ትራምፕ ለዩክሬን ረዥም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳዔል ሊሰጡ እንደሚችሉ ተናገሩ

ከመርከብ ላይ የሚወነጨፍ ሚሳዔል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ቶማሆክ የተሰኘው ሚሳዔል ዩክሬን የሩሲያን ከተሞች ለማጥቃት ዕድል ይሰጣታል

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቶማሆክ የተሰኘ ረዥም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳዔል ለዩክሬን ለመላክ እንዳሰቡ ተናገሩ።

ፕሬዚዳንቱ ሚሳዔሉ ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ለምታካሄደው ጦርነት "አዲስ የማጥቃት ዕድል" ይሰጣል ብለዋል።

ትራምፕ በኤር ፎርስ ዋን አውሮፕላናቸው ላይ ሳሉ ቶማሆክ (Tomahawk) ሚሳዔልን ለዩክሬን ይሰጡ እንደሆን ተጠይቀው "እናያለን. . . ልልክ እችላለሁ" ሲሉ ተናግረዋል።

ትራምፕ ይህንን ያሉት በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ከዩክሬኑ አቻቸው ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ጋር ለሁለተኛ ጊዜ በስልክ ከተነጋገሩ በኋላ ነው።

ዜሌንስኪ ሩሲያ ለምትፈጽመው ጥቃት ምላሽ ለመስጠት ጠንካራ ወታደራዊ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ሲጠይቁ ቆይተዋል።

ሞስኮ ከዚህ ቀደም ዋሽንግተን ረዥም ርቀት የሚወነጨፍ ሚሳዔል ለኪየቭ የሚሰጥ ከሆነ የአሜሪካ ሩሲያን ግንኙነት ያበላሻል፣ በግጭቱ ላይም ሌላ ውጥረት ይፈጥራል በማለት እንዳይሰጥ ስታስጠነቅቅ ነበር።

ቶማሆክ ሚሳዔል 2,500 ኪ.ሜ. የሚወነጨፍ ሲሆን ዩክሬን በቀላሉ ሞስኮን እንድታጠቃ ያስችላታል።

ትራምፕ ዩክሬን ቶማሆክ ሚሳዔል መጠየቋን ለሩሲያ እንደሚያሳውቁ ጨምረው ተናግረዋል።

"ጦርነቱ የማይፈታ ከሆነ ልነግራቸው እችላለሁ [ለሩሲያ]፣ ልናደርገው እንችላለን፣ ላናደርገውም እንችላለን፣ ነገር ግን ልናደርገው እንችላለን።"

"ቶምሆክ ወደ እነርሱ አቅጣጫ እንዲወነጨፍ ይፈልጋሉ? አይመስለኝም" ሲሉ አክለዋል።

ኪየቭ በተደጋጋሚ ከውጊያው ቀጠና በርቀት የሚገኙትን የሩሲያ ከተሞች ለማጥቃት ረዥም ርቀት የሚወነጨፉ ሚሳዔሎች እንዲሰጧት ስትጠይቅ ቆይታለች።

ዜሌንስኪ እና ትራምፕ በስልክ ውይይታቸው ወቅት የኪየቭን የአየር መከላከያ እና የረዥም ርቀት ተተኳሾችን ጨምሮ ወታደራዊ አቅሟን ለማጠናከር ተነጋግረዋል።

ኪየቭን ጨምሮ በርካታ የዩክሬን ከተሞች በተደጋጋሚ የሩሲያ አየር ጥቃት ሰለባ ሆነዋል።

ሩሲያ በተከታታይ የዩክሬን የኃይል አቅርቦት መሠረተ ልማቶችን ዒላማ አድርጋ ተከታታይ ጥቃት የፈጸመች ሲሆን በዚህም የተነሳ የኤሌትሪክ ኃይል መቋረጥ አጋጥሟል።

ባለፈው ሳምንት የትራምፐ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት ኪት ኬሎግ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሩሲያ ውስጥ ዘልቆ የሚፈጸም ጥቃትን ማጽደቃቸውን ለፎክስ ኒውስ ተናግረዋል።

ሩሲያ ዩክሬንን እአአ በ2022 የካቲት ወር የወረረች ሲሆን ቶማሆክ ሚሳዔል የጦርነቱን አቅጠጫ ይቀይረዋል መባሉን አጣጥለዋለች።

ባለፈው ወር የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ "ቶማሆክ ወይም ሌሎች ሚሳዔሎች የጦርነቱን ሁኔታ ሊቀይሩት አይችሉም" ብለው ነበር።