ኢራን ከተቃውሞ ሰልፎቹ ጋር በተያያዘ ተጨማሪ አምስት ሰዎች ላይ የሞት ፍርድ ፈረደች

በኢራን በቅርቡ መንግስትን በመቃወም ከተደረጉ ሰልፎች ጋር በተያያዘ ''የፈጣሪ ጠላትነት'' በሚል ክስ አምስት ሰዎች በአብዮታዊው ፍርድ ቤት የሞት ፍርድ ተፈረደባቸው።

በዋና ከተማዋ ቴህራን የሚገኘው አብዮታዊ ችሎት በስም ያልተገለጸ አንድ ''አመጸኛ'' በመኪና አንድ ፖሊስን ገጭቶ በመግደል ክስ ጥፋተኛ በማለት የሞት ፍርድ ቅጣቱ እንደተጣለበት የሕግ ተርጓሚው ሚዛን የተሰኘ የዜና ወኪል ይፋ አድርጓል።

ሁለተኛው ግለሰብ ቢላ እና ሽጉጥ በመያዝ ብሎም ሶስተኛው ግለሰብ መንገድ በመዝጋት ''ሽብር'' ፈጥሯል በሚል ክስ ነው የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው።

አራተኛው ግለሰብ በቢላ ሰው ወግቷል በሚል ክስ የሞት ፍርዱ እንደተፈረደበት ሚዛን የተሰኘው መገናኛ ዘግቧል። ካለፈው ዕሁድ ጀምሮ አምስት የሞት ፍርድ ቅጣቶች ተሰጥተዋል።

የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች የሞት ፍርዱን የተቃወሙት ሲሆን ፍትሃዊ ያልሆነ የፍርድ ሂደት ውጤት ነው ሲሉም አውግዘውታል።

''ሰልፈኞቹ በምርመራ ወቅት ጠበቃ የማግኘት መብት የላቸውም። የሃሰት የዕምነት ቃላቸውን ለመውሰድም አካላዊ ብሎም ስነ-ልቦናዊ ስቅይት ይደርስባቸዋል። እናም ፍርድ የሚሰጠው በዚህ የዕምነት ክህደት ቃል ላይ በመመስረት ነው'' ሲሉ መሰረቱን ኖርዌይ ያደረገው የኢራን የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ተቋም ዳይሬክተር ማሃሙድ አሚሪ ሞግሃዳም ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ገልጸዋል። 

ምንም እንኳን ፍርድ ቤቱ የተከሳሾችን ስም ዝርዝር ይፋ ባያደርም አምነስቲ ኢንተርናሽናል የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቐማት ክሳቸውን በመመልከት ማንነታቸውን መለየት ችለዋል። መሃመድ ጎሆባደሉ፣ ማኖቸህር ምሀማን ናቫዝ፣ ማሃን ስዳራት፣ መሃመድ ቦሩግሃኒ እና ሳሃንድ ኑርሞሃመድ ዛዴህ የሞት ፍርዱ መሆናቸውን ይፋ አድርጓል።

አምነስቲ ግለሰቦቹ ከጸጥታ ጋር በተያያዘ ተመሳሳይ ክስ ከታሰሩ 21 ሰዎች ውስጥ ሲሆኑ የቀረቡባቸው ክሶችም በኢራን የሸሪአ ሕጎች መሰረት በሞት ፍርድ የሚያስቀጡ ናቸው። ''የፈጣሪ ጠላትነት'' እና ''በምድር ላይ የሚፈጸም ሙስና'' የሚሉ ክሶች መሆናቸውንም አክሏል።

በኢራን ባለፉት ወራት ቢያንስ 348 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 15 ሺህ 900 ሰዎች ደግሞ ለእስር ተዳርገዋል።ይህም የጸጥታ ሃይሎች የኢራን መሪዎች በውጭ ሃይሎች የታገዘ ''አመጽ'' ብለው በጠሩት የተቃውሞ ሰልፎች ላይ በተሳተፉ ዜጎች ላይ በወሰዷቸው እርምጃዎች መሆኑን መሰረቱን በውጪ አገር አድርጎ በሚንቀሳቀሰው የሰብአዊ መብቶች አክቲቪስቶች የዜና ኤጀንሲ የተሰኘ ተቋም ሰንዷል።

በሴቶች የሚመራው ይህ የተቃውሞ እንቅስቃሴ በፖሊስ እጅ ሳለች ህይወቷ ያለፈው የ 22 ዓመት ወጣት ማሻ አሚን ህልፈትን ተከትሎ ነበር የተቀጣጠለው።

የኢራን የብሔራዊ የቴሌቪዢን ጣቢያ እንደዘገበው ባሳለፍነው ረቡዕ ኢዜህ በተሰኘች ከተማ ''አሸባሪዎች'' በተቃዋሚ ሰልፈኞች እና በፖሊስ ላይ በገበያ ውስጥ በከፈቱት ተኩስ አምስት ሰዎች ተገድለዋል። የኩሁዜስታን ምክትል አስተዳዳሪ እንደገለጹት ሶስት ወንዶች አንዲት ሴት ብሎም አንድ ታዳጊ ሴት ልጅ ህይወታቸው ማለፉን ተናግረዋል።

ነገር ግን የተቃዋሚ አክቲቪስቶች ተሟጋቾች የሟቾች ቁጥር ከእዚህም ሊያይል እንደሚችል እና የጸጥታ ሃይሎች የ 10 ዓመት ታዳጊን መግደላቸውን በመግለጽ ወንጅለዋል። እንዲሁም ሰልፈኞች አንድ የክርስትና ሃይማኖት መማሪያ ትምህርት ቤትን ሲያቃጥሉ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ይፋ አድርገዋል።

የሰብአዊ መብቶች ዜና ኤጀንሲው አመጹ ከተጀመረ ጀምሮ የተገደሉ ሰዎች 43 ናቸው ያለ ሲሆን የአገሪቱ ብሔራዊ ሚዲያ ግን 38 ናቸው ሲል ገልጿል።