ፈረንሳይ እና እንግሊዝ ተጋጣሚዎቻቸውን በብቃት በመርታት ሩብ ፍጻሜን ተቀላቀሉ

ኳታር እየተካሄደ በሚገኘው የዓለም ዋንጫ ትናንት የጥሎ ማለፍ ጨዋታቸውን ያደረጉት ፈረንሳይ እና እንግሊዝ ተጋጣሚዎቻቸውን በመርታት ወደ ቀጣይ ዙር አለፈዋል።

ፈረንሳይ ከፖላንድ ተገናኝታ 3 ለ 1 ያሸነፈች ሲሆን እንግሊዝ ደግሞ ሴኔጋልን 3 ለ 0 ረትታለች።

ትናንት ታጋጣሚዎቻቸውን በብቃት ያሸነፉት ሁለቱ ቡድኖች በሩብ ፍጻሜው እርስ በርስ የሚገናኙ ሲሆን ገና ከአሁኑ በርካቶች ጨዋታውን ከፍጻሜ በፊት ለዋንጫ የሚደረግ ጨዋታ ነው እያሉት ይገኛል።

የፈረንሳይ እና እንግሊዝ ግጥሚያ የፊታችን ቅዳሜ ምሽት 4 ሰዓት ይካሄዳል።

12 ሰዓት ላይ ቀድሞ በተካሄደው ጨዋታ ኦሊቪዬ ጂሩድ ቡድኑን ቀዳሚ ያደረገች ጎል ሲያስቆጥር ጎሏ ደግሞ ለእርሱ የምንግዜም የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ አድርገዋለች።

የቀድሞ የአርሰናል እና ቼልሲ የአሁን የኤሲ ሚላን አጥቂው የ36 ዓመቱ ጂሩድ ለአገሩ እስካሁን ድረስ 52 ጎሎችን አስቆጥሯል።

ከጁሩድ ጎል በኋላ ትናንት ድንቅ ሆኖ ያመሸው ካሊያን ምባፔ ሁለቱ ቀሪ ጎሎችን አስቆጥሯል። ምባፔ ትናንት ያስቆጠራቸውን ሁለት ጎሎች ጨምሮ በውድድሩ አምስት ጎሎችን በማስቆጠር እየመራ ይገኛል።

የሴኔጋሎች ሩጫ የተገታበት ጨዋታ

በምድብ ጨዋታቸው ኳታር እና ኤኳዶርን አሸንፈው ወደ ጥሎ ማለፉ የገቡት ሴኔጋሎች፤ እንግሊዝ ላይ ያልተጠበቀ ውጤት ሊያስመዘግቡ ይችላሉ የሚል ግምት ነበር።

ሆኖም ግን ሴኔጋሎች አንድ ግዜ ብቻ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርገው ከተሸነፉ በኋላ ከውድድሩ ተሰናብተዋል።

በአሁኑ ወቅት በውድድሩ ላይ ያለችው አፍሪካዊት አገር ሞሮኮ ብቻ ናት። ሞሮኮ ነገ ኃያሏን ስፔንን ትገጥማለች።

እንግሊዞች ሴኔጋልን 3 ለ 0 ያሸነፉት ከፍጽም የበላይነት ጋር ነበር።

የእንግሊዝን የማሸነፊያ ጎሎች ጆርዳን ሄንደርሰን፣ ሃሪ ኬን እና ቡካዮ ሳካ ሲያስቆጥሩ ኮከብ ሆኖ ያመሸው ግን አማካዩ ጁድ ቤሊንግሃም ነበር።

የቦሪሺያ ዶርትመንዱ አማካይ የመጀመሪያውን ጎል አመቻችቶ ከመስጠቱም በላይ እንግሊዝ ሁለተኛውን ጎል ማስቆጠር እንድትችል የመልሶ ማጥቃት ሥራ በበላይነት ሲከወን የነበረው ይህ የ19 ዓመት ወጣት ነበር።