ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢራን፡ የቴህራን ፍርድ ቤት ከሁከት ጋር በተያያዘ የመጀመሪያውን የሞት ፍርድ በየነ
የኢራን ፍርድ ቤት በሃገሪቱ በተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ ተሳትፏል በሚል በተያዘ ሰው ላይ የመጀመሪያውን የሞት ፍርድ መበየኑን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ።
በቴህራን የሚገኘው አብዮታዊ ፍርድ ቤት ስሙ ያልተጠቀሰውን ተከሳሽ የመንግስት ተቋም አቃጥሏል እንዲሁም "የፈጣሪ ጠላት" በመሆን ጥፋተኛ ብሎታል።
ሌላ ፍርድ ቤት ደግሞ ከብሔራዊ ደኅንነት እና የሕዝብ ሰላም በማወክ ክስ አምስት ሰዎችን ከአምስት እስከ 10 ዓመት የሚደርስ እስራት በይኖባቸዋል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድን ባለስልጣናት “ሳይለዩ የሞት ፍርድ” ለማስተላለፍ እያቀዱ ሊሆን ይችላል ሲል አስጠንቅቋል።
መቀመጫውን ኖርዌይ ያደረገው የኢራን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድን ቢያንስ 20 ሰዎች በሞት የሚያስቀጣ ክስ ቀርቦባቸዋል ሲል ይፋዊ ሪፖርቶችን ጠቅሷል አስታውቋል።
የድርጅቱ ዳይሬክተር ማህሙድ አሚሪ-ሞጋዳም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አስቸኳይ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል። "ተቃዋሚዎችን መግደል መዘዝ አለው ሲሉም እስላማዊ ሪፐብሊኩን በጥብቅ” አስጠንቅቀዋል።
ጥብቅ የሂጃብ ህግጋትን ጥሳለች በሚል በስነ ምግባር ፖሊስ ተይዛ የነበረችው የ22 ዓመቷ ማህሳ አሚኒ በቁጥጥር ስር ከዋለች በኋላ ህይወቷ በማለፉ ከሁለት ወራት በፊት ተቃውሞ ተቀስቅሷል።
ተቃውሞው ወደ 140 ከተሞች የተዛመተ ሲሆን ይህም ከአስር ዓመታት በላይ ከሆነ ጊዜ በኋላ ለእስላሚክ ሪፐብሊክ ትልቅ ፈተና መደቀኑ ተዘግቧል።
የኢራን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እንደገለጸው ቢያንስ 326 ተቃዋሚዎች በጸጥታ ሃይሎች በወሰዱት የሃይል እርምጃ ሲገደሉ 43ቱ ህጻናት ሲሆኑ 25ቱ ደግሞ ሴቶች ናቸው።
መቀመጫውን ከሃገር ውጭ ያደረገው የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች የዜና ወኪል የሟቾችን ቁጥር 341 አድርሶ ሌሎች 15 ሺህ 800 ተቃዋሚዎች መታሰራቸውንም ገልጿል። የ39 የደህንነት አባላት መሞታቸውንም አስታውቋል።
የኢራን መሪዎች ተቃውሞውን በሃገሪቱ የውጭ ጠላቶች የተቀሰቀሰ ‘ሁከት’ ሲሉ ገልጸውታል።
ባለፈው ሳምንት የፍትህ ኃላፊው ጎላምሁሴን ሞህሴኒ ኢጄይ "ዋና አጥፊዎች" በተቻለ ፍጥነት ተለይተው እንዲታወቁ እና ሌሎችም የሚያርም ቅጣት እንደሚተላለፍ አሳውቀዋል።
“ሁከት ፈጣሪዎች” “በሞሃረበህ” (በፈጣሪ ጠላትነት)፣ “ኤፍሳድ ፊል-አርዝ” (በምድር ላይ ሙስና) እና “ባጊ” (የታጠቀ አመጽ) ሊከሰሱ እንደሚችሉ አስጠንቅቋል። እነዚህ ክሶች በኢራን ሸሪዓ ህግ የሞት ቅጣት ሊያስቀጡ ይችላሉ።
መሳሪያ የያዙ እና የሚጠቀሙ፣ ብሄራዊ ደህንነትን የሚያደፈርሱ ወይም አንድን ሰው የገደሉ “ቂሳ” (ያጠፉትን ዓይነት ቅጣት) ሊቀበሉ ይችላሉ ብለዋል። ይህም ከ290ው የኢራን ፓርላማ አባላት 272 ፍትህ እንዲሰጥ ላቀረቡት ጥሪ ምላሽ ይመስላል።
የፍትህ አካላት እንደሚሉት ከ2 ሺህ የሚበልጡ ሰዎች “በቅርብ ጊዜ በተፈጠረው ግርግር” ተሳትፈዋል ተብለው ክስ ተመሥርቶባቸዋል።
የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን የፍትህ ባለስልጣናትን ዋቢ በማድረግ እሑድ እለት እንደገለፁት 164ቱ በደቡብ ሆርሞዝጋን ግዛት፣ 276ቱ በማዕከላዊው ማርካዚ እና 316ቱ በኢስፋሃን ግዛት ክስ እንደተመሰረተባቸው ዘግበዋል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ሰኞ ዕለት ከፈረንሳዩ ኢንተር ሬድዮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የኢራን ባለስልጣናት እየወሰዱት ያለው እርምጃ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ነው ብለዋል።
ለዚህም ተጠያቂ በሆኑት ላይ "ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ምላሽ እና ማዕቀብ" እንዲጣል እንደሚደግፉ ተናግረዋል።
አመጹን በተመለከተም በተደጋጋሚ አብዮት የሚለውን ቃልም በመጠቀም ገልጸውታል።
"ይህንን አብዮት ያነሱት ሴቶች ናቸው። የ[1979 የእስልምና] አብዮት የልጅ ልጆች አብዮት አንስተዋል" ብለዋል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስተያየቱን "አሳፋሪ" ሲል ገልጸውታል።
የአውሮፓ ህብረት "ለኢራን ተቃዋሚዎች አፈና ተጠያቂ ናቸው" ባላቸው 29 ኢራናውያን እና ሦስት ተቋማት ላይ ማዕቀብ ጥሏል።
ዒላማ ከተደረጉት መካከል የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ አህመድ ቫሂዲ፣ ማህሳ አሚኒን በቁጥጥር ስር ያዋለው የስነ-ምግባር ፖሊስ ቡድን፣ የህግ አስከባሪ ሃይሎች እና የእስልምና አብዮት ጠባቂ የክልል ኃላፊዎች ይገኙበታል።
ዩናይትድ ኪንግደም የኮሙኒኬሽን ሚኒስትሩ ኢሳ ዛሬፑርን፣ የሳይበር ፖሊስ አዛዥ ቫሂድ መሐመድ ናስር ማጂድን እና በርካታ ባለስልጣናት ላይ ያነጣጠረ የራሷን አዲስ ማዕቀብ ይፋ አድርጋለች።
በሌላ ዜና የኢራቅ ኩርዲስታን ክልል ባለስልጣናት እንዳሉት ኢራን ሚሳኤሎችን እና የታጠቁ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በመጠቀም በግዞት በሚገኙ የኢራን ኩርዲሽ ተቃዋሚዎች ላይ ባደረሰችው ጥቃት የሁለት ሰዎች ህይወት አልፏል።