፈታቸውን ተከትሎ ከፍተኛ አገሪቱ ባለሥልጣናት እንዲሁም በርካታ ሰላማዊ ዜጎች ተገድለዋል።

አገሪቱን እአአ ከ1989 ጀምሮ የመሪት አያቶላህ አሊ ኻሜኒ የተገደሉት የመጀመሪያው ጥቃት አንደተፈጸመ ነው።

የኢራን ቀይ ጨረቃ ማኅበር ባወጣው መግለጫ በመላው ኢራን በተፈጸሙ ትቃቶች የሞቱ ሰዎች ቁትር ከ700 በላይ ሆኗል። ከእነዚህ መካከል ደግሞ 176ቱ ሕጻናት መሆናቸውን እና 742 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገ የሰብአዊ መብት ድርጅት ገልጿል።

የኢራን የአየር ክልል ዝግ የተደረገ ሲሆን፣ የኢንተርኔት ግንኙነትም ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል።

የኢራን ጦር በሙሉ ኃይሉ ከአሜሪካ እና ከእስራኤል የሚፈጸምበትን ጥቃት እንደሚመክት ይናገራል።

አሜሪካ እና እስራኤል ከቅዳሜ ዕለት ጀምሮ በሚፈጽሙት ጥቃት ዋና ከተማዋን ጨምሮ የተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች እና ተቋማት ዒላማ ተደርገዋል።

ዶናልድ ትራምፕ የአገሪቱ ባሕር ኃይል ሙሉ በሙሉ መውደሙን ተናግረዋል።ሰኞ ዕለት የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንቶም) 11 የኢራን መርከቦችን በኦማን ባሕረ ሰላጤ ላይ ማስጠሙን ሲያስታውቅ ኢራን በቀጠናው ያለምንም መርከብ መቅረቷን ተነግሯል።

አሜሪካ እና እስራኤል ለምን ኢራንን አጠቁ?

ትራምፕ በኢራን ላይ የሚፈጸመው ጥቃት ዓላማ "የኑክሌር ጦር መሣሪያ እንዳይኖራት ማረጋገጥ" ነው ይላሉ።

"ሚሳኤሎቻቸውን እናወድማለን፣ የሚሳኤል ኢንዱስትሪያቸውን ዶግ አመድ እናደርጋለን" ሲሉ ቅዳሜ ዕለት በሶሻል ትሩዝ ገጻቸው ላይ በለጠፉት የቪዲዮ መልዕክት ላይ ተናግረዋል።

የኢራን የጦር ኃይሎች መሣሪያዎቻቸውን የሚፈቱ ከሆነ "ሙሉ የደኅንነት ዋስትና" እንደሚያገኙ አለበለዚያ ግን "የሞትን ጽዋ እንደሚጋፈጡ" አስጠንቅቀዋል።

ትራምፕ የኢራን ሕዝብ የአገሪቱን ሥርዓት ከመንበሩ ለማውረድ እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ አቅርበዋል።

"እኛ ስንጨርስ መንግሥትህን ከሥልጣን አውርደህ ተቆጣጠር። ያንን ማድረግ ያንተ ድርሻ ነው። ይህ ምናልባት በትውልድ ውስጥ የምታገኘው ብቸኛ ዕድል ሊሆን ይችላል።"

አሜሪካ "ኤፒክ ፊዩሪ" ብላ የሰየመችው ይህ ግዙፍ ወታደራዊ ዘመቻ የተጀመረው ትራምፕ ለሳምንታት ኢራን በኒውክሌር ፕሮግራሟ ላይ አዲስ ስምምነት ካላደረገች ወታደራዊ እርምጃ እወስዳለሁ እያሉ ከዛቱ በኋላ ነው።

ኢራን የኒውክሌር እንቅስቃሴዎቿ ሙሉ በሙሉ ሰላማዊ መሆናቸውን በተደጋጋሚ ትገልጻለች።

ኢራን የአሜሪካንና የእስራኤልን ጥቃቶች "ያለ ምንም ትንኮሳ የተደረጉ፣ ሕገወጥ እና ተቀባይነት የሌላቸው" ስትል ኮንናዋለች፤ እናም በምላሹ በቀጠናው ውስጥ በሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች ላይ ሰፊ ጥቃቶችን ፈጽማለች።

ኢራን እንዴት ምላሽ ሰጠች?

ኢራን ከአሜሪካ ጋር ግንኙነት ባላቸው በርካታ የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት፣ በቆጵሮስ የብሪታኒያ ወታደራዊ ሰፈር እና ከኢራን የባሕር ዳርቻ መርከቦች ጋር ግንኙነት ባላቸው እስራኤል ላይ የባላስቲክ ሚሳኤሎችን እና ድሮኖችን አስወንጭፋለች።

