የኢዚጄት አውሮፕላን በቦምብ ስጋት የበረራ አቅጣጫን ቀየረ

ከፖላንድ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም እየተጓዘ የነበረ አንድ የኢዚጄት አውሮፕላን የቦምብ ጥቃት ስጋት ገብቶት ወደ ቼክ ሪፐብሊክ ከተማ ፕራግ አቅጣጫ ለመቀየር ተገደደ።

ከፖላንድ ክራኮቭ ከተማ ወደ እንግሊዝ በሪስትል ከተማ እየበረረ የነበረው አውሮፕላን ነው እሑድ ፕራግ አየር ማረፊያ ለማረፍ የተገደደው።

የቼክ ሪፐብሊክ ፖሊስ አውሮፕላኑ ባረፈበት ቅጽበት ምርመራ ለማድረግ ከስፍራው ተገኝቷል።

የፕራግ አየር መንገድ በኋላ ላይ በትዊተር ገጹ “ምርመራ ከተደረገ በኋላ ምንም ዓይነት የቦምብ ምልክት አልተገኘም" ብሏል።

የበረራ ቁጥር EZY6276 ኢዚጄት ከሁለት ሰዓት በረራው ውስጥ አንድ ሰዓቱን አገባዶ ነበር፣ በፕራግ ቫክላቭ ሐቨል አየር ጣቢያ ተገዶ ሲያርፍ።

የፕራግ አየር ጣቢያ በይፋ እንዳለው 22፡50 ላይ አውሮፕላኑ በሰላም አርፏል።

በአውሮፕላኑ ውስጥ ቦምብ ተጠምዷል የሚል መረጃ እንዴት እንደተገኘ ኢዚጄት ከቢቢሲ ማብራሪያ ተጠይቆ ያለው ነገር የለም።