'ምትሃተኛው ተወልዷል!' ላሚን ያማል ማን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በእግር ኳስ ጨዋታ የሚቆጠር የትኛውም ጎሎ ይብዛም ይነስም ትርጉም አለው።
ይሁን እንጂ ከጎልም ግን ጎል አለው። ልዩ የሆኑ ጎሎች አሉ። የጨዋታ እና የውድድሮችን ቅርጽ የሚቀይሩ ልዩ ጎሎች ሁሌም ይታወሳሉ። ተደጋግመው ይታያሉ።
የትናንት ምሽቷ የያሚል ጎል ለአስርት ዓመታት መነጋገሪያ ሆና ትቀጥላለች።
ላሚን ያማል አገሩ ስፔን በዩሮ 24 ፈረንሳይ ላይ የበላይነትን እንድትጎናጸፍ ያስቆጠራት አስደናቂ ጎል ለታሪክ የምትቀመጥ ናት ያለው በአሊያንዝ አሬና ጨዋታውን የተከታተለው ጌሪ ሮስ ነው።
ስፔን 1 ለ 0 እየተመራች ሳለ ላሚን በጥበበኛው ግራ እግሩ ከሳጥኑ ውጪ ጠቅልሎ ያስቆጠራት ጎል ድንቅ ከመሆኗ በተጨማሪ ለአገሩ አቻ ያደረገች እጅግ ወሳኝ ጎል ነበረች።
ይህ ጎል ሲያስቆጥር 16 ዓመት ከ 362 ቀናት ላይ እያለ በመሆኑ በአውሮፓ ዋንጫ ታሪክ በዕድሜ ትንሹ ጎል አስቆጣሪ ሆኖም በታሪክ ተመዝግቧል።
ያማል ይህችን ጎል ሲያስቆጥር የቀድሞ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አጥቂ ጋሪ ሊኒከር “ምትሃተኛ ተወልዷል። . . . ይህ የውድድሩን አካሄደ የቀየር አጋጣሚ ነው” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።
“ጨርሶ ማመን የማይቻል። በዚህ ትንሽ ዕድሜው ይህን ማድረግ መቻል የማይታመን ነው” ያለው ደግሞ አለን ሽረር ነው።
ስፔናዊው ላሚን ያማል በአውሮፓ ዋንጫ ተሰልፎ የተጫወተ በዕድሜ ትንሹ ተጫዋች በመሆነ ሌላ ክብረ ወሰን ሰብሯል።
ላሚን ያማል በብሔራዊ ቡድን ብቻ ሳይሆን በክለብ ደረጃም በትንሽ ዕድሜው ብዙ ክብረ ወሰኖችን ይዟል።
ያማል ለክለቡ ባርሴሎና በትንሽ ዕድሜው ጎል ያስቆጠረ ተጫዋች ነው። ከዚህ በተጨማሪ በትንሽ ዕድሜው በቻምፒየንስ ሊግ ግጥሚያ ተሰልፎ የተጫዋተ፣ በላ ሊጋ እና ኮፓ ዴላሬ ጎል ያስቆጠረ ተጫዋች ነው።
ከትናንት ምሽቱ ጨዋታ በኋላ በእርሱ ዕድሜ ያሉ አብዛኛዎቹ ታዳጊዎች በሚተኙበት ሰዓት ያማል በሰጠው አስተያየት፤ “ከቡድኑ ጋር ለፍጻሜ መድረስ ሰመኘው የነበረው እውነት ሆኗል” ብሏል።
ላሚን ያማል ማን ነው?
ይህ የክንፍ ተጫዋች ሙሉ የመዝገብ ስሙ ላሚን ያማል ናስራዊ ኤባና ይባላል።
ከሞሮኳዊ አባቱ እና ከኢኳቶሪያል ጊኒ እናቱ በስፔን ተወልዷል። ቅዳሜ ሐምሌ 6/2016 ዓ.ም. 17 ዓመት የሚደፍነው ያማል፤ ከባርሴሎና የእግር ኳስ ክለብ ጋር የፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ሕይወቱን የጀመረው ገና የአምስት ዓመት ታዳጊ ሳለ ነበር።
ያማል ተወልዶ ያደገው በባርሴሎናዋ የድሆች ሰፍር በሆነችው ሮካፎንዳ 304 በሚባል ሰፈር ነው።
ጎሎችን ካስቆጠረ በኋላም በጣቶቹ 304 በመስራት ደስታውን ይገልጻል።
ተጫዋቹ የቀኝ እጁን ሦስት ጣቶች በመዘርጋት 3፣ አውራ ጣቱን እና ጠቋሚ ጣቱን በማገጣጠም 0 እንዲሁም የእግራ እጁ አራት ጣቶች በመጠቀም 4 ቁጥርን ያመላክታል።
ያማል ገና ከአሁኑ ለበርካታ ለሮካፎንዳ ጨቅላዎች የስፋ ምልክት ሆኗል።
ያማል በእግር ኳስ ፍቅር የወደቀው ወላጅ አባቱ እና የቅርብ ዘመዶቹ በዛረ የድሆች ሰፈር በኮንክሪት ግንብ ውስጥ ኳስ ሲጫወቱ ከተመለከተ በኋላ ነው።
“ከቤት ይለቅ አብዛኛውን ጊዜያን የማሳልፈው ኳስ በመጫወት ነው። ከቤት ውጪ ነኝ ማለት ሁሌም ኳስ እየተጫወትኩ ነው ማለት ነው። የኳስ ፍቅር ሁሌም አብሮ የሚኖር ነገር” በማለት ያማል ይናገራል።












