የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ ለሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መሣሪያ ታቀርባለች መባሉን አስተባበለች

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ለሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) የተለያዩ ድጋፎች ታደርጋለች መባሉን አስተባበለች።

ኤምሬትስ ለሱዳን ፈጣን ደራሽ ኃይል የጦር መሣሪያ እና ወታደራዊ ቁሳቁሶችን በገንዘብ ትደግፋለች እንዲሁም ታጓጉዛለች በሚል የቀረበባትን ውንጀላ ውድቅ አድርጋለች።

ሮይተርስ ማክሰኞ የካቲት 3/2018 ዓ.ም. ባወጣው የምርመራ ዘገባ ኤምሬትስ ለፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ወታደራዊ ሥልጠናዎችን እና ጦር ቁሳቁሶችን በመስጠት ድጋፍ ታደርጋለች ብሎ ነበር።

ይህንን ተከትሎ የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ለቢቢሲ በሰጠችው ምላሽ "ማንኛውንም የጦር መሳሪያ፣ ጥይት፣ ሰው አልባ አውሮፕላኖች፣ ተሸከርካሪዎች፣ ዒላማቸውን ለይተው የሚመቱ ተተኳሾች ወይም ሌሎች ወታደራዊ ቁሳቁሶችን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለአርኤስኤፍ አላቀረበኩምም" በማለት አስተባብለች።

በዚሁ መግለጫ ላይ የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ በሱዳን ግጭት ውስጥ ተሳታፊ እንዳልሆነች እና በግጭት ውስጥ እንደማትሳተፍም ገልጻለች።

መግለጫው አክሎም "የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ መሠረተ ቢስ እና በመሬት ላይ ያለውን እውነታ ወይም የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶችን የረጅም ጊዜ እና ግልፅ አቋም የማያንፀባርቁ ክሶችን ሙሉ በሙሉ ውድቅ ታደርጋለች" ብሏል።

የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት የጀመረው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በሚያዝያ 2023 በአገሪቱ ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል የሥልጣን ሽኩቻ መቀስቀሱን ተከትሎ ነው።

ጦርነቱ የተቀሰቀሰው የሱዳን ጦር አዛዥ ጄነራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን በወቅቱ ምክትላቸው ከነበሩት የአርኤስኤፍ አዛዥ ጄነራል መሐመድ ሀምዳን ዳጋሎ ጋር ባለመገባባታቸው የተነሳ ነው።

ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በሁለቱ የጦር መሪዎች መካከል አገሪቱን ለመቆጣጠር ከሦስት ዓመት በላይ የዘለቀ ፍልሚያ እየተካሄደ ይገኛል።

በዩናይትድ ስቴትስ እና በሳዑዲ አረቢያ የተመሩ ዓለም አቀፍ የድርድር ጥረቶች እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት እና የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ያደረጓቸው የማግባባት ጥረቶች ዘላቂ የሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት ማምጣት አልቻሉም።

የተባበሩት መንግሥታት በሱዳን እየተካሄደ ያለው የእርስ በርስ ጦርነት በዓለም አስከፊ የሆነ ሰብዓዊ ቀውስ ማስከተሉን ገልጿል።

እንደ መንግሥታት ድርጅት እና የሰብዓዊ እርዳታ ኤጀንሲዎች ዘገባ ከሆነ ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል።

ወደ 14 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለው ወደ ተለያዩ የጎረቤት አገራት ሸሽተዋል።

ጦርነቱ ሰፊውን የሱዳንን ክፍል ወደ ረሃብ መግፋቱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።

አክሎም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለከፋ የምግብ ዋስትና እጦት እንደሚዳረጉ ያስጠነቀቀ ሲሆን፣ የጤና እና የእርዳታ አቅርቦቶች በግጭት ወደተጠቁ አካባቢዎች መድረስ ሳይችሉ መቅረታቸውን ገልጿል።

የአርኤስኤፍ እና የሱዳን ጦር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በዩናይትድ ስቴትስ እና በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት፣ ማንነት ተኮር ግድያ እና ሰፊ ፆታዊ ጥቃትን ጨምሮ ከባድ የሰብአዊ መብት ረገጣዎችን በማድረስ ክስ ቀርቦባቸዋል።

በሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ላይ ዓለም አቀፍ ጫናዎች እየተባባሱ ቢሄዱም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ጦርነቱ እንደቀጠለ ነው።

የተለያዩ አካላት ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ኃይሎች በግጭቱ ውስጥ ተቀናቃኝ ወገኖችን ይደግፋሉ በሚል ይወነጅላሉ።