የአብዮታዊው ዘብ በቴል አቪቭ እና በሌሎች ቦታዎች የእስራኤልን መንግሥት እና ወታደራዊ ቦታዎችን ዒላማ እንዳደረገ ገልጿል።

ይህንን ጥቃት ተከትሎ በእስራኤል በቤት ሼሜሽ በሚገኝ የመኖሪያ አካባቢ ዘጠኝ ሰዎች መሞታቸውን ተገልጿል።

የአሜሪካ ወታደራዊ ሰፈሮች መገኛ የሆኑት ኳታር፣ ባህሬን፣ ዮርዳኖስ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና ኩዌት ዒላማ ሆነዋል፤ ኦማን እና ሳዑዲ አረቢያም ከኢራን ጥቃት አላመለጡም።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዜጎቹ በመካከለኛው ምሥራቅ ከሚገኙ 14 አገራት በአስቸኳይ ለቅቀው እንዲወጡ አዝዟል።

የአገሪቱ የቆንስላ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስቴር የሆኑት ሞራ ናምዳር በመሥሪያ ቤታቸው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ ባሰፈሩት መልዕክት አሜሪካውያን "ሊያጋጥሙ በሚችሉ ከባድ አደጋዎች ምክንያት" ከአስራ አራቱ አገራት "ያሉ የትራንስፖርት አመራጮችን በመጠቀም አሁኑኑ" ለቅቀው እንዲወጡ አሳስበዋል።

የአሜሪካ ዜጎች በአስቸኳይ ለቅቀው እንዲወጡ የታዘዙባቸው አገራት ባህሬን፣ ግብፅ፣ ኢራን፣ ኢራቅ፣ እስራኤል፣ የፍልስጤም ግዛቶች፣ ዮርዳኖስ፣ ኩዌት፣ ሊባኖስ፣ ኦማን፣ ኳታር፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ሶሪያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና የመን ይገኙባቸዋል።

በኩዌት የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ከማክሰኞ ጀምሮ ዝግ ሆኗል።

ጦርነቱ ተጽዕኖ በምጣኔ ሀብትን እና በነዳጅ ላይ

በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው አለመረጋጋት በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ተጽዕኖ ማሳደር ጀምሯል።

በተለይም የባሕረ ሰላጤውን ወሳኝ የነዳጅ ኢንዱስትሪዎች በዚህ ግጭት ዒላማ ከሆኑ ዘርፎች መካከል ነው።

የኳታር የመንግሥት የኢነርጂ ድርጅት በኢራን ጥቃት ምክንያት የተፈጥሮ ጋዝ ምርቱን ማቆሙን አስታውቋል። ይህም ሰኞ ዕለት በጋዝ ዋጋ ላይ በ50 በመቶ ጭማሪ አስከትሏል።

የኢራን ድሮኖች በሳዑዲ አረቢያ በሚገኘው የራስ ታኑራ የነዳጅ ማጣሪያ ላይ ጥቃት በመሰንዘራቸው በከፊል መዘራቱን የአገሪቱ የኢነርጂ ሚኒስቴር ሰኞ ዕለት አስታውቋል።

ኢራን መርከቦች በሆርሙዝ በኩል እንዳያልፉ አስጠነቅቃለች። ይህም በዓለም ላይ 20 በመቶ የሚሆነው የነዳጅና የጋዝ ምርት የሚጓጓዝበት ዋና መተላለፊያ ነው።

የነዳጅና የጋዝ ዋጋ ጨምሯል፤ ባለፈው ቅዳሜና እሁድ ቢያንስ ሦስት መርከቦች በሆርሙዝ ሰርጥ አቅራቢያ ጥቃት ከተፈጸመባቸው በኋላ፣ ዓለም አቀፉ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ለአጭር ጊዜ በአንድ በርሜል 82 ዶላር ደርሷል።

ጦርነቱ ምን ያህል ሊቆይ ይችላል?

ትራምፕ ቅዳሜ ዕለት በኢራን ላይ የሚሰነዘሩት ጥቃቶች "ለሳምንት ወይም አስፈላጊ እስከሆነ ድረስ ያለማቋረጥ ይቀጥላሉ" ብለዋል።

ከዚያን ጊዜ በኋላ ደግሞ ጦርነቱ ረዘም ላለ ጊዜ ሊካሄድ እንደሚችል ጠቁመዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት እሁድ ዕለት ለኒው ዮርክ ታይምስ እንደተናገሩት አሜሪካ እና እስራኤል ከአራት እስከ አምስት ሳምንታት በተመሳሳይ ስልት ማጥቃታቸውን መቀጠል ይችላሉ።

ትራምፕ ሰኞ ዕለት በዋይት ሐውስ ንግግር ሲያደርጉ "ከመጀመሪያው ጀምሮ ከአራት እስከ አምስት ሳምንታት ገምተናል፤ ነገር ግን ከዚያ በላይ ረዘም ላለ ጊዜ የማካሄድ አቅም አለን" ብለዋል።

አሜሪካ ከተነበየችው ጊዜ "በከፍተኛ ደረጃ ቀድማለች" ሲሉም አክለዋል።

ትራምፕ በኋላ ላይ እንዳሉት አሜሪካ ረዘም ላለ ጊዜ ጦርነት ማካሄድ የሚያስችል የመሣሪያ ክምችት እንዳላትም ተናግረዋል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው ቅዳሜ ዕለት "ይህ ዘመቻ አስፈላጊ እስከሆነ ድረስ ይቀጥላል" ብለዋል።