በባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ መሬት ለኢንቨስተሮች መሰጠቱ በዝሆኖች ደኅንነት ላይ ስጋት ፈጠረ

ዝሆኖች

የፎቶው ባለመብት, HENOK SEYOUM

በኢትዮጵያ ትልቁ የዝሆኖች መጠለያ የሆነው እና በምሥራቅ ሐረርጌ የሚገኘው የባቢሌ ፓርክ ከፊል ሥፍራ ተቆርሶ ለግብርና ኢንቨስተሮች መሰጠቱ አደጋ ላይ ላሉት ዝሆኖች ደኅንነት መሆኑ ተነገረ።

ባለፈው ቅዳሜ ጠዋት ረፋድ 5፡00 ሰዓት አካባቢ ለልማት ተፈቅዶልናል ያሉ ባለሃብቶች ዶዘር አስከትለው በመሄድ ወደ ቅጥሩ ለመግባት ሲሞክሩ በዝሆኖቹ መጠለያ ጠባቂዎች በመከልከላቸው ግጭት ተፈጥሮ እንደነበር ቢቢሲ ተረድቷል።

በዚህም ሳቢያ በተወሰኑ መንግሥት በመደባቸው እና ሕጋዊ የደንብ ልብስ በለበሱ የዱር እንሰሳት ጥበቃ ልማት ሬንጀሮች ላይ ድብዳባ እንደተፈጸመባቸው ተናግረዋል።

ወደ ፓርኩ ለመግባት የተከለከሉት ባለሃብቶች ይህንን የፈጸሙት የፀጥታ አካላትን በማምጣት ሲሆን፣ በተጨማሪም የመጠለያውን ጣባቂዎች አስረዋቸው እንደነበረ እና ትናንት ሰኞ ነሐሴ 22/2015 ዓ.ም. መፈታታቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ግለሰቦች ገልጸዋል።

ግጭቱን ተከትሎ ባለሃብቶቹን ማስቆም እንዳልተቻለ እና ይህ ዘገባ በሚጠናቀርበት ወቅትም ዶዘር ይዘው ወደ ቅጥሩ በመግባት በፍጥነት ቁፋሮ እያካሄዱ መሆኑንን የቢቢሲ ምንጮች ተናግረዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የፓርኩ ጥበቃ ዋርደን አቶ አደም መሐመድ ክልሉ ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመነጋገር በፍጥነት ይህን ድርጊት ሊያስቆም ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዱር እንሰሳት ጥበቃ ባለሥልጣንም ድርጊቱ ዝሆኖችን ለአደጋ የሚያጋልጥ እና አኗኗራቸውን የሚያናጋ በመሆኑ ከኦሮሚያ ክልል ጋር በመሆን የፓርኩ ደኅንነት ለማስከበር እየሠራ መሆኑን ገልጿል።

ስፋቱ 6980 ካሬ ኪሎ ሜትር የሆነው የባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ ውስጥ ለእርሻ ልማት በሚል በባለሃብቶች እየታረሰ ነው የተባለው ቦታ በፓርኩ ሰሜናዊ ክፍል ኤረር ሸለቆ በሚባለው ስፍራ ያለ ነው።

እንደ አቶ አደም መሐመድ ገለጻ ደግሞ ይህ የጣቢያው ክፍል የዝሆኖቹ ዋንኛ የመራቢያ እና መንቀሳቀሻ ስፍራ በመሆኑ በእንስሳቱ አጠቃላይ ደኅንነት ላይ አደጋን ያስከትላል።

“75 ከመቶ የሚሆኑት ዝሆኖች ህልውና የተመሠረተው በዚህ ክፍል ነው። ኤረር ሸለቆ ከሌለ የባቢሌ ዝሆኖች አይኖሩም። አስቸኳይ መፍትሄ ያስፈልጋል የምንለውም ለዚሁ ነው” ብለዋል ዋርደን አቶ አደም መሐመድ።

