ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኤርትራ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳስን አሰረች
የካቶሊኩ ጳጳስ አቡነ ፍቅረማርያም ሀጐስ ዘመንበረ ሰገነይቲ ከአውሮፓ መልስ በኤርትራ መታሰራቸው ምንጮች ለቢቢሲ ተናገሩ።
ቅዳሜ ጥቅምት 5/2015 ዓ.ም. የኤርትራ የጸጥታ ኃይሎች የሰገነይቲ ግዛት ጳጳስ አቡነ ፍቅረማርያም ሀጐስን ከአሥመራ አየር ማረፊያ ወስደው እንዳሰሯቸው በኤርትራ እና ከኤርትራ ውጪ ያሉ ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
እስካሁን ድረስ የኤርትራ መንግሥት የጳጳሱን እስር የሚመለከት ምንም አይነት አስተያየት አልሰጠም።
ይሁን እንጂ የአቡነ ፍቅረማርያም እስርን ተከትሎ የኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተክስርቲያን የጻጻሱን መገኛ በተመለከተ ለሚመለከታቸውን የኤርትራ ኃላፊዎች ጥያቄ ካቀረቡ በኋላ የሃይማኖት አባቱን "ይዘናል" የሚል ምላሽ አግኝተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የኤርትራ መንግሥት የጸጥታ ኃይሎች አባ ምህረትአብ እስጢፋኖስ የተባሉ የሰገነይቲ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን አገረ ስብከት አስተባባሪን ባለፈው ማክሰኞ ማሰራቸውን የቢቢሲ ምንጮች አክለዋል።
ከቄሱ እስር በኋላ የሃይማኖት አባቱ የት እንደሚገኙ እና ስላሉበት ሁኔታ የኤርትራ መንግሥት ምንም አይነት መረጃ አልሰጠም። ቤተክርስቲያኒቱም እስካሁን ይህንን የተመለከተ መረጃ አልተሰጣትም።
ምንጮች አክለው እንደገለጹት የጸጥታ ኃይሎች ተሰነይ ከተማ ካፕቹኒ ማህበር ቄስ የሆኑትን አባ አብራሃምን አስረዋል።
የኤርትራ መንግሥት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳስን እና ቄሶችን ለምን በቁጥጥር ስር እንዳዋለ እስካሁን ድረስ የሚታወቅ ነገር የለም።
ይሁን እንጂ የካቶሊክ ጳጳሳቱ በኤርትራ የፖለቲካ ሪፎርም እንዲደረግ እና የመንግሥት የፈላጭ ቆራጭነት ባህሪ እንዲቀየር ጥሪ ማቅረባቸውን የሚያሳዩ ሪፖርቶች ወጥተዋል። ይህም የኤርትራ መንግሥትን ሳያስቆጣ አይቀርም ተብሏል።
የኤርትራ መንግሥት ከቅርብ ግዜ ወዲህ ጦር ኃይሉን አልቀላቀልም ያሉ ሰዎችን ለማደን የሚያደርገው እንቅስቃሴ መጨመሩ ተዘገቧል። ከዚህም በተጨማሪ በመላው ኤርትራ ያሉ ንግድ ቤቶች የመዝጋት ዘመቻ መደረጉንም ቢቢሲ መዘገቡ ይታወሳል።
አሥመራ ውስጥ የቤት ለቤት የሚደረግ አፈሳ ተጠናክሮ መቀጠሉን እና ይህም ነዋሪዎችን ስጋት ውስጥ መክተቱን አንድ ምንጭ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የኤርትራ ጦር ከፌደራል መንግሥቱ ጎን በመሰለፍ የትግራይ ኃይሎችን እየወጋ ይገኛል።
ከቅርብ ግዜ በኋላ በኤርትራዊያን ዘንድ አገራቸው በኢትዮጵያ ውስጥ ያላትን የወታደራዊ ተሳትፎ በሚመለከት የተቃውሞ ድምጾች እያሰሙ መጥተዋል።
እኤአ በ2019 የኤርትራ የስራ ኃላፊዎች የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የምታስተዳድራቸውን ትምህርት ቤቶች እና ሆስፒታሎች መዝጋቱ ይታወሳል።
ከኤርትራ ሕዝብ ውስጥ 4 በመቶ ያሕሉ የሮማን ካቶሊክ እምነት ተከታይ ነው። በኤርትራ ውስጥ እንዲንቀሳቀሱ ከሚፈቀድላቸው አራት ሃይማኖቶች ውስጥ አንዱ የካቶሊክ እምነት ነው። የኤርትራ ኦርቶዶክስ፣ የሉትራን ወንጌላዊያን እና የሱኒ እስልምና ቀሪዎቹ ናቸው።
የኤርትራ መንግስት ከአራቱ እምነቶች ውጪ ያሉ ሃይማኖቶችን የውጪ መንግስታት መጠቀሚያዎች ናቸው ሲል ይፈርጃቸዋል።
ባለፉት 30 ዓመታት በፕሬዘዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የምትመራው ኤርትራ እስካሁን ድረስ ወደ ስራ የገባ ሕገ-መንግሥት የላትም።