ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ዝሆኖች በታጣቂዎች ተገደሉ

ከተገደሉ ዝሆኖች አንዱና ፖሊሶች

የፎቶው ባለመብት, Mago National Park

ባለፈው ሳምንት በደቡብ ክልል በሚገኘው የማጎ ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ ከዚህ ቀደም አጋጥሞ በማያውቅ ሁኔታ ስምንት ዝሆኖች መገደላቸው ተገለጸ።

የማጎ ብሔራዊ ፓርክ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጋናቡል ቡልሚ እና የደቡብ ክልል ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ፍሬሕይወት ዱባለ ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት በአንድ ቀን ውስጥ ስምንት ዝሆኖች ለጥርሳቸው ሲባል በታጠቁ ሰዎች ተገድለዋል።

የማጎ ብሔራዊ ፓርክን በደንብ የሚያውቀው የቱሪዝምና ጉዞ ጋዜጠኛው ሄኖክ ስዩም እንደሚለው ይህ ግድያ እጅግ የከፋና ከዚህ ቀደም አጋጥሞ የማያውቅ በእንስሳቱና በአገር ላይ የተፈጸመ ወንጀል ነው ብሏል።

ማክሰኞ ግንቦት 18/2012 ዓ.ም በዝሆኖቹ ላይ ጥቃቱ የተፈጸመው በፓርኩ አቅራቢያ ባለው ኦሞ ወንዝ ላይ ውሃ በሚጠጡበት ጊዜ በርካታ ጥይት ተተኩሶባቸው እንደሆነና ጥርሳቸውም እንደተወሰደ የፓርኩ ሥራ አስኪያጅ ገልጸዋል።

በዝሆኖቹ ላይ ጥቃቱን ከፈጸሙት ሰዎች መካከል ሁለቱ በዝሆኖቹ አማካይነት ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው በህክምና ላይ እንደሚገኙ የገለጹት ወ/ሮ ፍሬሕይወት አንደኛው ከዚህ ቀደም በወረዳ አመራር ውስጥ የነበረ ግለሰብ እንደሆነ ጠቅሰው መንግሥት በድርጊቱ ፈጻሚዎች ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ እንዲወሰድ ያደርጋል ብለዋል።

ከአምስት ዓመት በፊት በተደረገ ቆጠራ በማጎ ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ 175 ዝሆኖች ይገኙ አንደነበረ የገለጹት አቶ ጋናቡል በስምንቱ ዝሆኖች ላይ የተፈጸመው ግድያ ከዚህ በፊት ያልታየ "ጭፍጨፋ" ነው ሲሉ በምሬት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዝሆኖቹ ላይ ግድያውን የፈጸሙት ሰዎች አስበውና ተዘጋጅተው ለጥርሳቸው ሲሉ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ጋናቡል አንድ ዝሆን ከ30 በላይ በሆነ ጥይት መመታቱን እንዳረጋገጡ ገልጸው ድርጊቱን "ዘር ማጥፋት ነው" ሲሉ ገልጸውታል።

በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎች አርብቶ አደሮችና የታጠቁ በመሆናቸው በፓርኩ ውስጥ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠርና በእንስሳቱ ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት ለማስቆም አስቸጋሪ እንዳደረገው የሚናገሩት የፓርኩ ሥራ አስኪያጅ ይህ ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ሄኖክ ስዩም እንደሚለው ተጎራብተው በሚገኙት በማጎና በኦሞ ብሔራዊ ፓርኮች በአጠቃላይ 600 ያህል ዝሆኖች የሚገኙ ሲሆን በተለያዩ ወቅቶች በሚፈጸሙ ግድያዎች የዝሆኖቹ ቁጥር ሳያንስ እንደማይቀር ይናገራል።

ከተገደሉ ዝሆኖች አንዱ

የፎቶው ባለመብት, Mago National Park

ሄኖክ ጨምሮም ጥቃቱ በዝሆኖቹ ላይ ብቻ ያነጣጠረ ሳይሆን የፓርክ ጠባቂዎችም ኢላማ ናቸው ይላል። "ዝሆኖቹን ለማደን የሚመጡት ሕገወጦች የፓርኩን በሚጠብቁ ስካዉቶች ላይ ጥቃት ይፈጽማሉ።"

የማጎ ብሔራዊ ፓርክ ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ጋናቡል ቡልሚም ይህ ስጋት እውነት እንደሆነ ጠቅሰው ጠባቂዎቹ ዝሆኖቹን ለመከላከል እርምጃ ሲወስዱ እንደሚጠየቁ እንደዚሁም ለአደጋ እንደሚጋለጡ ጠቅሰው፤ " ባለፈው ዓመት አንድ አባላችን ሲገደል እስካሁን ከአስር በላይ በሕገ ወጦች ጥቃት ተገድለዋል።"

እንዲህ አይነት በሰዎችና በእንስሳቱ ላይ ወንጀሎች ሲፈጸሙ ጉዳዩ የአገር ሽማግሌዎች ተይዞ ያለተገቢ ቅጣት ስለሚታለፍ ድርጊቱ እንዲደገም ይበረታታል። ለፓርኮቹና ጠባቂዎቹ ተገቢው ከለላና አስፈላጊ የመከላከያ መሳሪያ ካልተሰጠ ተመሳሳይ ነገር ማጋጠሙ አይቀርም ይላል ሄኖክ።

ለአሁኑ ጥቃትም ያለው አለመረጋጋትና የመንግሥት ትኩረት በኮናቫይረስ ወረርሽኝ ላይ መሆኑን ተገን ተደርጎ እንደሆነ በመግለጽ ጥብቅ እርምጃና ትኩረት ለፓርኮቹ እንዲሰጥ አሳስቧል።

ወ/ሮ ፍሬህይወት እንደሚሉት የክልሉና የዞኑ መስተዳደር አጥቂዎችን ለይቶ ለሕግ ለማቅረብ አስፈላጊው ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። "ወንጀለኞቹን አጋልጦ ለሕግ በማቅረብ ቀጣይ ጥቃቶችን በማያዳግም እርምጃ ለማስቆም እየሰራን ነው" ብለዋል።

በዝሆኖቹ ላይ በተፈጸመው ጥቃት ክፉኛ ያዘነው ሄኖክ ስዩም፤ "ኢትዮጵያ ዝሆኖችን ለመጠበቅ ስምምነት ፈርማለች ቀላል የማይባል ድጋፍም እያገኘች ነው። ነገር ግን በማጎ እና በባቢሌ ፓርኮች ውስጥ በዝሆኖች ላይ ተደጋጋሚ ችግር እየደረሰ ነው" በማለት የጉዳቱን አሳሳቢነት አመልከቷል።

ዝሆኖቹ ላይ የሚደርሰው ጉዳት በዚህ ከቀጠለ ሊጠፉ እንደሚችሉ የሚሰጋው ሄኖክ አገሪቱ ለእንስሳቱ ጥበቃና ከጎብኚዎች የምታገኘው ገቢ ከመቆሙ ባሻገር ለትውልድ ተጠብቀው መተላለፍ ያለባቸውን ሐብቷን ታጣለች ይላል።

ከሁሉ ያሳዘነው ደግሞ ይህን ያህል ቁጥር ያላቸው ዝሆኖች ተገድለው "የሚመለከታቸው የፌደራልና የክልል ኃላፊዎች የወሰዱት ፈጣን እርምጃ ያለመኖሩ ነው።"