በዚህ ፓርክ ውስጥ 40 ሺህ አባወራዎች መስፈራቸው እና ከጊዜ ወደ ጊዜ የዝሆኖቹ ሕልውና አደጋ ላይ እየወደቀ እንደመጣ ሲዘገብ ቆይቷል።

ባለሃብቶች በተለይ ለእርሻ፣ ለከብት ማደለቢያ እና ለንብ እርባታ አካባቢውን ይፈልጉታል። በዋናነትም ስፍራው ከ50 ዓመታት በላይ በመንግሥት እጅ ስለቆየ ጥብቅ እና ለም መሬት ስለሆነ እንዲሁም ወንዝ ዳር በመሆኑ ውሃ በቀላሉ ማግኘት ስለሚችሉ ባለሃብቶች ዐይናቸውን እንደጣሉበት ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በተጨማሪም ከአካባቢው የሚፈናቀል ሰው ስለሌለ እና ካሳ ስለማይከፍሉ ወደ ፓርኩ ቅጥር ገብቶ የእርሻ ሥራ ማከናወን አትራፊ እንደሚያደርጋቸው ስለሚያውቁ አካባቢው ለባለሃብቶች እንዲፈለግ አድርጎታል።

ሆኖም ማንኛውም ሰፈራ እና የእርሻ እንቅስቃሴ በጥብቅ ፓርኩ ውስጥ መከናወኑ ለዝሆኖቹ ሕልውና ቀጥተኛ አደጋ ነው ይላሉ ባለሙያዎች።

ከዚህ ቀደም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድ እና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ይህ ፓርክ 75 ከመቶ ክፍሉ ወደ እርሻነት እየተቀየረ እንደሆነ ገልጾ ነበር።

ዝሆኖች

የፎቶው ባለመብት, HENOK SEYOUM

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ይህ ፓርክ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሐረርጌ ዞን እና በሶማሌ ክልል የፋፈን እና የረር ዞኖችን ይዋሰናል።

ይህ ፓርክ በተደጋጋሚ ለእርሻ ለግጦሽ እና ለደን ምንጣሮ የተጋለጠ ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎች ወደ ጥብቅ ፓርኩ በመግባት ኑሮ መመሥረት መጀመራቸውን ቢቢሲ ከአካባቢው ያገኘው መረጃ ያሳያል።

የሰፋሪዎችን በስፋት መምጣት ተከትሎ ዝሆኖች አካባቢውን እየለቀቁ መሆኑም ይነገራል።

አቶ አደም መሐመድ “ፓርኩ አጥር የለውም፤ ከስፋቱ የተነሳ ማጠርም የሚቻል አይደለም። ነገር ግን ድንበሩ ይታወቃል። ሕጋዊ ካርታ አለው። ሰዎች ድንበሩን አልፈው ነው እየቆፈሩ ያሉት” ብለዋል።

“ጥበቃዎቻችን ላይ ‘ምናገባችሁ እናንተ’ በሚል ድብደባ ደርሶባቸዋል። ምሥራቅ ሐረርጌ ፖሊስ መምሪያ አስረዋቸዋል። ከዞን እና ፖሊስ አመራሮች ጋር ተነጋግረን ነው ልጆቻችን እንዲፈቱ ያደረግነው’’ ብለዋል አቶ አደም።

በጉዳዩ ዙሪያ ቢቢሲ ያነጋገራቸው በኢትዮጵያ የዱር እንሰሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ብሔራዊ ፓርኮች አስተዳደር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር አዳነ ፀጋዬ ይህ ቦታ ተሰጥቶኛል የሚለው ኩባንያ ‘ስቲ አፕልስ’ የሚባል ሲሆን፣ ለእርሻ ልማት ተሰጠኝ ከሚለው 160 ሄክታር ቦታ ፓርኩ ውስጥ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ለአልሚዎቹ የተሰጠው መሬት ፓርኩ ውስጥ እንደሚያርፍ ባለሃብቱም የአካባቢውም አስተዳደር እንደሚያውቁ የተናገሩት ዶ/ር አዳነ፣ በዚህ ምክንያት ወደ ፓርኩ ውስጥ ዘልቆ በመግባት ማረስ እንደማይቻል ተነግሯቸው ሙከራው ለጊዜው ተገቶ እንደነበር ገልጠዋል።

