ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሱዳን ከኢትዮጵያ የሚነሱ ድሮኖች ድንበሯን ጥሰው እየገቡ መሆናቸውን በመግለጽ ከሰሰች
ሱዳን ከኢትዮጵያ የሚነሱ ድሮኖች ወደ ግዛቷ ዘልቀው በመግባት ጥቃት እየፈጸሙ መሆኑን እና ይህም በሉዓላዊነቷ ላይ የተፈጸመ "ግልጽ ጥሰት" እንዲሁም "የጠብ ጫሪነት ድርጊት" ነው ስትል ከሰሰች።
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰኞ የካቲት 22 2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በአውሮፓውያኑ የካቲት እና ጥር ወር መጀመሪያ ቀናት ከኢትዮጵያ ግዛት የሚነሱ ድሮኖች ወደ ግዛቱ መግባታቸውን ሲከታትል እንደነበር አመልክቷል።
ጨምሮም ድሮኖቹ በሱዳን ውስጥ የሚገኙ ቦታዎችን ዒላማ አድርገው ጥቃት መፈጸማቸውን ገልጿል፤ ነገር ግን ጥቃት ስለተፈጸመባቸው ቦታዎች እና ስለደረሰ ጉዳት ምንም ዓይነት ዝርዝር ማብራሪያ አልሰጠም።
የሱዳን መንግሥት ከኢትዮጵያ በኩል ተፈጽሟል ያለውን የድሮን ጥሰት "ግድየለሽ እና ተቀባይነት የሌለው ድርጊት" በማለት ሌላ መዘዝ ሊያስከትል እንደሚችል አስጠንቅቋል።
በአረብኛ የተሠራጨው የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ይህ ድርጊት የሚቀጥል ከሆነ ሉዓላዊነቱን እና የግዛት አንድነቱን ለመከላከል መብቱ እንዳለው እንዲሁም "በተለያዩ መንገዶች" ምላሽ የሚሰጥበት አቅም እንዳለው ገልጿል።
ቢቢሲ ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቀረበው ክስ ላይ ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም።
በሱዳን ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል በሚካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ በአል ቡርሐን የሚመራው ጦር ሠራዊት ተቀናቃኙን በመርዳት ይከስሳታል።
በኢትዮጵያ መንግሥት በኩልም በተለያዩ ጊዜያት ከሱዳን የጦር መሳሪያዎች እና ታጣቂዎች ወደ ግዛቱ እንደሚገቡ በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል።
ባለፈው ወር ሮይተርስ የዜና ወኪል ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር በሚያዋስናት ግዛቷ ውስጥ የፈጥኖ ደራሹ ኃይል ተዋጊዎች የሚሠለጥኑበት ካምፕ እንዳለ የተለያዩ ምንጮች እና የሳተላይት ምሥሎችን በማስረጃነት በመጠቀም ዘገባ ማቅረቡ ይታወሳል።
ይህንንም በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት እስካሁን ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ አልሰጠም።
በሱዳን በሚካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የተለያዩ ኢትዮጵያን ጨምሮ አገራት አንደኛውን ወገን እንደሚደግፉ የተለያዩ ዘገባዎች ቢወጡም ሁሉም አገራት ሲያስተባብሉ ቆይተዋል።
በተለይ የኢትዮጵያ የቅርብ ወዳጅ የሆነችው ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ በግብፅ የሚደገፈውን የሱዳን ጦር ሠራዊትን እየተዋጋ የሚገኘውን በሐምዳን ዳጋሎ የሚመራውን የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይልን ትደግፋለች በሚል በዋናነት ትከሰሳለች።
በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ምክንያት ከግብፅ ጎን በመቆም ኢትዮጵያን የሚቃወመው የሱዳን ጦር ኃይል መሪ ጄኔራል አል ቡርሐን ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ግንኙነት መቀዛቀዙ ሲነገር ቆይቷል።
ሱዳን እና ግብፅ ኢትዮጵያ ገንብታ ያጠናቀቀችው በአፍሪካ ትልቁ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ወደ ግዛታቸው የሚደርሰውን የአባይ ውሃ መጠን ይቀንሳል በሚል ስጋት የግድቡን ሥራ በሚመለከት ኢትዮጵያ አስገዳጅ ስምምነት እንድትፈርም እየወተወቱ ነው።
ኢትዮጵያ ግን ግድቡ የወንዙን የውሃ ፍሰት የማይገታ መሆኑን በመጥቀስ ሁለቱ አገራት የሚያቀርቡትን ሃሳብ ውድቅ አድርጋለዋለች።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ እና ሱዳን ለእርሻ ለም በሆነው የአል ፋሽጋ አካባቢ ይገባኝል ምክንያት ለዓመታት የቆየ አለመግባባት እንዳላቸው ይታወቃል።