ቭላድሚር ፑቲን ዩክሬን ሰላም የሚኖራት “ዓላማችን ሲሳካ ብቻ ነው” አሉ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን ከአንድ ዓመት በላይ ሲካሄድ የቆየው ጦርነት አብቆቶ ሰላም የሚወርደው “ዓላማችን ሲሳካ ብቻ ነው” አሉ።
ፑቲን ይህን ያሉት ዩክሬን ላይ መጠነ ሰፊ ወረራ ከፈጸሙ በኋላ በሰጡት የመጀመሪያው ጋዜጣዊ መግለጫቸው ነው።
ፑቲን “በዩክሬን እየተካሄድ ስላለው ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ” ሲናገሩ የሩሲያ ሉዓላዊነት መረጋገጥ አለበት ብለዋል። “አገራችን ሉዓላዊነቷ ሳይረጋገጥ ልትኖር አትችልም። ፈጽሞ አትኖርም” ብለዋል።
“በዩክሬን ሰላም የሚኖረው ዓላማችን ሲሳካ ብቻ ነው። እነዚህ ዓላማዎች አልተቀየሩም” ሲሉም አክለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ዓላማቸው በዩክሬን አለ የሚሉትን የናዚ ርዮተ ዓለም ማጥፋት፣ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን ማምከን እና ዩክሬንን ገለልተኛ አገር ማድረግ እንደሆነ ተናግረዋል።
ፑቲን በጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ ሩሲያ በዩክሬን እየተዋጉ ያሉ 617 ሺህ ወታደሮች እንዳሏት ተናግረዋል። ፕሬዝዳንቱ ከእነዚህ የሠራዊት አባላት በተጨማሪ ሌሎች 300 ሺህ ለአገልግሎት ጥሪ እንደተደረገላቸው እና 486 ሺህ ሰዎች ደግሞ በፈቃዳቸው በውል ለሩሲያ ለመዋጋት መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
ፑቲን “አገራችንን ለመከላከል ጦር መሳሪያ የሚያነግቡ ወታደሮች ቁጥር አልቀነስም” ካሉ በኋላ . . . “በአጠቃላይ በዚህ ዓመት ማብቂያ ላይ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ ተዋጊዎች አሉን። ተጨማሪ የወታደር ምልመላ ማድረግ ለምን ያስፈልገናል?” ሲሉም ጠይቀዋል።
ፑቲን ሁለት ዓመት ለመድፍን በተቃረበው ጦርነት ምን ያህል የሠራዊታቸው አባላት አንደሞቱ ያሉት ነገር ባይኖርም፣ በቅርብ የሚያውቋቸው ሰዎች ልጆች ለሩሲያ በመዋጋት ዋጋ መክፈላቸውን በመግለጽ “በርካታ ለእኔ ቅርብ የሆኑ ሰዎች” ሕይወታቸው አልፏል ብለዋል።
ምንም እንኳ ሩሲያ በዩክሬኑ ጦርነት ምን ያክል የጦር አባላት እንደተገደሉባት በይፋ ያለችው ነገር ባይኖርም የአሜሪካ የደኅንነት ተቋማት ከጦርነቱ መጀመር አንስቶ ቢያንስ 315 ሺህ ወታደሮች ተገድለዋል ወይም የተለያየ ደረጃ ያለው ጉዳት ደርሶባቸዋል ያሉ ሲሆን፣ ይህ አሃዝ በጦርነቱ ጅማሬ ወቅት ሩሲያ ከነበራት ሠራዊት 90 በመቶ ይሆናል ብለዋል።
ፑቲን በመንግሥት ቁጥጥር የሚደረግበት ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው በሰጡት መግለጫ የዩክሬን ባለሥልጣናት ከምዕራባውያኑ ወታደራዊ ድጋፍ ለማግኘት ሲሉ ወታደሮቻቸውን እያስገደሉ ነው ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ፕሬዝዳንቱ የዩክሬን ሠራዊት አባላት በሩሲያ በኃይል ከተያዙት ግዛቶች መካከል አንዷ በሆነችው ክሬሚያ ወደፊት ገፍቶ ለመሄድ ትልቅ መስዋትነት እየከፈሉ እንደሆነ ተናግረዋል።
“ለምን ይህን እንደሚያደርጉ አይገባኝም። የራሳቸውን ሰዎች እያስገደሉ ነው። የዩክሬን ወታደሮች ወደማይመለሱበት አቅጣጫ እየሄዱ ነው። ለዚህ ምክንያቱ ፖለቲካዊ ነው፤ ምክንያቱም የዩክሬን መሪዎች የውጭ እርዳታ እንዲሰጣቸው እየተለማመጡ ነው።”
ፑቲን በንግግራቸው በዩክሬን ባሉ በሁሉም ጦር ግንባሮች ጦራቸው የበላይትን ይዞ እንደሚገኝ ከተናገሩ በኋላ፣ ሠራዊታቸው አስፈላጊ ከሆነ ወደፊት መገስገስ እንደሚችልም ጨምረው ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ ሩሲያ ከአውሮፓ ኅብረት እና ከአሜሪካ ጋር ስላለት ግንኙነት ሲናገሩ ደግሞ አሜሪካ “አስፈላጊ አገር” መሆኗን ጠቅሰው አገሪቱ “ሌሎች ሰዎችን እና አገራትን ግን ማክበር ይኖርባታል” ብለዋል።
ፑቲን አሜሪካ “ሌሎች ሰዎችን እና አገራትን ማክበር” ስትጀምር አገራቸው ከአሜሪካ ጋር የነበራትን ግንኙነት ለማስቀጠል ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል።












