ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በደቡብ ሱዳን በተፈጸመ ድንገተኛ ጥቃት ቢያንስ 169 ሰዎች ተገደሉ
በደቡብ ሱዳን ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በፈጸሙት ድንገተኛ ጥቃት በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል የመንግሥት ኃላፊዎችን ጨምሮ ቢያንስ 169 ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ ባለሥልጣናት ገለፁ።
ጥቃቱ የተፈጸመው ሩዌንግ ተብሎ በሚጠራው ግዛት መሆኑን የግዛቲቱ ቃል አቀባይ ጀምስ ሞኒላውክ ሚጆክ ተናግረው የጥቃት ፈጻሚዎቹ ከጎረቤት ግዛት [ዩኒቲ ግዛት] የመጡ እና ከተቃዋሚው የሱዳን ነጻነት ጦር ጋር ግንኙነት ያላቸው ወጣቶች ሊሆኑ ይችላሉ ብለዋል።
የሱዳን የነጻነት ጦር ግን የአገሪቱ ግዛቶች ግጭቶችን ከፖለቲካ ጋር እያነካኩ ነው በሚል የቀረበበትን ክስ አስተባብሏል።
ደቡብ ሱዳን ወደ እርስ በርስ ጦርነት ለመመለስ ጫፍ ላይ ነች በማለት የመንግሥታቱ ድርጅት በተደጋጋሚ አስጠንቅቋል።
ቃል አቀባዩ እንዳሉት ከሟቾቹ መካከል 79 የሚሆኑት የመንግሥት ታጣቂዎች ናቸው። ቀሪዎቹ 90 ሟቾች ደግሞ ሕጻናት፣ አዛውንቶች እና ሴቶች ናቸው ብለዋል።
15 የቆሰሉ ሰዎች ለሕክምና ወደ አቢዬ ግዛት ተወስደዋል።
የካቲት 22 /2018 ዓ.ም አመሻሽ ላይ ጥቃቱ ድንገት ሲፈጸም የአካባቢው የመንግሥት ታጣቂዎች ምላሽ ቢሰጡም ጥቃቱን መመከት አልቻሉም። የአካባቢው የፖሊስ አዛዥን ጨምሮ በርካታ ፖሊሶች በጥቃቱ ተገድለዋል። ታጣቂዎቹ መኖሪያ ቤቶችን በእሳት በማያያዝ ከፍተኛ ውድመት ፈጽመዋል።
በደቡብ ሱዳን የሚገኘው የመንግሥታቱ ድርጅት ወኪል ጥቃቱን ተከትሎ አንድ ሺህ የሚደርሱ ሰዎች ከለላ ፍለጋ ወደ ጣቢያቸው መሄዳቸውን ገልጿል። እንደዚህ ዓይነት ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችልም ከ48 ሰዓት በፊት ማስጠንቀቂያ ደርሶት እንደነበር የድርጅቱ ወኪል ገልጿል።
በደቡብ ሱዳን የመንግሥታቱ ድርጅት ወኪል አኒታ ኪኪ ግቤሆ "እንደዚህ ዓይነት ጥቃቶች ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማ ስለሚያደርጉ በፍጥነት መቆም አለባቸው" ብለዋል።
አክለውም ጥቃት የደረሰባቸውን የማኅበረሰብ ክፍሎች ለመከላከል እና መልሶ ለማቋቋም ከደቡብ ሱዳን መንግሥት ጋር እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት ወኪል ሁለቱም አካላት ወዲያውኑ ግጭት እንዲያቆሙ እና ወደ ንግግር እንዲገቡ ጥሪ አቅርበዋል። ከቆሰሉት የተወሰኑ ሰዎችንም ሕክምና እየሰጠ መሆኑን የመንግሥታቱ ድርጅት ወኪል ገልጿል።
በተፈጠረው የጸጥታ ስጋት እና በደረሰው ከፍተኛ ጥቃት ሳቢያ ሟቾች በጅምላ መቀበራቸውን ኤኤፍፒ እና የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ተከታታይነት ባለው ግጭት ምክንያት ጆንግሌይ በሚባለው ሌላ ግዛት የድንበር የለሽ የሕክምና ቡድን በጎ አድራጎት ድርጅት 26 ሰራተኞቹ መጥፋታቸውን ገልጿል። የበጎ አድራጎት ድርጅቱ በግዛቷ ሁለት ቀጠናዎች እርዳታ ማቆሙን አስታውቋል። ጥር ወር መጀመሪያ አንደኛው የሕክምና መስጫ ጣቢያው በመንግሥት የጦር ጀት ጥቃት እንደተፈጸመበትም ገልጿል።
በ2003 ዓ.ም ነጻነቷን ያወጀችው ደቡብ ሱዳን፣ በእርስበርስ ጦርነት፣ በሙስና እና በድህነት በተደጋጋሚ እየተፈተነች ትገኛለች።
የመንግሥታቱ ድርጅት በፈረንጆቹ 2018 በፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር እና በምክትላቸው ሬክ ማቸር የተደረሰው የሥልጣን መጋራት ስምምነት በመጣሱ በአገሪቱ የርስ በርስ ጦርነት ሊያገርሽ ይችላል በማለት አስጠንቅቋል።