ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢራን ከከፍተኛ ሕዝባዊ ተቃውሞ በኋላ የግብረ ገብ ፖሊስን ልትበትን ነው
ኢራን ግብረ ገብን ጥሰዋል እያለ ዜጎችን የሚያስረውን የሞራል ፖሊስ እየተበተነች ነው ተባለ።
ይህን ያለው የአገሪቱ ዐቃቤ ሕግ ነው።
የኢራን የግብረ ገብ ፖሊስ ሴቶች ጥብቅ ኢስላማዊ አለባበስን ስለመከተላቸው የሚቆጣጠር አካል ነው።
ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሆኑት መሐመድ ጃፋር ሞንታዜሪ ይህን ፖሊስ እየበተንን ነው ቢሉም ሌሎች ባለሥልጣናት ግን ይህን አላረጋገጡም።
ኢራን በዚህ የፖሊስ አካል ተፈጸመ በተባለ ሰብአዊ ጥሰት ላለፉት ሁለት ወራት ያላባራ አገር አቀፍ አመጽን አስተናግዳለች።
ማሻ አሚን የተባለች ሴት ሒጃብ በአግባቡ አልጠመጠምሽም በሚል በደረሰባት እንግልትና ድብደባ ለሞት መዳረጓን ተከትሎ ነው አመጹ የተቀሰቀሰው።
መሐመድ ጃፋር ሞንታዜሪ በአንድ መንፈሳዊ ስብሰባ ላይ ሳሉ ነበር የሞራል ፖሊስ ሊበተን ይችላል ወይ ተብለው የተጠየቁት።
እሳቸው ሲመልሱ ‘እየበተንነው ነው’ ብለዋል።
ጨምረውም፣ ‘የግብረ ገብ ፖሊስ ከፍትሕ ሥርዓቱ ጋር ምንም የሚፈይደው ነገር የለም፤ እየበተንን ያለነውም ለዚሁ ነው’ ብለዋል።
የግብረ ገብ ፖሊስ ተጠሪነቱ ለአገር ውስጥ ሚኒስቴር እንጂ ለፍትሕ ሚኒስቴር አይደለም።
ቅዳሜ ዕለት ሞንታዜሪ ፓርላማ ቀርበው እንደተናገሩት ደግሞ ሴቶች ሒጃብ መልበሳቸውን የሚያስገድደው ሕግ ‘በድጋሚ ሊጤን ይገባዋል’።
ኢራንን እየናጣት ያለው አመጽ የተቀሰቀሰው የ22 ዓመቷ አሚኒ በግብረ ገብ ፖሊስች በተያዘች በሦስተኛ ቀኗ መሞቷን ተከትሎ ነው።
የርሷ ሞት ለአመጽ መቀስቀስ ምክንያት ይሁን እንጂ በኢራን ባለው ድህነት፣ ሥራ አጥነት፣ ፍትሕ ማጣትና የሙስና መበራከት ሕዝቡ ቅሬታ ገብቶታል።
አመጹ ዘለግ ላለ ጊዜ እንዲቆይ ያደረገውም ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለው ተስፋ መቁረጥ ነው።
የግብረ ገብ ፖሊስ እንደተባለው የሚበተን ከሆነ መንግሥት ባልተለመደ ሁኔታ ለሕዝብ ጥያቄ ምላሽ መስጠት መጀመሩን ጠቋሚ ይሆናል።
ነገር ግን አመጹን ላያሳቆም ይችላል። በርካታ ሴቶች በኢራን አደባባይ ወጥተው ሒጃባቸውን ሲያቃጥሉ ነበር።
“የግብረ ገብ ፖሊስ ተበተነ ብለን አመጻችንን እናቆማለን ማለት አይደለም’ ብላለች ለቢቢሲ አንዲት ኢራናዊት።
ይቺ ሴት ጨምራ እንዳለችው፤ “መንግሥት ሒጃብ የግለሰቦች ምርጫ ነው ማለት ቢጀምርም ይህ የኢራን አስተዳደር ከሥልጣን ሳናነሳ አመጽ አናቆምም።"
ሌላ ኢራናዊት በበኩሏ “የሒጃብ ጉዳይ መነሻ ሆነ እንጂ ጥያቄያችን በዚያ አያበቃም። አብዮት ማካሄድ ነው የምንፈልገው። የአያቶላህን ሞትና የአስተዳደሩን ለውጥ ሳናይ አመጽ አናበርድም።" ብላለች።
የኢራን ሚዲያ የዐቃቤ ሕጉን አስተያየት የምዕራቡ ሚዲያ ባልተፈለገ መንገድ እየተረጎመው ነው ሲሉ ዘግበዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የኢራን የግብረ ገብ ፖሊስ መበተን መልካም ጅማሮ ነው ካሉ በኋላ የኢራን ወጣቶች ለመብታቸው መታገላቸው ታላቅ ጀግንነት ነው ሲሉ አሞካሽተዋቸዋል።
የኢራን የግብረ ገብ ፖሊስ የተመሠረተው የ1979ኙን ኢስላማዊ አብዮት ተከትሎ ነው።
በዘመናት መልኩን የቀያየረ ሲሆን በአደባባይ ሴቶች የተጋለጠ ጂንስ ሱሪ እንዳይለብሱ፣ ሒጃብ እንዲጠመጥሙ፣ አጭር ቀሚስ እንዳይለብሱ ጥብቅ ክትትል ያደርጋል።