የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ አጣዳፊ ዓለም አቀፍ ስጋት መሆኑ አበቃ

የዝንጀሮ ፈንጣጣ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ዓለም አቀፍ አጣዳፊ የጤና ስጋት መሆኑ ማብቃቱን የዓለም ጤና ድርጅት ገለጸ።

በሽታው አስቸኳይ የጤና ስጋት መሆኑ የታወጀው ከዓመት በፊት ነበር።

ቫይረሱ አሁንም እንዳለና በቀጣይ ወረርሽኝ ሆኖ ሊቀሰቀስ ወይም የበሽታው ስርጭት ዳግመኛ ሊያገረሽ እንደሚችል የዓለም ጤና ድርጅት አስረድቷል።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም አገራት አሁንም “በተጠንቀቅ እንዲጠብቁ” ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።

በዝንጀሮ ፈንጣጣ ከተያዙ ሰዎች ጋር በሚደረግ ንክኪ በሽታው ወደ ሰው ይተላለፋል።

ሞንኪፖክስ በተባለው ቫይረስ አማካይነት የሚመጣው ቫይረሱ ይፋዊ መጠሪያው ኤምፖክስ ነው። በሽታው ፈንጣጣ ከሚያስይዘው ቫይረስ ጋር የሚያያዝ ቢሆንም የዝንጀሮ ፈንጣጣ ግን የከፋ ነው።

ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ እብጠት፣ የጀርባ ሕመም እና የጡንቻ ሕመም ከበሽታው ምልክቶች መካከል ናቸው።

ትኩሳት ከያዘ በኋላ ሽፍታ ከፊት ጀምሮ በመላው ሰውነት ላይ ይወጣል።

የበሽታው ምልክት የታየባቸው ሰዎች ወደሌሎች ቫይረሱን ላለማስተላለፍ ከግብረ ሥጋ ግንኙነት እና ሌሎችም አካላዊ ንክኪዎች እንዲታቀቡ ይመከራል።

ከበሽታው የሚከላከል ክትባት መውሰድም መፍትሄ ይሆናል።

ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ በሆነበት ወቅት በ111 አገራት 87,000 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው 140 ሰዎች መሞታቸውን የዓለም ጤና ድርጅት ገልጿል።

ዶ/ር ቴድሮስ እንዳሉት ባለፉት ሦስት ወራት በበሽታው የመያዝ መጠን 90 በመቶ የቀነሰ ሲሆን፣ ይህም ቀደም ካሉት ወራት ያነሰ በመሆኑ በሽታው ከዚህ በኋላ አጣዳፊ የጤና ስጋት መሆኑን እንደሚቀንሰው አሳውቀዋል።

ከሳምንት በፊት ኮቪድ-19 አጣዳፊ ዓለም አቀፍ የጤና ስጋት መሆኑ ማክተሙን የዓለም ጤና ድርጅት መግለጹ ይታወሳል።

አንድ ሕመም ዓለም አቀፍ አጣዳፊ ስጋት ነው ተብሎ ሲታወጅ አገራት የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታት በጋራ እንዲሠሩ ይጠበቃል።

የዓለም ጤና ድርጅት አጣዳፊ ዓለም አቀፍ ስጋት ካላቸው መካከል ፖሊዮ ቫይረስ ይገኝበታል። እአአ ከ2014 ጀምሮ ነው ሕመሙ በዝርዝሩ ውስጥ እንዲገባ የተደረገው።