ደቡብ ኮሪያዊው ፖለቲከኛ እራሳቸውን የሚያጠፉ ወንዶች የመጨመር ምክንያቱ ሴቶች ናቸው አሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ደቡብ ኮሪያዊው ፖለቲከኛ እራሳቸውን የሚያጠፉ ወንዶች ቁጥር የጨመረው ሴቶች በማኅብረሰቡ ውስጥ የበላይነትን እየያዙ በመምጣታቸው ነው አሉ።
የመዲናዋ ሴኡል ምክር ቤት አባል የሆኑት ኪም ኪ-ዳክ በሰጡት መረጃ ላይ ያልተደገፈ አስተያየት ከፍተኛ ትችት እየገጠማቸው ይገኛል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደቡብ ኮሪያ እራሳቸውን የሚያጠፉ ወንዶች ቁጥር ጭማሪ አሳይቷል።
ፖለቲከኛው በስራ መስክ የሚሳተፉ ሴቶች ቁጥር በመጨመሩ ወንዶች ስራ ማግኘት እና ሊያገቧቸው ፍቃደኛ የሆኑ ሴቶችን እያገኙ ስላልሆነ እራሳቸውን እያጠፉ ነው ሲሉ ተሰምተዋል።
ኪም ኪ-ዳክ አገራቸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሴቶች የበላይነት ወዳለበት ማኅብረሰብ እየተቀየረች ነው ካሉ በኋላ ይህ ወንዶች እራሳቸውን ከሚያጠፉባቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ ሊሆን ይችላል ብለዋል።
ደቡብ ኮሪያ ከለጸጉ አገራት እራሳቸውን የሚያጠፉ በርካታ ሰዎች የሚገኙባት አገር ናት። ነገር ግን ሰልጥነዋል ከሚባሉ አገራት ደግሞ የጾታ እኩልነት የሌለባት አገር ናት።
ይህ ፖለቲከኛ በደቡብ ኮሪያ ብዙ እያነጋገር ያለውን አስተያየት የሰጡት በመዲናዋ በሚገኘው ሃን ወንዝ ላይ ካለው ድልድይ እራሳቸውን እየወረወሩ የሚገድሉ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ ነው።
የከተማ አስተዳደር ባወጣው ሪፖርት እአአ 2018 ላይ ከድልድዩ ላይ እራሳቸውን ለማጥፋት የሞከሩ ሰዎች ቁጥር 430 ነበር። ይህ አሃዝ በ2023 በ77 በመቶ ጨምሮ 1035 ደርሷል።
በሶል ዮንሲ ዩኒቨርሲቲ የአእምሮ ጤና መምህር የሆኑት ሶንግ ኢን ሃን “መረጃ ላይ ሳይመሰረቱ መሰል አስተያየት መስጠት አደገኛ እና ብልህነት የሌለበት ነው” ብለዋል።
እንደ መምህሩ ከሆነ በመላው ዓለም ከሴቶች ይልቅ እራሳቸውን የሚያጠፉት ወንዶች ቁጥር ይበልጣል።
ሶንግ ኢን ሃን በበርካታ አገራት ዕድሜያቸው ከ50 በታች ለሆኑ ወንዶች ቀዳሚው የሞት ምክንያት እራሳን ማጥፋት ነው ይላሉ።
መምህሩ በደቡብ ኮሪያ እራሳቸውን የሚያጠፉ ወንዶች ቁጥር የመጨመሩ ምክንያት ለማወቅ ሳይንሳዊ የሆነ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።












