የቫግነር መሪ የቭጌኒ ፕሪጎዢን ሥርዓተ ቀብር መፈጸሙ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, REX/SHUTTERSTOCK
የሩሲያው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ቫግነር የቭጌኒ ፕሪጎዢን ሥርዓተ ቀብሩ በሴንት ፒተርስበርግ መፈጸሙን ቡድኑ አስታወቀ።
የፕሪጎቀዢን የቀብር ሥነ ሥርዓቱ የተካሄደው በትውልድ ከተማው ጥቂት ሰዎች በተገኙበት መሆኑ ተገልጿል።
ሊሰናበቱት የሚፈልጉ ሰዎች የተቀበረበት ስፍራ መሄድ እንደሚችሉም ተገልጿል።
ባለፈው ሳምንት ሞስኮ አቅራቢያ ፕሪጎዢንን ጨምሮ 10 ሰዎችን ያሳፈረ አውሮፕላን ተከስክሶ ሕይወቱ ማለፉ ይታወሳል። ሩሲያ በሞቱ እጄ የለበትም ብላለች።
ሆኖም በሩሲያ ውስጥና ከውጭም የአገሪቱን ጉዳይ የሚከታተሉ እንደሚሉት የ62 ዓመቱ ፕሪጎዢን ሞስኮ ላይ ወታደራዊ አመጽ ማካሄዱን ተከትሎ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ “መሞቱ አይቀርም ነበር” ሲሉ ተደምጠዋል።
የቫግነር የመገናኛ ብዙኃን ክፍል ስለ ፕሮጎዢን ሥርዓተ ቀብር አጭር ማብራሪያ በቴሌግራም ሰጥቷል።
የት ሊቀበር ይችላል የሚለውን በተመለከተ ብዙ መላ ምቶች ሲሰነዘሩ ቆይተዋል።
ኋላ ላይ ግን የተቀበረው ፖሮኮቭስኮ የተባለ የቀብር ስፍራ ከአባቱ መቃብር አጠገብ መሆኑ ተገልጿል።
ወታደራዊ ሽኝት እንዳልተደረገለትና በቀብሩም ብዙዎች እንዳልተገኙ ተገልጿል።
መገናኛ ብዙኃንም እንዲገቡ አልተፈቀደም።
በቦታው አድማ በታኝ ፖሊሶች፣ ፀረ ሰው አልባ አውሮፕላን ፖሊሶችና አነፍናፊ ውሾችም ጥበቃ ሲያደርጉ ታይቷል።
ኤምኤስኬ 1 የተባለው የሩሲያ ድረ-ገጽ እንደዘገበው በቀብሩ የቫግነር ሰንደቅ አላማ ተውለብልቧል።
የፕሪጎዢን ቀኝ እጅ የነበረው እና በተከሰከው አውሮፕላን አብሮት ተሳፍሮ የነበረው ዲሚትሪ ኡትኪን ሥርዓተ ቀብርም በተመሳሳይ ቀን ነው የተከናወነው።
የቡድኑን ንግድ ነክ ሥራዎች የሚያሳልጠው ዲሚትሪ እንደነበር ይታመናል።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በፕሪጎዢን ቀብር ላይ እንደማይገኙ ተገልጾ ነበር።
ከአውሮፕላን አደጋው በኋላ ሐዘናቸውን በአደባባይ ከመግለጻቸው በፊት 24 ሰዓታት አልፈዋል።
ፑቲን “በሕይወት ትልልቅ ስህተቶች የፈጸመ፣ ብዙ ክህሎት ያለው ሰው ነበር” ብለዋል ስለ ፕሪጎዢን ሲናገሩ።
የፕሪጎዢን ወታደሮች በወታደራዊ አመጹ ወደ ሞስኮ ማቅናት ጀምረው እንደነበር ይታወሳል። ይህንንም ፑቲን እንደ ክህደት ነው የወሰዱት።
ሩሲያ ከግድያው ጀርባ አለች የሚሉ የጥርጣሬ አስተያየቶች ቢሰሙም ሩሲያ አስተባብላለች።
የአሜሪካ ባለሥልጣኖች ለቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ በሰጡት አስተያየት አውሮፕላኑ የተከሰከሰው በውስጡ በተከሰተ ፍንዳታ ምክንያት ነው።












