ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ያለጸጉር መሸፈኛ የተወዳደረችው ኢራናዊት አትሌት ቤተሰቦች ቤት ፈረሰ
የኢራን ስፖርተኞችን የአለባበስ ሕግ በመጣስ በደቡብ ኮርያ በተደረገ ውድድር ላይ ያለ ጸጉር መሸፈኛ የተሳተፈችው ኤልናዝ ሬካቢ ቤተሰቦች ቤት መፍረሱ ተዘገበ።
የ33 ዓመቷ የግድግዳ ዝላይ ስፖርት ተወዳዳሪ ከውድድሩ በኋላ የጸጉር መሸፈኛዋ በድንገት እንደወደቀባት ብትገልጽም ቢቢሲ አትሌቷ ማስተባበያውን የሰጠችው በግዳጅ እንደሆነ ተረድቷል።
በመላው ኢራን የጸጉር መሸፈኛውን ግዴታነት በመቃወም ለወራት የዘለቁ ሰልፎች እየተደረጉ ሲሆን አትሌቷም ጀግና ተብላ በተቃዋሚዎች ዘንድ እየተሞገሰች ትገኛለች።
በተገባደደው ሳምንት በማህበራዊ ሚዲያው ላይ በፈረሰው የቤተሰቦቿ ቤት ብሎም በውስጡ የወዳደቁ ሜዳሊያዎችን የሚያሳይ ቪዲዮ በመዘዋወር ላይ ይገኛል።
ዳቮድ የተሰኘው የአትሌቷ ወንድም እንዲሁም በኢራን ከፍተኛ አትሌት በቪዲዮው ላይ ሲያለቅስ ይታያል።
መንግስትን የሚቃወሙት ሰልፈኞች በአትሌቷ ላይ የተወሰደውን የበቀል እርምጃ የተቃወሙ ሲሆን ቪዲዮው ግን በርግጠኝነት የተወሰደበት ቀን አልታወቀም።
በከፊል ንብረትነቱ የመንግስት የሆነው ታስኒም የተሰኘው የዜና ወኪል በቱ መፍረሱን ያረጋገጠ ሲሆን ምክኒያቱ ግን ቤተሰቤ ቤቱን ለመገንባት አስፈላጊው የግንባታ ፈቃድ ስለሌው እንደሆነ በመግለጽ አስተባብሏል።
ሚዲያው አክሎም ቤቱ የፈረሰው አትሌቷ ያለጸጉር መሸፈኛ ከመሮጧ በፊት እንደሆም ግልጿል።
በኢራን ሴቶች ጸጉራቸውን እንዲሸፍኑ እንዲሁም እጅ እና እግራቸውን ባልጠበቁ ልብሶች የመሸፈን ግዴታ ያለባቸው ሲሆን ይህም የአለባበስ ስርአት በስፖርታዊ ውድድር ላይ በሚሳተፉ ሴት አትሌቶች ላይም ይተገበራል።
አትሌቷ ወደ አገሯ ስትመለስም በርካታ ቁጥር ያለው ህዝብ የተቀበላት ሲሆን ጀግና ሲሉም ጠርተዋታል። ኤርፖርት ስትደርስም ያለ ጸጉር መሸፈኛ የቤዝቦል ኮፍያ እና ባለኮፍያ ሹራብ ለብሳ ታይታለች።
በሚቀጥለው ቀንም ከኢራን የስፖርት ሚኒሰትር ጋር ተገናኝታ የተነጋገረች ሲሆን በወቅቱም ተመሳሳይ ልብስ ለብሳ ታይታለች። ይህም ወደ ቤቷ ሳትሄድ እንዳልቀረች ጥርጣሬዎችን ጨምሯል።
ምንጮች እንደገለጹት ሬካቤ በአገሪቱ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ውስጥ በሚገኝ አንድ ክፍል ውስጥ ሲቪል በለበሱ የጸጥታ ሃይሎች ታስራ ሚኒስትሩን እስከምታገኝ ድረስ ቆይታለች።
አትሌቷ ወደ አገሯ ከመመለሷ አንድ ቀን በፊት በኢንስታግራም ገጿ ላይ ''ስላስጨንኳችሁ ይቅርታ እጠይቃለሁ'' ስትል ጽፋለች። ''በድንገት ሳላስበው እንድዘል በመጠየቄ የጸጉሬ መሸፈኛ ከራሴ ላይ ወድቆብኛል'' ስትልም አክላ ነበር።