የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ትራምፕ ኢራን ላይ የወሰዱትን እርምጃ ተችተው የአገራቸውን አቋም ተከላከሉ

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር ለፓርላማ አባላት መንግሥታቸው "በጥቃት የሚመጣ የመንግሥት ለውጥን አያምንም" ሲሉ ተናገሩ።

ይህም ከእስራኤል ጋር በመሆን ኢራን ላይ ጥቃት ከከፈቱት ትራምፕ በተቃራኒ እንዲቆሙ ያደርጋቸዋል።

የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢራን ላይ ጥቃት ከተፈጸመ ወዲህ ባደረጉት የመጀመርያ የፓርላማ ንግግራቸው፣ አሜሪካ የዩኬን ጦር ሠፈር እንድትጠቀም መፍቀዳቸው ተገቢ እንደነበር በመግለጽ ተከላክለዋል።

"ከፕሬዚዳንት ትራምፕ ጋር በመጀመሪያ ጥቃቶች ላይ ላለመሳተፍ በመወሰናችን አልተግባብንም ነበር፤ ነገር ግን የብሪታኒያ ብሔራዊ ጥቅም ምን እንደሆነ የመወሰን የእኔ ኃላፊነት ነው" ሲሉ ለፓርላማ አባላት ተናግረዋል።

ነገር ግን እሁድ ዕለት ሁኔታዎች ተቀየሩ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የኢራን "ተገቢ ያልሆነ" ምላሽ "ለሕዝባችን እና ለፍላጎታችን እንዲሁም ለአጋሮቻችን ስጋት ሆነ" ሲሉ ተናግረዋል።

ኢራን ለአሜሪካ እና ለእስራኤል ጥቃቶች የወሰደችው የበቀል እርምጃ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ የብሪታኒያ ሕዝቦች ስጋት ላይ ጥሏል፤ ይህም የቴህራንን የሚሳዔል መሠረተ ልማት ለመምታት የጦር ሠፈሮቻችን ጥቅም ላይ እንዲውሉ እንድንፈቅድ አድርጓል ብለዋል።

በተጨማሪም በቆጵሮስ በሚገኘው የዩኬ አክሮቲሪ ላይ የተፈጸመውን የድሮን ጥቃት ጠቅሰዋል ፤ ይህንንም ጥቃት "በአሜሪካ የጦር አውሮፕላኖች ጥቅም ላይ አልዋለም" ብለዋል።

ቅዳሜ ዕለት [21/06/2018 ዓ.ም] አሜሪካ እና እስራኤል ኢራንን በማጥቃት የአገሪቱን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒን ገድለዋል።

ኢራን በአካባቢው ሚሳዔሎችንና ድሮኖችን በመተኮስ ምላሽ ሰጥታለች፤ ይህም እስራኤልን፣ ባህሬንን፣ ኩዌትን፣ ኳታርን፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስንና ሳዑዲ አረቢያን እንዲሁም በሆርሙዝ የባህር ሰርጥ የሚያልፉ መርከቦችን ጨምሮ ዒላማ አድርጓል።

አሜሪካ በሕንድ ውቅያኖስ የሚገኘውን የዲያጎ ጋርሲያ ጦር ሰፈር እና በግላስተርሻየር የሚገኘውን የራፍ ፌርፎርድ ጦር ሰፈር እንድትጠቀም ብትጠይቅም፣ ሰር ኪር ውሳኔያቸው ታሪክን መሠረት ያደረገ እንደሆነ ለፓርላማ አባላት በመግለጽ "ሁላችንም ኢራቅ ላይ የተሰራውን ስህተት እናስታውሳለን" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እስራኤል እና አሜሪካ በኢራን ላይ በጋራ የከፈቱትን ዘመቻ "የማጥቃት ዘመቻዎች" ብለው የጠሯቸው ሲሆን፣ ነገር ግን በኋላ ላይ የብሪታኒያ ወታደራዊ ሰፈሮች የኢራን የሚሳኤል ጣቢያዎች ላይ "የመከላከያ" ጥቃቶችን ለመፈጸም እንዲውሉ መስማማታቸውን ተናግረዋል።

ሰር ኪር ለፓርላማ አባላት "ግልጽ ለመሆን የብሪታኒያ ጦር ሰፈሮች አጠቃቀም ላይ የተስማማነው ውስን ለሆነ የመከላከል ዓላማ ብቻ ነው፤ እኛ የአሜሪካንና የእስራኤልን የማጥቃት ዘመቻዎች አንቀላቀልም" ብለዋል።

አክለውም "ታሪክ እንደዚህ ዓይነት ውሳኔዎችን ስናደርግ ዩናይትድ ኪንግደም እያደረገች ላለው ነገር ሕጋዊ መሠረት መኖሩን ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን አስተምሮናል።"

"ይህ ከኢራቅ ከወሰድናቸው ትምህርቶች አንዱ ነው፤ እና ሊደረስበት የሚችል ወይም ሊሳካ የሚችል ዓላማ ያለው ተግባራዊ የአስተሳሰብ እቅድ መኖሩ ነው።"

"ይህ መርህ ቅዳሜና እሁድ ባደረግኳቸው ውሳኔዎች ላይ ተግባራዊ ያደረግኩት ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር፣ "ይህ መንግሥት በጥቃት በሚመጣው የአገዛዝ ለውጥ አያምንም" ብለዋል።