ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢራን ሃይማኖታዊ መሪ በአገራቸው ለተቀሰቀሰው ሁከት አሜሪካና እስራኤልን ተጠያቂ አደረጉ
በኢራን የመንግሥት ስርዓት ውስጥ ትለቁን ስፍራ የሚይዙት የሃይማኖት መሪ በፖሊስ ይዞታ ስር ሳለች አንዲት ሴት መገደሏን ተከትሎ በኢራን ለተቀሰቀሰው ተቃውሞ አሜሪካና እስራኤልን ተጠያቂ አደረጉ።
ሃይማኖታዊ መሪው አያቶላህ አሊ ካሃሜኒ ከሕዝባዊ ተቃውሞ በኃላ ባደረጉት የመጀመሪያ ንግግር በአገራቸው ሁከት ያቀጣጠሉት የኢራን ታሪካዊ ጠላቶች ናቸው ብለዋል።
ለአስርት አመታት በቆየውን የስልጣን ዘመናቸው ትልቅ የሚባለውን ተቃውሞ ያስተናገዱት መሪው የጸጥታ ኃይሎች ይበልጥ እንዲዘጋጁ አዘዋል።
አሜሪካ በበኩሏ በኢራን ለተቀሰቀሰው ሕዝባዊ ተቀውሞ እየተሰጠ ያለው ምላሽ አሳሳቢ ነው ብላለች።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ባወጡት መግለጫ ሰለማዊ ታቃዋሚዎችን ለመቅጣት የሚወሰዱት የኃይል እርምጃዎች በተመለከተ እየወጡ ያሉ ሪፖርቶች እጅግ እንደሚያሳስባቸው ገልጸዋል።
እንነዚህ ታቀዋሚዎች ለፍትህ እና ዓለም አቀፍ መርህዎች እንዲከበሩ ነው ጥሪ እያቀረቡ ያሉት ሲሉ ያከሉት ፕሬዝዳንቱ፤ አሜሪካ “በጀግንነነታቸው ዓለምን ካነቃቁት የኢራን ሴቶች ጎን ትቆማለች” ብለዋል።
ከዚህ ሃሳብ ጋር ተመሳሳይነት ያልው አቋም ያንጸባረቀችው ዩናይትድ ኪንግድምም በለደን የሚገኘውን የኢራን ከፍተኛ ዲፕሎማትን በመጥራት የኢራን መሪዎች “ጣትን ወድ ውጪ በመጠቆም ሌሎችን ከመወንጀል ይለቅ ለተፈጸመው ድርጊት ኃላፊነት እንዲወስዱ እና የሕዝባቸውን ቅሬታ እንዲሰሙ” መልዕክት ለቴህራን ንግሩልኝ ብላለች።
የ22 ዓመቷ ማሻ አሚኒ በቴህራን ሴቶች በሂጃብ ጸጉራቸውን እንዲሸፍኑ የሚጠይቀወን ጥብቅ ህግ ተላልፋለች በሚል በስነ-ምግባር ደንብ አስከባሪዎች ከተያዘች ከሶስት ቀናት በኃላ ሕይወቷ አልፏል።
ቤተሰቦቿ የፖሊስ መኮንኖቹ ማሻ አማኒን እንደደበደቧት እና ከመኪና ጋር እንዳገጯት ይገልጻሉ። ሆኖም ፖሊስ ይህ ስለመሆኑ ምንም ማስረጃ የለም በማላት ሕይወቷ ያለፈው በድንገተኛ የልብ ህመም ነው የሚል መልሽ ሰጥቷል።
የአሚኒ ቀብር ተከትሎ በአገሪቱ ሴቶች የመሩት ተቃውሞ የተቀሰቀሰ ሲሆን የጸጉር መሸፈኛቸውን በአየር ላይ እያወለበለቡ እና በእሳት እያቃጠሉ የታዩ ሲሆን “ሴቶች፣ ህይወት፣ ነጻነት” እና “ሞት ለአንባገነኖች” ሲሉ ተድምጠዋል።
ትላንት ሰኞ በፖሊሶች እና የጸጥታ ኃይሎች ምርቃት ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ሃይማኖታዊ መሪው የአሚና ሞት “ልባችንን ሰብሮታል” ብለዋል።
“. . . ቁርአን በማቃጠል፣ ከሴቶች ላይ ሂጃብ በማውለቅ፣ መስጅድ እና መኪና ላይ እሳት በመለኮስ መንገዱን አስፈሪ አድርገውታል” ብለዋል።
በሀገሪቱ መንግሥታዊ ስርዓት የመጨረሻውን ውሳኔ የሚሰጡት አያቶላህ “በሁሉም መስክ ጥንካሬ ያላትን ኢራንን” መታገስ የማይችሉት የውጪ ኃይሎች ኢራንን ለማወክ እቅድ አላቸው ብለዋል።
“በግልጽ የምናገረው የዚህ ብጥብጥ እና ጸጥታው መደፍረስ መሃንዲሶች አሜሪካ እና ሃሰተኞቹ ጽዮናውያን [እሳራኤል] እንዲሁም የነሱ ተከፋይ የሆኑ እና በውጪ የሚኖሩ ከሃዲ ኢራናውያን የሚታገዙ ናቸው” ብለዋል።
መሪው ለጸጥታ አስከባሪዎች ያላቸውን ሙሉ ድጋፍም ገልጸዋል።
መሠረቱን ኖርዌይ ያደረገ የኢራን ሰብአዊ መብት ቡድን ባለፈው ዕሁድ ባወጣው መግለጫ ቢያንስ 133 ሰዎች በጸጥታ ኃይሎች መገዳላቸውን ገልጿል።
የአገሪቱ ብሄራዊ ጣቢያ ደግሞ የጸጥታ አካላትን ጨምሮ 40 ሰዎች መገደላቸውን ዘግቧል።