“ባለሃብቱ የመከላከያ አባላት ነን የሚሉ ሰዎችን ይዘው መጥተው ነው፣ የፓርኩን ጥበቃዎች መሣሪያ አስፈትተው ወደ ሐረር በመውሰድ ያሳሰሯቸው” በማለት መንግሥት የመደባቸው የፓርኩ ሠራተኞች መታሰራቸውን ረጋግጠዋል።

ይህ ቦታ ተላልፎ ቢሰጥ ከፓርኩ 160 ሄክታር የሚቀንስ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪ ባቢሌ ካለው ይዞታ ሰፊ ቦታው በሕገ ወጥ ሰፈራ በመወረረሩ አደጋውን የከፋ ያደርገዋል።

በተለይ ለግብርና ኢንቨስትመንት ተሰጠ የተባለው ሰፊ አካባቢ ለዝሆኖቹ እጅግ ወሳኝ የሚባለውን ውሃ የሚያገኙበት፣ ወንዝ ያለበት ቦታ ስለሆነ የሚያስከትለው ተጽእኖ ከፍተኛ ነው ይላሉ።

“ዝሆኖች ምግባቸውን እና ውሃ የሚያገኙበት እና የሚራቡበት ስፍራ ስለሆነ ያ አካባቢ ተረበሸ ማለት ሙሉ የባቢሌ ፓርክ ጥብቅ ሥፍራ ተረበሸ ማለት ስለሆነ ተያያዥ ጉዳትን ይዞ ይመጣል” ብለዋል ዶ/ር አዳነ።

የፓርኩን ሠራተኞች አንገላተው እንዲታሰሩ አድርገዋል ስለተባሉት የመከላከያ ሠራዊት አባላት በተመለከተም “ለዚህ ተግባር የታዘዙ የመከላከያ አባላት ስለመኖራቸው ምንም መረጃ የለም” በማለት እየተጣራ መሆኑንም ገልጠዋል።

በፓርኩ ውስጥ በሠራተኞቹ ላይ ባለፈው ቅዳሜ የተፈጸመው ድርጊት “የኢትዮጵያ ዱር እንሰሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ከኦሮሚያ ክልል ጋር በመሆን በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ባለበት ጊዜ ይህ መከሰቱ አስደንግጦናል” ብለዋል ዶ/ር አዳነ።

አክለውም ይህን በጥበቃው ሠራተኞች ላይ የተደቀነ ድንገተኛ እና አደገኛ እርምጃን ለማስቆም እንዲሁም ይህ ችግር እንዴት እንደተፈጠረ ለመረዳት ከኦሮሚያ ክልል ጋር በመሆን እያጣሩ መሆናቸው ለቢቢሲ አስረድተዋል።

የባቢሉ ዝሆኖች መጠለያ በምሥራቅ ኢትዮጵያ ሐረርጌ ዞን ባቢሌ ወረዳ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በ1962 ዓ.ም. ነበር የተመሠረተው።

ይህ የዝሆኖች መጠለያ በአፍሪካ ውስጥ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት መካከል ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ብቸኛው የጥቁር ዝሆኖች መጠለያ ፓርክም ነው።

በኢትዮጵያ ብቸኛ የጥቁር ዝሆኖችን መጠለያ ባቢሌ ፓርክ ከ30 በላይ አጥቢ እንሰሳት 220 ብርቅዬ አእዋፋት መጠለያ ሆኖ ቆይቷል።

የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በፓርኩ ውስጥ ከ31 በላይ አጥቢ እንስሳት እና ከ220 በላይ የአዕዋፋት ዝርያዎች ይገኛሉ።