ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር የሩሲያን ነዳጅ መግዛት ለማቆም መስማማታቸውን ትራምፕ ተናገሩ
የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ የሩሲያን ነዳጅ ላለመግዛት መስማማታቸውን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ።
አሜሪካ የዩክሬንን ጦርነት ለማስቆም የሚደረጉት ጥረቶች አካል በማድረግ በክሬሚሊን ላይ የኢኮኖሚ ጫናዎችን ማሳደር ትፈልጋለች።
ትራምፕ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ ሕንድ "በአጭር ጊዜ ውስጥ" ከሩሲያ ነዳጅ መግዛት እንደምታቆም ከሞዲ ማረጋገጫ ማግኘታቸውን እና ይህም 'ትልቅ እቀባ' መሆኑን ገልጸዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚደንት ሕንድ ከሩሲያ ነዳጅ መግዛቷን ለማስቆም ቢፈልጉም፤ደልሒ ግን እስካሁን ይህንን ሳትቀበል ቆይታለች።
የአገሪቷ መንግሥት ቃል አቀባይ ለትራምፕ ንግግር በሰጡት ምላሽም " ከሕንድ ጋር የኢነርጂ ትብብሩን ለማጠናከር ፍላጎት ካሳየው የአሜሪካ አስተዳደር ጋር ውይይቶች እየተካሄዱ ነው" ብለዋል።
"በዋናነት ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ በሚለዋወጠው የኢነርጅ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙትን የሕንድ ሸማቾችን ፍላጎት መጠበቅ ነው" ያሉት ቃል አቀባዩ፣ የገቢ ንግድ ፖሊሲያቸውም በዚህ ዓላማ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ገልጸዋል።
ሩሲያ ወደ ውጭ ከምትልካቸው ምርቶች መካከል ነዳጅ ዘይት እና ጋዝ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዙ ሲሆን ከዋና ደንበኞቿ መካከል ቻይና፣ ሕንድ እና ቱርክ ይጠቀሳሉ።
ትራምፕ በኦቫል ቢሮ ረቡዕ ዕለት እንደተናገሩት አስተዳደራቸው የሞስኮን የኃይል ድጋፍ ለመቁረጥ በሚያደርገው ሰፊ ግፊት ቻይናም ተመሳሳይ እርምጃ እንድትወስድ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።
ጃፓንም ከሩሲያ ነዳጅ እና ጋዝ ማስገባቷን እንድታቆም የትራምፕ አስተዳደር ግፊት እያደረገ ነው።
የአሜሪካ የግምዣ ቤት ኃላፊ ስኮት ቢሰንት እንዳሉት በጉዳዩ ላይ ረቡዕ ዕለት ከጃፓኑ የፋይናንስ ሚኒስትር ካትሱኖቡ ካቶ ጋር መነጋገራቸውን ገልጸዋል።
ሕንድ የነዳጅ ግዥዋን ወዲያውኑ ማቆም አትችልም ያሉት ትራምፕ፣ "እርምጃው የተወሰኑ ሒደቶችን ይፈልጋል፤ ሆኖም በቅርቡ ያበቃል" ብለዋል።
የትራምፕ አስተዳደር ሕንድ ከሩሲያ ነዳጅ እና የጦር መሣሪያ በመግዛቷ ምክንያት በምርቶቿ ላይ የ50 በመቶ ቀረጥ ጥሏል።
ባለፈው ነሐሴ ወር ላይ ተግባራዊ የሆነው ቀረጥ፣ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት ወሳኝ የገንዘብ ምንጭ ነው በተባለው ግብይቷ ምክንያት የተጣለባትን የ25 በመቶ ቅጣት ጨምሮ በዓለም አገራት ላይ ከተጣለው ከፍተኛው ነው።
ሞዲ አገራቸው ምንም እንኳን ከሩሲያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ግንኙነት ቢኖራትም በሁለቱ አገራት ጦርነት አገራቸው ገለልተኛ መሆኗን በመግለጽ በአቋማቸው ፀንተው ቆይተዋል።
የሕንድ ባለሥልጣናት የትራምፕ አስተዳደር ሩሲያ በዩክሬን በምታካሂደው ጦርነት ደልሒ ጥቅም እያገኘች ነው ሲል ያቀረበውን ክስም ሚዛናዊ ያልሆነ ብለውታል። ለዚህም ባለሥልጣናቱ አሜሪካ እና አውሮፓ ከሩሲያ ጋር እያካሄዱት ያለውን የንግድ ግንኙነትም ጠቅሰዋል።
ሕንድ በሩሲያ ድፍድፍ ነዳጅ ላይ ጥገና ስትሆን በዓለም በአምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ግዙፍ ኢኮኖሚዋን ለመደገፍ በቅናሽ ዋጋ ግዥ መፈፀሟን ቀጥላለች።
በሩሲያ ነዳጅ ላይ የተፈጠረው ውዝግብም ምንም እንኳን ትራምፕ ረቡዕ ዕለት የሕንዱን መሪ "ታላቅ ሰው" ሲሉ ቢያወድሱም በትራምፕ እና በሞዲ መካከል ያለውን ግንኙነት ውጥረት ውስጥ ከቶታል።
ሞዲ ባለፈው ሳምንት ከትራምፕ ጋር መነጋገራቸውን ገልጸው በንግድ ድርድር ላይ የተገኙ ውጤቶችን መገምገማቸውን ተናግረው ነበር።