ሁለት የሴኔጋል የሕዝብ እንደራሴዎች ነፍሰ ጡር ባልደረባቸውን በመምታታቸው እስር ተፈረደባቸው

በዚህ ወቅት ነው ሌላኛው የሕዝብ እንደራሴ ማማዶው ኒአንግ ሆዷን የሚመቷት።

የፎቶው ባለመብት, Dakaractu TV HD

የምስሉ መግለጫ, በዚህ ወቅት ነው ሌላኛው የሕዝብ እንደራሴ ማማዶው ኒአንግ ሆዷን የሚመቷት።

በሴኔጋል ሁለት ተቃዋሚ የሕዝብ እንደራሴዎች ነፍሰ ጡር የሥራ ባልደረባቸውን በአገሪቱ ምክር ቤት ውስጥ በመማታታቸው የስድስት ወራት እስራት ተፈረደባቸው።

ግለሰቦቹ በምክር ቤት ክርክር ወቅት ኤሚ ንዳዬ የተባለች ነፍሰ ጡር የሥራ ባልደረባቸውን ሆዷን በእርግጫ መተዋታል።

ኤሚ ተቀናቃኝ ታዋቂ የሃይማኖት ሰው ከተቸች በኋላ ነው ሁለቱ ወንድ የሥራ ባልደረቦቿ የመቷት።

ማማዶው ኒአንግ እና ማስራ ሳምብ የተባሉት የሕዝብ እንደራሴዎች 8,100 ዶላር (አምስት ሚሊዮን ፍራንክ) ካሳ እንዲከፍሉም በዳኛ ታዘዋል።

ክስተቱን በርካቶች ያወገዙ ሲሆን፣ ስለ ሴቶች መብትም ክርክር አስነስቷል።

ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት እየተዘዋወረ ባለው ተንቀሳቃሽ ምሥል ማስራ ሳምብ የተባሉት የሕዝብ እንደራሴ በክርክር ወቅት ነፍሰ ጡሯን በጥፊ ሲመቷት ይታያል።

እሷም ወንበር አንስታ በመወርወር ራሷን ትከላከላለች።

በዚህ ወቅት ነው ሌላኛው የሕዝብ እንደራሴ ማማዶው ኒአንግ ሆዷን የሚመታት።

ቀጥሎም በምክር ቤቱ ውዝግብ ተነስቷል።

ብዙም ሳይቆይ ነፍሰ ጡሯ ኤሚ ራሷን ስታለች፣ ልጇን አጥታ ሊሆን ይችላል ተብሎ ተሰግቶም ነበር።

ኤሚ የአገሪቱ ገዢ ቤኖ ቦክ ያክር ፓርቲ አባል ናት።

ጠበቃዋ ባቡከር ሲሴ ለፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ እንዳሉት አሁን ከሆስፒታል ብትወጣም “አስጊ ሁኔታ ውስጥ ናት።”

የተንቀሳቃሽ ምሥል ማስረጃ ቢቀርብም፣ የሕዝብ እንደራሴዎቹ ነፍሰ ጡሯን አልመታንም ብለው በፍርድ ቤት ተከራክረዋል።

የሕዝብ እንደራሴዎቹ ያለመከሰስ መብት እንዳላቸው ቢከራከሩም እምብዛም ተሰሚነት አላገኙም።

ከጠበቆቻቸው አንዱ አብዲ ናር ንዳዬ ለኤኤፍፒ “አቤቱታ እስከሚገባ ድረስ ታስረው ይቆያሉ” ብሏል።

አምና የሴኔጋል መንግሥት ምክር ቤት ውስጥ አብላጫ ድምጽ ካጣ በኋላ በምክር ቤቱ ውጥረት ነግሷል።