መንግሥትን የተቃወመው ኢራናዊ ራፐር ከሞት ፍርድ ጋር ተጋፍጧል

በኢራን መንግሥትን የሚቃወሙ ሰልፎችን የደገፈው ራፐር በሞት ፍርድ ሊያስቀጣ በሚችለው ''በምድር ላይ በሚፈጸም የሙስና ወንጀል’’ ክስ ተመሰረተበት።

የ 31 ዓመቱ ቱማጅ ሳሌይሂ ፕሮፓጋንዳን በማሰራጨት፣ ከጠላት አገር ጋር በመተባበር እንዲሁም ግጭትን በማነሳሳት ወንጀል ተጠርጥሮ ክስ እንደተመሰረተበት አንድ የኢራን ፍርድ ቤት ባለስልጣን ተናግረዋል።

ይሄው ባለስልጣን የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ተከሳሽ ጠበቃ ሳይኖረው ክሱ ተጀምሯል ማለታቸውንም አስተባብለዋል።

ግለሰቡ ከአንድ ወር በፊት በተቃውሞ ሰልፎች ላይ ሲሳተፍ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በማሕበራዊ ሚዲያ ካሰራጨ በኋላ ነበር በቁጥጥር ስር የዋለው።

ቱማጅ ሳሌይሂ ከወራት በፊት ማሻ አሚኒ የተሰኘች ወጣት የኢራንን ጥብቅ የሂጃብ ግዴታ ጥሳለች በሚል በፖሊስ ቁጥጥር ስር እያለች ሕይወቷ ማለፉን ተከትሎ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ የሚደግፍ የራፕ ሙዚቃ ሰርቶ ለህዝብ አድርሷል።

በዚህ ተቃውሞም እስካሁን ድረስ 451 ሰዎች ህይወታቸውን እንዳጡ ትኩረቱን በኢራን ላይ አድርጎ የሚሰራው የሰብአዊ መብት ተቋም ይፋ አድርጓል። እንዲሁም ከ 18 ሺ በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር እንደዋሉም አክሏል።

ራፐሩ በቁጥጥር ስር ከመዋሉ ከቀናት በፊት ከአሜሪካው ሲቢሲ ጋር ባደረገው ቆይታ ''የተቃውሞ ቪዲዮዎችን ማጋራት በተለይም የአገዛዙ ኢላማ እንደሚያደርጉ እና ይህም ከባድ ነው'' ሲል ገልጾ ነበር።

ኢራናዊያን በጣም አስከፊ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ እና ''ኢራናዊያን ስልጣኑን፣ ገንዘቡን ብሎም የጦር መሳሪያውን ለማስጠበቅ ሲል ካስፈለገ ሙሉ ሕዝቡን ለመግደል ዝግጁ ከሆነ የማፊያ አገዛዝ ጋር ተጋፍጠዋል'' ሲልም ተናግሮ ነበር።

ከአንድ ወር በፊት ራፐሩ በቁጥጥር ስር ሲውል የሚያሳየውን ቪዲዮ የኢራን ብሔራዊ ሚዲያ አስተላልፎት ነበር። በቪዲዮው ላይ ሳሌይሂ ነኝ ያለ እና አይኑ በጨርቅ የተሸፈነ ግለሰብ ተንበርክኮ በሚንቀጠቀጥ ድምጽ የኢራን የጸጥታ ሃይሎች እንዲያመልጡ በተቃውሞ ሰልፍ ወቅት መናገሩ ጥፋት እንደሆነ ሲናገር ይደመጣል።

ሃሳብን በነጻነት በመግለጽ መብት ላይ አተኩሮ የሚሰራው አርቲክል 19 የተሰኘው ተቋም ሳሌይሂ ተገዶ የእምነት ክህደት ቃሉን መስጠቱን ተቃውሟል።

በለንደን የሚኖረው የራፐሩ ወንድም እንዳለው ሳሌይሂ ላይ ለማስፈረድ የሃሰት ማስረጃ ሊቀርብ እንደሚችል ስጋት እንዳለው ለሲቢሲ ተናግሯል።

በርካታ ኢራናዊያን የጥበብ ሰዎች በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ በመውጣት የራፐሩን እስር እንዲሁም የሞት ፍርድ ሊያስከትል የሚችለውን ክስ በመቃወም ሃሳባቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።

በርካታ ኢራናዊያን የጥበብ ሰዎች ይህንኑ የተቃውሞ እንቅስቃሴ መደገፋቸውን ተለከትሎ ለእስር የተዳረጉ ሲሆን መንግስት የተወሰኑትን ከእስር ለቋል።