የጋዛው ጦርነት እንዲቆም እስራኤል ያቀረበችውን ሐሳብ ባይደን ይፋ አደረጉ

ባይደን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሐማስ እስራኤል ያቀረበችውን ሐሳብ ተቀብሎ የጋዛው ጦርነት እንዲያቆም አሳሰቡ።

“ጦርነቱን ማቆሚያው ሰዓት አሁን ነው” ብለዋል።

ሦስት ክፍል ያለው ምክረ ሐሳብ ያቀረቡ ሲሆን፣ የመጀመሪያው ለስድስት ሳምንታት የሚቆይ የተኩስ አቁም ነው።

በእነዚህ ሳምንታት የእስራኤል ወታደሮች በርካታ ሰዎች ከሚኖሩባቸው የጋዛ አካባቢዎች ይወጣሉ።

የሰብአዊ እርዳታ “ጭማሪ” ይኖራልም ተብሏል። በምላሹ የታገቱ ሰዎችና ፍልስጤማውያን እስረኞች ይፈታሉ።

በሐሳቡ መሠረት ግጭትን “እስከወዲያኛው” በጋዛ ማቆምና ጋዛን መልሶ መገንባት ይገኝበታል።

ሐማስ ይህንን ሐሳብ “በበጎ አየዋለሁ” ብሏል።

ባይደን የመጀመሪያው የዕቅዱ ክፍል የእስራኤል ወታደሮች “በአጠቃላይ ተኩስ የሚያቆሙበት” ነው ብለዋል።

በምላሹም ታጋቾችና ፍልስጤማውያን እስረኞች ይፈታሉ።

“ትልቅ ነገር ነው። ሐማስ ተኩስ እንዲቆም እፈልጋለሁ ብሏል። እውነታቸውን ከሆነ ይሄን ትልቅ ዕድል መጠቀም አለባቸው” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

የተኩስ አቁም ተጨማሪ ሰብአዊ እርዳታ እንዲገባ ያግዛልም ብለዋል።

“600 እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች በየቀኑ ይገባሉ” ሲሉ አክለዋል።

በሁለተኛው የዕቅዱ ክፍል ወንድ ወታደሮችን ጨምሮ ታጋቾች ተለቀው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ይቀላቀላሉ።

ይህ ሲሆን “ዘላቂነት ያለው ግጭት ማቆም” ተግባራዊ ይሆናል።

የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን ሐማስ በዕቅዱ እንዲስማማ ጠይቀዋል።

“ሐማስ ሐሳቡን ተቀብሎ ግጭቱ መቆም አለበት። ሁላችንም ትክክለኛውን እርምጃ ከወሰድን ግጭቱ ይቆማል” ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጉቴሬዝም ሐሳቡን ደግፈዋል።

“ዓለማችን በጋዛ ብዙ ስቃይና ቀውስ አይታለች። መቆም አለበት። የባይደንን ጥረት አደንቃለሁ። የተኩስ አቁም እንዲተገበር፣ ታጋቾች እንዲለቀቁ፣ ያልተገደበ ሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲኖር፣ በመካከለኛው ምሥራቅ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም አካል የበኩሉን እንዲወጣ አበረታታለሁ" ብለዋል።

በመጀመሪያው እና ሁለተኛው የዕቅዱ ክፍል ላይ ድርድር ማድረግ ቀላል እንደማይሆን ባይደን ተናግረዋል።

ከቀናት በፊት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ በሚል ጦርነቱን ለማቆም የቀረበውን ሐሳብ ነቅፈዋል።

አሁን የቀረበው ሐሳብ ከዚህ ቀደም መስማማት ላይ ካልተደረሰበት ሐሳብ ጋር ተመሳሳይነት ቢኖረውም፣ አሜሪካ ሐማስን ወደ ድርድር ጠረጴዛ ለማምጣት የተኩስ አቁም መተግበርን እንደምታበረታታ ተገልጿል።

በመጨረሻው የዕቅዱ ክፍል የእስራኤላውያን አስክሬን እንደሚመለስ ይደረጋል።

በአሜሪካ እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እርዳታ የጋዛን መኖሪያ ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶችና ሆስፒታሎች መልሶ መገንባትም ይከናወናል።

ሐሳቡን የማይቀበሉ እስራኤላውያን ባለሥልጣኖች ሊኖሩ እንደሚችሉ ባይደን ገልጸዋል።

“የእስራኤል አመራር ይሄንን ዕቅድ እንዲደግፍ ጠይቄያለሁ። ይሄን አጋጣሚ ማጣት የለብንም” ብለዋል።

ሐማስ ከዚህ ቀደም እንዳደረገው እስራኤል ላይ ጥቃት መሰንዘር የሚችልበት አቅም አሁን እንደሌለው ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

ኔታንያሁ በበኩላቸው ታጋቾች ሳይለቀቁና የሐማስ ወታደራዊና አስተዳደራዊ አቅም ሳይወገድ ጦርነቱ አይቆምም ብለዋል።

አሁን የቀረበው ሐሳብ ይህንን ዕቅዳቸውን እንደሚያሳካም አክለዋል።

ሐማስ በበኩሉ ሐሳቡን “በአወንታዊነት” እንደሚቀበለው ገልጿል። ዕቅዱ ዘላቂ የተኩስ አቁም የሚያረጋግጥ፣ የእስራኤል ወታደሮች ከጋዛ እንዲወጡ የሚያስችል፣ ጋዛን መልሶ ለመገንባት መንገድ የሚከፍት እንደሆነ ገልጿል።

ዘላቂ የተኩስ አቁምን የያዘው ዕቅዱ “አወንታዊና ገንቢ ነው” ያለው ሐማስ እስራኤል ይህንን ለማድረግ “ግልጽ ስምምነት” ማድረግ አለባት ሲልም አሳስቧል።

አንድ ፍልስጤማዊ ባለሥልጣን እንዳሉት፣ ይህ ዕቅድ ጦርነቱን ለማስቆምና የእስራኤልን ወታደሮች ከጋዛ ለማስወጣት ማረጋገጫ ሊሆን አይችልም።

ዕቅዱን በሁለቱ ወገኖች መካከል እያቀረበች ያለችው ኳታር ናት።

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን የዮርዳኖስ፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ቱርክ ተሳትፎም እንዲታከልበት ጠይቀዋል።

“ሐማስ ስምምነቱን መቀበል አለበት። ከሐማስ ጋር ግንኙነት ያላቸው አገራት ሐማስ ስምምነቱን እንዲቀበል ማድረግ አለባቸው” ብለዋል ብሊንከን።

በጋዛ ያለው ቀውስ እየተባባሰ ከመሄዱ ጋር በተያያዘ ባይደን አሜሪካ ውስጥ ጫና እየበረታባቸው ነው።

እስራኤል በራፋሕ ያደረገችው ወረራ መስመር ያለፈና የአሜሪካን ፓሊሲ የሚያስቀይር እንዳልሆነ ዋይት ሀውስ ገልጿል።

ዋይት ሀውስ ይህን ቢልም እስራኤል ከቀናት በፊት በአየር ጥቃት 45 ሰዎችን መግደሏ ተዘግቧል።

ኔታንያሁ በአሜሪካ ምክር ቤት ቀርበው ማብራሪያ እንዲሰጡ የሕዝብ እንደራሴዎች የጠየቁ ሲሆን፣ መቼ እንደሚሆን ግን አልታወቀም።

በጋዛ እስራኤል በፈፀመችው ጥቃት ከ36,000 በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል። ከሐማስ ጥቃት በኋላ 252 ሰዎች በጋዛ ታግተዋል።