አሜሪካ ኤርትራን ጨምሮ 12 አገራት በሃይማኖት ነጻነት አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ናቸው አለች

አሜሪካ ኤርትራን ጨምሮ አስራ ሁለት አገራት ከእምነት ነጻነት አንጻር ባላቸው አያያዝ የተነሳ በአሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ናቸው ስትል ፈረጀች።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንክን በመሥሪያ ቤታቸው በኩል ባወጡት መግለጫ እንዳመለከቱት፣ ዓለም አቀፍ የሃይማኖት ነጻነት ደንብን የሚጻረሩ ድርጊቶችን ይፈጽማሉ ያለቻቸውን አገራት በመለየት አሜሪካ ስጋት እንዳላት ገልጸዋል።

በዝርዝሩ ውስጥ የተካተተችው ኤርትራ የእምነት ነጻነትን በመገደብ በተደጋጋሚ በአሜሪካ እና በተለያዩ የመብት ቡድኖች ስትተች ቆይታለች።

በተለያዩ ጊዜያትም በኤርትራ ውስጥ ያሉ የሃይማኖት መሪዎችን እና ምዕመናኖቻቸው ለእስር እንደሚዳረጉ እንዲሁም፣ በስራቸው የሚተዳደሩ ተቋማት እንደሚዘጉ እና እንደሚወረሱ ሪፖርት መደረጉ ይታወሳል።

በወጣው መግለጫ ላይ ከእምነት ጋር ተያይዞ ጭቆናዎችን የሚፈጽሙ አገራት እና ከባድ የሃይማኖት ነጻነት መብት ጥሰትን የሚፈጽሙ አገራት ስም በዝርዝር ተጠቅሷል።

እንዲሁም ሃይማኖትን መሠረት አድርገው የትጥቅ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ቡድኖችንም የአሜሪካ መንግሥት በስጋት ዝርዝሩ ውስጥ አካቷቸዋል።

በዚህም መሠረት 12 አገራት የተጠቀሱ ሲሆን፣ ከአፍሪካ ኤርትራ በብቸኝነት በዝርዝሩ ውስጥ ተካታለች። በተጨማሪም በርማ፣ ቻይና፣ ኩባ፣ ኢራን፣ ኒካራጓ፣ ሰሜን ኮሪያ፣ ፓኪስታን፣ ሩሲያ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ታጂክስታን እና ቱርክሜንስታን የእምነት ነጻነትን በመገደብ ተጠቅሰዋል።

በኤርትራ በሃይማኖት ተቋማትና በተከታዮቻቸው ላይ ይደርሳል ከሚባለው የመብት ጥሰት በተጨማሪ፣ በአገሪቱ ውስጥ በእምነት ተቋምነት እንዲንቀሳቀሱ ተፈቀደላቸው ሃይማኖቶች የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን፣ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን፣ የሉተራን ቤተክርስቲያን እና የሱኒ አስልምና ናቸው።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት መግለጫው አሳሳቢ ናቸው ካላቸው አገራት በተጨማሪ የሃይማኖት ነጻነትን በመጣስ አልጄሪያን፣ የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክን፣ ኮሞሮስን እና ቬትናምን የተለየ ትኩረት በአሜሪካ መንግሥት እንደሚደረግባቸው አመልክቷል።

እንዲሁም ከእምነት ጋር የተያያዘ የትጥቅ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ቡድኖች የተለየ ስጋት መደቀናቸውን በመጥቀስ፣ የአሜሪካ መንግሥት የሶማሊያውን አልሻባብ፣ የናይጄሪያውን ቦኮ ሃራም፣ የሶሪያውን ሃያት ታህሪር አል-አልሻም፣ የየመኑን ሃውቲ፣ የሰሜን አፍሪካውን አይኤስ፣ የምዕራን አፍሪካውን አይኤስ፣ የማሊውን ጃማአት ኑስራት የተባሉት ቡድኖችን ብሊንከን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም የአሜሪካንን ኃይል ከአፍጋኒስታን በማስወጣት የመሪነት ሥልጣኑን የያዘው ታሊባን እና የሩሲያው የቅጥር ወታደራዊ ቡድን የሆነው ዋግነር ቡድን በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ውስጥ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ለሃይማኖት ነጻነት ስጋት ከደቀኑ ቡድኖች መካከል ተቀምጠዋል።

የውጭ ጉዳይ ኃላፊው እንዳሉት አሜሪካ በዓለም ዙሪያ የሃይማኖት ነጻነት እንዲከበር የምታደርገውን ክትትል የምትቀጥል መሆኑን በመግለጽ፣ የመብት ጥሰቱን ከሚፈጸሙ አገራት ጋር በሚደረግ ግንኙነት መሻሻሎች እንዲመጡ ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።