የተጎሳቆሉት የባቢሌ ዝሆኖች ህልውና አደጋ ላይ ነው

Arba

የፎቶው ባለመብት, Science Photo Library

ዝሆን በኢትዮጵያ ውስጥ በደቡብ፣ በኦሮሚያ፣ ጋምቤላ እና ትግራይ ክልሎች ጨምሮ በተለያዩ 10 ሥፍራዎች ይገኛል።

ከእነዚህ ሥፍራዎች መካከል በስፋት የሚገኘው በምስራቅ ሃረርጌው የባቢሌ የዝሆን መጠለያ ውስጥ ነው።

አቶ ገዛኸኝ ፍቃዱ የመጠለያ ጣቢያው የቱሪዝም ባለሙያ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ የተቋቋመው ዝሆኖችን ለመጠበቅ በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በ1962 ዓ.ም. ነበር።

ባለሙያው እንደሚሉት መጠለያ ጣቢያው በንጉሡ ዘመን ከመመስረቱ በፊት ቦታው ዝሆን እና አንበሳ የሚታደኑበት ሥፍራ ነበር። በዚህም ሳቢያ የዝሆኖች ቁጥር እየተመናመነ ሲመጣ ነበር መጠለያው የተቋቋመው።

ይህ መጠለያ በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች መካከል የሚገኝ ሲሆን በውስጡ እስከ 350 የሚገመቱ ሎክሶዳንታ አፍሪካና የሚባል ዝርያ ያላቸው ዝሆኖችን ይዟል።

ይሁን እንጂ በባቢሌ የዝሆን መጠለያ ውስጥ የሚገኙት ዝሆኖች በተጋረጡባቸው ፈተናዎች ምክንያት ሙሉ በሙሉ ከአካባቢው ሊጠፉ እንደሚችሉ የተለያዩ ጥናቶች ይጠቁማሉ። በአካባቢው ከሚገኙ ባለሙያዎች እንደሰማነው እና እኛም በቦታው ተገኝተን እንደታዘብነው ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ በሆኑ ምክንያቶች የዝሆኖቹ ህልውና አደጋ ላይ ወድቋል።

የዝሆኖቹን ህልውና አደጋ ላይ ከጣሉ ግንባር ቀደም ምክንያቶች አንዱ ሕገ-ወጥ አደን እንደሆነ አቶ ገዛኸኝ ይናገራሉ።

ከዚህም ባሻገር ሕገ-ወጥ ሰፈራ፣ እርሻ፣ በመጠለያ ውስጥ የቤት እንስሳትን ለግጦሽ ማሰማራት እና ከሰል ማክሰል ተጨማሪ ችግሮች መሆናቸውን የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ ጠባቂ አቶ ሀሰን አሕመድ ነግረውናል።

"ዝሆን በባህሪው ጸጥታ የሚፈልግ እንስሳ ነው። ረብሻ አይወድም። በሕገ-ወጥ መንገድ በአካባቢው የሰፈሩ ሰዎች ዝሆኑን እየረበሹት ነው" ይላሉ አቶ ሀሰን። እኛም ዝሆኖቹን ለመመልክት ወደ መጠለያ ጣቢያው በሄድንበት ወቅት እረኞች ድምጻቸውን ከፍ አድርገው እየተጯጯሁ ከብቶቻቸውን ለግጦሽ ሲያሰማሩ ተመልክተናል።

አቶ ሀሰን አሕመድ (ቀኝ) ከባልደረባቸው ጋር በባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ ሥፍራ
የምስሉ መግለጫ, አቶ ሀሰን አሕመድ (ቀኝ) ከባልደረባቸው ጋር በባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ ሥፍራ

የመጠለያው ጥበቃዎች እንደነገሩን ዝሆን ረብሻ ስለማይወድ የጩኸት ድምጽ ከሰማ አካባቢውን ለቅቆ ይሄዳል። በዚህም እረኞቹ ያለ ስጋት ከብቶቻቸውን አሰማርተው ወደ ቀያቸው ይመለሳሉ።

"የአካባቢው ማህበረሰብ ከዝሆኖቹ የሚያገኙት ጥቅም ስለሌለ አይወዷቸውም" የሚሉት ደግሞ አቶ ገዛኸኝ ናቸው። ይህንን በዝርዝር ሲያስረዱም፤ የዝሆን መጠለያ ሥፍራው የተዘጋጀው ዝሆኖቹን ለመጠበቅ ብቻ ነው።

በአካባቢው ያለው ነባራዊ ሁኔታ ጎብኚዎችን የሚስብ ስላልሆነም የአካባቢው ነዋሪዎች ዝሆኖቹን ከመጠበቅ ይልቅ እየተስፋፋ ያለው በረሃማነት ወደ መጠለያው ዘልቀው እንዲገቡ እያስገደዳቸው ነው ይላሉ።

አቶ ገዛኸኝ አክለውም መንግሥት በአካባቢው መሠረተ ልማትን በማጠናከር የጎብኝ ፍሰት እንዲኖር በማድረግ የአካባቢ ህዝብ ተጠቃሚ የሚሆንበት ሁኔታ መፈጠር አለበት ሲሉ እንደ ባለሙያ ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል።

የመጠለያው ጠባቂ አቶ ሀሰን በበኩላቸው ዝሆኖቹን እየገደሉ ጥርሱን ወደ ውጪ የሚወስዱት ሰዎች የተደራጁ እና ዘመናዊ መሳሪያዎችን የሚታጠቁ ናቸው ይላሉ። ይህ ብቻም ሳይሆን በዝሆን ግድያ እና በዝሆን ጥርስ ንግድ የተሰማሩት ቡድኖች ከጎረቤት ሃገራት ጭምር እንደሚመጡ እናውቃለን ሲሉ አቶ ሀሰን ነግረውናል።

"ሕገ-ወጥ አዳኞችን ለማስወገድ ብንንቀሳቀስ በመቶ የሚቆጠሩ ዘመናዊ መሳሪያዎችን ይዘው ይወጡብናል። እኛ በቁጥር አነስተኛ ነን። የታጠቅነው መሳሪያው ኋላ ቀረሽ ነው" ሲሉም ያለባቸውን ተግዳሮት ያስረዳሉ።

በባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ በነበረን ቆይታ እንዳስተዋልነው፤ በጥብቁ መጠለያ ውስጥ የሰዎች እንቅስቀሴ እጅግ ከፍተኛ ነው። ሰፋፊ እርሻዎች፣ የቤት እንስሳት፣ የመኖሪያ ቤቶች እና የጫት ገበያ ጭምር ተመልክተናል።

መጠለያው በዚህ ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ ምናልባትም ከሁለት እና ከሦስት ዓመታት በኋላ ዝሆኖቹን በፎቶ እንጂ በአካል መመልከት እንደማንችል የመጠለያው ጣቢያ የቱሪዝም ባለሙያ አቶ ገዛኸኝ ስጋታቸውን ለቢቢሲ ገልፀዋል።

በመጠለያው ከዝሆኖች በተጨማሪ፣ 31 አጥቢ እንስሳት እና ከ191 በላይ አእዋፋት ይገኛሉ።