ደቡብ አፍሪካ ለሩሲያ የጦር መሳሪያ አቅርባለች ሲሉ የአሜሪካ አምባሳደር ከሰሱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ደቡብ አፍሪካ በዩክሬኑ ጦርነት ውስጥ ገለልተኛነቷን በይፋ ብትገልጽም ለሩሲያ የጦር መሳሪያዎች አቅርባለች ሲሉ በደቡብ አፍሪካ የአሜሪካ አምባሳደር ክሰሱ።
አምባሳደሩ ሩበን ብሪጌት እንዳሉት ባለፈው ታኅሣሥ የጦር መሳሪያ እና ጥይቶችን የጫነች አንዲት የሩሲያ መርከብ ኬፕ ታውን ነበረች ብለዋል።
የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ጽህፈት ቤት ምንም አይነት ደጋፊ ማስረጃ አልቀረበበትም ባለው የአምባሳደሩ ክስ መቆጣቱን ገልጿል።
ደቡብ አፍሪካ በዩክሬን ላይ ከተፈጸመው ወረራ አንጻር ገለልተኛነቷን ጠብቃ እንዳለች አሁንም እየገለጸች ነው።
የአሜሪካው አምባሳደር ሐሙስ ዕለት ፕሪቶሪያ ውስጥ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፣ ዋሽንግተን ደቡብ አፍሪካ በግጭቱ ውስጥ ገለልተኛ ነኝ በማለት የያዘችው አቋም እንዳሳሰባት ተናግረዋል።
አምባሳደሩ በታኅሣሥ ወር መጀመሪያ ሳምንት ላይ በኬፕታውን በሚገኘው የባሕር ኃይል ሰፈር ቆማ የነበረችው የጭነት መርከብ በእርግጠኝነት የጦር መሳሪያ እና ጥይቶችን ጭና “ወደ ሩሲያ መመለሷን” ገልጸዋል።
የደቡብ አፍሪካ ባለሥልጣናትን ባስደነገጠው የአሜሪካው አምባሳደር ባቀረቡት ክስ “ሩሲያን ማስታጠቅ በጣም ኣሳሳቢ ጉዳይ ነው” በማለት በቀላሉ የሚታይ ጉዳይ እንዳልሆነ አመልክተዋል።
ይህንን ክስ ተከትሎ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት በአንድ ጡረተኛ ዳኛ የሚመራ ገለልተኛ አጣሪ ማቋቋሙን የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ ይፋ አድርገዋል።
በደቡብ አፍሪካ እና በሩሲያ መካከል ተጠናክሮ የቀጠለውን ግንኙነት በተመለከተ ስትተች ቆይታለች።
ሩሲያ ዩክሬንን የወረረችበት አንደኛ ዓመት በታሰበበት ጊዜ ደቡብ አፍሪካ ሩሲያ እና ቻይና ባካሄዱት ወታደራዊ ልምምድ ውስጥ መሳተፏ እንዳሳሰባት አሜሪካ ገልጻ ነበር።
የጦር ልምምዱ የዩክሬን ወረራ ከተጀመረበት አንደኛ ዓመት ጋር መግጠሙ ወረራውን መደገፍ ነው በሚል ተቃውሞ ቢገጥመውም፣ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር ክሱን አስተባብለዋል።
ጨምረውም ደቡብ አፍሪካ ከፈረንሳይ እና ከአሜሪካ ጋር ወታደራዊ ልምምድ እንደምታደርገው ሁሉ ከቻይና እና ከሩሲያ ጋር ያደረገችው የተለመደ ተግባር ነው ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በተባበሩት መንግሥታት የሩሲያን ወረራ በማውገዝ ድምጽ በተሰጠበት ጊዜ ደቡብ አፍሪካ ድምጿን ያቀበች ሲሆን፣ አሜሪካ እና የአውሮፓ አገራት በሩሲያ ላይ ማዕቀብ ሲጥሉ እንድትተባበር ቢጠይቋትም ሳትቀበለው ቀርታለች።
