ሶማሊያ ውስጥ በድርቅ ምክንያት 43,000 ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ ተገለጸ

በድርቅ ምክንያት ተፈናቅለው በመጠለያ ውስጥ ከሚገኙ ሶማሊያውያን መካከል አንዷ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በድርቅ ምክንያት ተፈናቅለው በመጠለያ ውስጥ ከሚገኙ ሶማሊያውያን መካከል አንዷ

ለተከታታይ ወቅቶች ዝናብ ባለመጣሉ ምክንያት ባለፈው ዓመት ሶማሊያ ውስጥ 43,000 የሚጠጉ ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀሩ በሶማሊያ መንግሥት እና በተባበሩት መንግሥታት አማካይነት የወጣ አዲስ ሪፖርት አመለከተ።

ይህም በአፍሪካ ቀንድ ባጋጠመው ድርቅ ምክንያት የሞቱ ሰዎችን የጠቆመ የመጀመሪያው ይፋዊ ዘገባ ነው ተብሏል። ከሟቾቹ ውስጥም ግማሾቹ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት እንደሚሆኑ ተገልጿል።

የድርቁ ቀውስ ገና መፍትሄ ያላገኘ በመሆኑ በተያዘው የአውሮፓውያን ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ውስጥ ከ18,000 አስከ 34,000 የሚደርሱ ተጨማሪ የሰዎች ሞት ሊኖር እንደሚችል ተገምቷል።

ከአርባ ሺህ በላይ ሶማሊያውያን መሞታቸውን ይፋ ያደረገው የዚህ ሪፖርት ጥናት በዩኒሴፍ እና በዓለም ጤና ድርጅት መሪነት በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ በሚገኙ ሁለት ታዋቂ ዩኒቨርስቲዎች አማካይነት የተካሄደ ነው።

ከአስር ዓመት በፊት ሶማሊያን በመታው ድርቅ ምክንያት በተከሰተ ረሃብ ከ240 ሺህ በላይ ሰዎች መሞታቸው ይነገራል።

በሶማሊያ “ሊከሰት የሚችል ተጨማሪ ሞትን በመከላከል ሕይወት ለማትረፍ ከጊዜ ጋር እየተፎካከርን ነው” ሲሉ የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ ዶክተር ማሙኑር ራህማን ማሊክ ተናግረዋል።

እርምጃ የማንወስድ ከሆነ ልጆች፣ ሴቶች እና ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች “ተስፋ አጥተው፣ ያለ ድጋፍ የሚሞቱበትን አሰቃቂ ሁኔታ የምንመለከት ይሆናል” ሲሉ ዶክተር ማሙኑር ጨምረው ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት በዚህ የአውሮፓውያን ዓመት በሶማሊያ ውስጥ የድርቅ ተጎጂዎችን ለመደገፍ 2.6 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው ገልጿል። ከዚህ ውስጥ እስካሁን የተገኘው ከ15 በመቶ በታቹ ነው።

በድርቅ ምክንያት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የእርሻ እንስሳት ለሞት የተዳረጉ ሲሆን፣ ይህም በአየር ጠባይ ለውጥ፣ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እና በዓለም ደረጃ የምግብ ዋጋ መናር ደግሞ ቀውሱን አባብሶታል።

በሶማሊያ ውስጥ ሌላው አሳሳቢ የሆነው ጉዳይ ከአልቃኢዳ ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚነገረው እና በአሜሪካ እንዲሁም በዩናይትድ ኪንግደም በሽብር ቡድንነት በተፈረጀው አልሻባብ ቁጥጥር ስር ወደ ሚገኙ አካባቢዎች እርዳታ ማድረስ አለመቻሉ ነው።

አልሻባብ ተደጋጋሚ የሆኑ ከባድ ጥቃቶችን በሶማሊያ ውስጥ የሚፈጽም በመሆኑ በሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ሥራ ላይ ከባድ እንቅፋትን ፈጥሯል።

በተጨማሪም የአሜሪካ መንግሥት በሽብር የተፈረጁ ቡድኖች ከሰብአዊ እርዳታ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ የሚያደርገው መመሪያ በራሱ ድጋፍ የሚፈልጉ ማኅበረሰቦችን ለመድረስ ያለውን ዕድል አወሳስቦታል ተብሏል።

በሶማሊያ ያሉ የሰብአዊ እርዳታ ባለሥልጣናት በበኩላቸው በዩክሬን ያለው ጦርነት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በአገሪቱ ያለውን ቀውስ ችላ እንዲለው አድርጎታል ብለው ያምናሉ።

አሶሺየትድ ፕሬስ እንደዘገበው ባለፈው ጥር ወር ላይ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ እርዳታ አስተባባሪ የሆኑት አደም አብደልሙላ፣ ለጋሾች “ቀሪውን ዓለም እርግፍ አድርገው በመተው በዩክሬን ላይ አተኩረዋል” ሲሉ ተናግረዋል።