ኢራን ለእስራኤል ሰልለዋል ያለቻቸውን አራት ዜጎች በስቅላት ቀጣች

ኢራን ከእስራኤል የስለላ ድርጅት ጋር ተመሳጥራችኋል ያለቻቸውን አራት ዜጎች በስቅላት ቀጣች።

የኢራን መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት የኢራን ዜግነት ያላቸው አራቱ ወንዶች በሞት የተቀጡት ትናንት እሑድ ነው።

የኢራን ፍርድ ቤት በአራት ሰዎች ላይ የሞት ቅጣቱን ያጸናው ባለፈው ረቡዕ ነበር።

አራቱ ዜጎች በቁጥጥር ሥር የዋሉት ደግሞ ባለፈው ግንቦት ወር ነበር።

ይህ የሞት ቅጣት ተፈጻሚ የሆነበት ወቅት በኢራን ላለፉት አራት ወራት የተደረገውን ጸረ መንግሥት ተቃውሞ ተከትሎ ነው።

ከአራቱ ዜጎች ስቅላት ሌላ ሌሎች ሦስት ዜጎች ከአምስት እስከ አሥር ዓመት እስራት ተፈርዶባቸዋል።

ሦስቱ ዜጎች የተከሰሱት ዜጎችን በማፈን ተግባር ተባባሪ በመሆናቸው፣ ፍቃድ የሌለው የጦር መሣሪያ በመያዝ እና ሌሎች የደኅንነት ደንቦችን በመጣሳቸው እንደሆነ የአገሬው ራዲዮ ዘግቧል።

እስራኤል ከሌሎች አካባቢው ካሉ አረብ አገራት ጋር ግንኙነቷን አሻሽላለች። ይሁንና ከኢራን ጋር አሁንም ደመኛ ጠላቶች ናቸው።

በገሀድ ጦርነት ባያካሄዱም በስለላው ዓለም አንዳቸው ለሌላቸው ተኝተው አያውቁም።

ሰዎችን በማፈን በሚል ክስ ተመሥርቶባቸው የእስር ብይን ከተላለፈባቸው መሀል አንዱ የእሰራኤል ሚዲያ ከወር በፊት የኢስላሚክ አብዮታዊ ዘብ አባል ነኝ የሚል ሰውን አቅርበው የእስራኤል ዲፕሎማቶችን በአውሮፓ የመግደል ሴራ እንደነበረ ከተናዘዘበት ጉዳይ ጋር የተያያዘ ነው።

ኢራን ይህ ሰው ተራ ገበሬ ነው፤ አንድ ‘ወሮበላ ቡድን’ እንደ አውሮፓዊያኑ በ2021 ካገተው በኋላ ያንን እንዲል አስገድደውት ነው ትላለች።

ኢራን አሁን በአገሯ የተቀሰቀሰውን ከፍተኛ አመጽ በማቀጣጠል አሜሪካና እስራኤልን ትከሳለች።

አመጹ የተቀሰቀሰው የሞራል ፖሊስ በሴቶች ላይ እየፈጸመ ያለውን ተግባር በመቃወም ነው።

በቅርብ ጊዜ በኢራን ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ዘለግ ላለ ጊዜ የሰነበተው ይህ አመጽ በመላ አገሪቱ ተስፋፍቶ ቆይቷል።

የኢራን ፍርድ ቤት ከአመጹ ጋር በተያያዘ 6 ሰዎች ላይ የሞት ቅጣት ውሳኔን አጽንቷል።

አምነስቲ በበኩሉ 21 የሚሆኑ ሰዎች በስቅላት ሊቀጡ ይችላሉ ሲል ስጋቱን ገልጧል።

የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉት ኢራን በዓለም ከቻይና በስተቀር የትኛውም አገር በስቅላት ቅጣት ተጸፋሚ በማድረግ የሚስተካከላት የለም።