ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ስተርሊንግ የታጠቁ ሰዎች መኖሪያ ቤቱን ሰብረው ከገቡ በኋላ ወደ እንግሊዝ ተመለሰ
በኳታር ከእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ጋር አብሮ የነበረው የፊት መስመር ተጫዋቹ ራሂም ስተርሊንግ የታጠቁ ሰዎች ቤቱን ሰብረው ከገቡ በኋላ ወደ ለንደን መመለሱ ተገለጸ።
ክስተቱ ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ እንዳጋጠመ የተገለጸ ሲሆን የተጫዋቹ የቤተሰብ አባላት በቤት ውስጥ ሳሉ የታጠቁ ሰዎች ቤቱን ሰብረው ገብተዋል ተብሏል።
ይህ ተከትሎ በቤተሰብ አባላቱ ላይ ጉዳት ስለመድረሱም ሆነ በወንጀሉ ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር የዋለ ሰው ስለመኖሩ የተባለ ነገር ባይኖርም ስታርሊንግ ግን ከቤተሰቡ ጋር ለመሆን ከኳታር ወደ እንግሊዝ ተመልሷል።
የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ጋርዝ ሳውዝጌት ከትናንት ምሽቱ ድል በኋላ ስተርሊንግ ወደ ለንደን መመለሱን አረጋግጠዋል።
“አንዳንድ ግዜ ትልቁ ነገር እግር ኳስ ላይሆን ይችላል፤ ቤተሰብ ከሁሉም ቀዳሚ ነው” ብለዋል።
የስተርሊንግ የቡድን አጋር ደክለን ራይስ ደግሞ “ዛሬ ጠዋት (እሁድ) ቁርስ ስንመገብ አይቼው ነበር አሰልጣኛችን ችግር እንዳጋጠመው ሲነግረን ሁላችንም መልዕክት ላክልነት” ብሏል።
ከሁለት ዓመት በፊት ዘራፊዎች የሰተርሊንግ መኖሪያ ቤትን ሰብረው ገብተው ነበር። ሦስት ዘረፊዎች በወቅቱ የማንችስተር ሲቲ ተጫዋች የነበረውን የስተርሊንግ መኖሪያ ቤትን ጨምሮ የዝነኛ ሰዎች መኖሪያ ቤቶች ሰብሮ በመግባት ግምሽ ሚሊዮን ፓዎንድ የሚያወጡ ንብረቶችን ዘርፈው ነበር።
በዚህ ወንጀል ጥፋተኛ የተባሉት ሦስቱ ዘራፊዎች ከ7-8 ዓመታትን በእስር እንዲያሳልፉ ተፈርዶባቸዋል።
ስታርሊን የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድንን ለቅቆ ከኳታር የተመለሰ ሁለተኛው ተጫዋች ሆኗል።
ከጥቂት ቀናት በፊት የአርሰናል ተከላካይ ቤን ዋይት በግል ጉዳይ ወደ አገሩ መመለስ አስፈልጎታል ተብሎ ነበር።