የአገሪቱ ፕሬዝዳንት የአሜሪካው አምባሳደር ያቀረቡት ክስ እንዲመረመር እንደሚያደርጉ እና ሂደቱ ሲጠናቀቅ ውጤቱ ይፋ እንደሚሆ በመግለጽ ተቃዋሚዎቻው እንዲታገሱ ጠይቀዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በጉዳዩ ላይ እስካሁን በይፋ የሰጠው አስተያየት የለም።
ክሱ እውነት ሆኖ ከተገኘ ደቡብ አፍሪካ የያዘችውን የገለልተኝነት አቋምን የሚጎዳ ከመሆኑ በላይ አንዳንዶች ሩሲያ በዩክሬን ላይ በፈጸመችው ወረራ ተባባሪ ናት እስከማለት ሊደርሱ ይችላሉ።
ለሩሲያ ቀርቧል ስለተባለውን የጦር መሳሪያን በተመለከተ ግልጽ መረጃ የለም። በተጨማሪም የጦር መሳሪያው ከመንግሥት ወይም ከግል የጦር መሳሪያ አምራች ተቋማት የተገኙ ስለመሆናቸው የታወቀ ነገር የለም።
ምንም ይሁን ምን ይህ ክስ የደቡብ አፍሪካን ገለልተኝነት የጥያቄ ውስጥ በመክተት ምዕራባውያን እንደወራሪ ከሚያይዋት ሩሲያ ጋር መቆምን መርጣለች በማለት ትልቋ የንግድ አጋሯ ከሆነችው ከአሜሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት የሚጎዳው ይሆናል ተብሏል።
ደቡብ አፍሪካ ከሩሲያ ጋር ቀረበ ግንኙነት ያላት ሲሆን ገዢው የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኤኤንሲ) ፓርቲም ለሩሲያ ጋር ለረጅምጊዜ የቆየ ትስስር አለው።
ሩሲያ አባል የሆነችበት ብሪክስ የተባሉት አገራት ማኅበር ጉባኤን በመጪው ነሐሴ የምታስተናግደው ደቡብ አፍሪካ በስብሰባው ላይ ይገኛሉ የተባሉት ፕሬዝዳንት ፑቲን ጉዳይ አወዛጋቢ ሆኗል።
ከዩክሬኑ ጦርነት ጋር በተያያዘ ተፈጽመዋል በተባሉ ወንጀሎች ምክንያት በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) የመያዣ ትዕዛዝ በወጣባቸው በሩሲያ ፕሬዝዳንት ምክንያት ዲፕሎማሲያዊ አጣብቂኝ ውስጥ ትገኛለች።
የፍርድ ቤቱ ፈራሚ የሆነችው ደቡብ አፍሪካ ቭላድሚር ፑቲን ወደ አገሯ ሲገቡ አስራ ለችሎቱ ማስረከብ የሚጠበቅባት ሲሆን፣ ይህንን ግን ለመፈጸም ፈቃደኛ ባለመሆኗ ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብን አስከትሎባታል።
ደቡብ አፍሪካ በአህጉሪቱ ውስጥ ለሚገኙ አገራት የጦር ማሰሪያዎችን የሚያርቡ እያደጉ የመጡ የጦር መሳሪያ አምራች ኢንዱስትሪዎች አሏት። ነገር ግን እነዚህ አምራቾች ምን ያህል አቅም እንዳላቸው በአሁኑ ወቅት የሚታወቅ ነገር የለም።
አሁን የአሜሪካው አምባሳደር ደቡብ አፍሪካ ለሩሲያ የጦር መሳሪያ ታቀርባለች በሚል ያረቡት ክስ የአገሪቱን ባለሥልጣናት ያስቆጣ ሲሆን፣ ጉዳዩ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መያዝ ነበረበት ይላሉ።












